Monday, December 24, 2012


አንድ ምሳ በማንኩሽ

Mankush
 ማንኩሽ በጣም ጥንታዊ ቀጠና ናት፤ እንደ አክሱም ሮሐ ጎንደርና ሸዋ አንድ ወቅት የሃገሪቱ የፖለቲካ ቀጠና ሆና አገልግላለች፡፡ ይህ ታሪኳ ከታላቁ የዳኣማት ስርወ መንግስት የሚጀምር ነው፡፡ የ2005 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀንን ያስተናገደው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የበዓሉን ተጓዦች ካስተናገደበት ስፍራ አንዱ ማንኩሽ ነበረች፡፡ ማንኩሽ ከመድረሳችን በፊት አሻግሮ ይመለከተን የነበረው ጉባ ተራራ ነበር፡፡ ማንኩሽ ስንደርስም ከተማዋን ቁልቁል እየተመለከተ ጠበቀን… የማንኩሽ ህዝብ በሆታ ሲቀበለን ጉባ ግን እንደተኮፈሰብን ተያየን፡፡ ከከተማዋ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጉባ ተራራ ለጉባ ወረዳ መጠሪያም ሆኗል፡፡

Tuesday, December 11, 2012


ካፋና ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ

በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ የለቅሶ፣ የሰርግ፣የጸሎትና የፍቅር ዘፈኖች አሉ፡፡  በለቅሶ ወቅት ሟችን የሚያወድሱ ጀግንነቱን የሚተርኩ ዘፈኖች ይዘፈናሉ፡፡ በተመሳሳይ የሸካዎች የሰርግ ሥነ-ሥረዓትም በባህላዊ ዘፈኖቻቸው የታጀበ ነው፡፡ እነዚህ ዘፈኖች እንደ ባህሉ በሚቃኙ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎች የሚደምቁ ናቸው፡፡ ጥቂቶችን እንቃኛቸው ከቲንቦ እንጀምር የትንፋሽ መሳሪያው ቲንቦ የካፋን የለቅሶ ሥረዓት በማድመቅ ወደር የሌለው መሳሪያ ሲሆን ከእንጨት የሚሰራ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለአዋጅ የሚጠቀሙበት ሲሆን ሃይል ያለው ድምጽ በማውጣት ይታወቃል፡፡

ያንጉ ዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ

የአዘሎ ስር ውበት

አዘሎ ውብና ግዙፍ ተራራ ነው፤ እንደ ሌላው ተራራ አዘሎን ከባህር ጠለል በላይ ይሔን ያክል ብሎ በሜትር በመለካት ርዝመቱን መተረክ አይቻል ይሆናል… ምክንያቱም የአዘሎ ውበቱ ከስሩ ሆኖ መታየቱ ነውና፤ ከመልካ ወረር ሜዳማ ምድር አልያም ከገዳማይቱ የተንጣለለ መስክ ሲታይ አዘሎ ርቆ የቆመ ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ አካባቢው ዝናብ ሲያገኝ አዘሎ አረንጓዴ ካባ ይለብሳል፡፡ ዝናብ ከራቀው ግን ከል ይለብሳል፡፡ አዘሎ ክረምትና በጋ ልቡስን የሚቀይር ተራራ፤

አብረሃ ወ አጽብሃ

Tigeray
ውቕሮ ከአዲስ አበባ በ829 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከውቕሮ ከተማ በስተ ምዕራብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ በአብረሃ ወ አጽብሃ ዘመነ መንግስት የታነጹ ናቸው፡፡ ከአክሱም ነገስታት በዝናቸው ገናና ስማቸው ዛሬም ድረስ ህያው ከሆኑ ነገስታት መካከል በጉልህ የሚጠቀሱት ወንድማማች ነገስታት አብረሃና ወ አጽብሃ ናቸው፡፡ ዒዛናና ሲዛን የተባሉትና በክርስትና ስማቸው በጉልህ ሚታወቁት እነኚህ ሁለት ወንድማማች ነገስታት ጥለዋቸው ያለፍት በርካታ የታሪክ ሰነዶች፣ የጹሑፍ ቅርሶችና የኪነ ህንጻ ውጤቶች ኢትዮጵያን የእድሜ ጠገብ መስህብ ሃብቶች ባለቤት ያደረጓት ናቸው፡፡

አንጎለላን በወፍ በረር                       

ሰሜን ሸዋ ብዙ ያልተነገረለት ምድር ነው፡፡ በሁሉም ወረዳዎች ከሶስት መቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠሩ ቅርሶች በርካታ ናቸው፡፡ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች የሚበዙበት ሰሜን ሸዋ ከስምጥ ሸለቆ ምድር እስከ ከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎችን ያካተተ መሆኑ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ ቀጠና ያደርገዋል፡፡ እንደ መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ የቱሪዝም ስፍራ ያሉ ቦታዎች ቱሪዝሙ ላይ ከተሰራ ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማከናወን እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡

የሀላላ ካብ

king halala wall
ብዙዎች ስለምን ይህን የመሰለ ቅርስ ሚስጥር ሆኖ ሳይወራለት ቀረ በሚል ይቆጫሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ቀኑ አልመሸም በሚል የኢትዮጵያውያን ድንቅ እሴት ማሳያ ነውና እንተርክለት ሲሉ ዝናውን ይናገሩለታል፡፡ የሁሉም ድምር ግን ከዳውሮዎች ምድር ያለው ድንቅ ቅርስ የኢትዮጵያውያንነታችን የኩራት ተምሳሌትነትን መዘከር ነው፡፡

የቻይናውን ግንብ የመሰለው ይህ ግንብ እንዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል ቢባል ለሰሚው ግራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያዊ ሰሚ፡፡ ምክንያቱም ይህ ከአምስት መቶ ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረው ካብ አንድ ዙር ርዝመት 170 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ነው፡፡ በዚህ ርዝመቱ የጎፋ፣ የወላይታን፣ የወላይታን፣ የካፋንና የጅማን ድንበር በሙሉ ያካልላል፡፡

Friday, December 7, 2012


7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን
የዋዜማ በዓል ዛሬ በድምቀት ይከበራል፡፡

ሀሚኮ፡-
ከባህር ዳር ከተማ
የአማራ ክልሏ መዲና ባህር ዳር እያስተናገደችው ያለው 7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ቀጥሏል፡፡ በባህር ዳር ዩንቨርስቲ ፔዳ ጊቢ አዳራሽና በአዲሱ የክልሉ ምክር ቤት መሰብሰቢያ እየተካሄደ ያለው ሲምፖዚየም ዛሬ ግማሽ ቀን በተናጥል ቀጥሎ ከሰዓት በኃላ 10፡00 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በወጣው መርሀ ግብር መሰረት ምሽቱን በጣና ሀይቅ ላይ የጀልባ ትርኢት የሚቀርብ ሲሆን በባህር ዳር ከተማ ጎዳናዎች ላይ የብሄር ብሄረሰብ ባህል ቡድን አባላት የባህል ትእይንት ያቀርባሉ፡፡ በባህር ዳር ስታዲየም ነገ የሚከበረውን አብይ በዓል በማስመልከት ዛሬ ምሽቱን ደማቅ የዋዜማ ዝግጅትና የርችት ተኩስ ይኖራል፡፡

Wednesday, December 5, 2012


 
ባህር ዳር በከፍተኛ ሁኔታ ደምቃለች፤

7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ተጀምሯል፤

እንግዶች እየገቡ ነው፤ ምናልባትም እስከዛሬ በክልሉ ተዘጋጅተው ከነበሩ ኩነቶች የበለጠ ደማቁ ኩነት ሳይሆን አይቀርም፤

ከ100 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ታድመውበታል፤

የአማራ ክልል እርእሰ ከተማ የሆነችው የጣና ዳሯ ባህር ዳር በመብራት ባጌጡ ዘንባባዎቿ ተሞሽራ ከእስዛሬው የተለየ ደማቅ ሀገራዊ ኩነት እያስተናገደች ነው፡፡ 50 ሺ የሚደርስ ተመልካች የሚይዘው የባህር ዳር ስቴዲየም ለበዓሉ ማስተናገጃ ከተመረጡ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ አዲሱና አጠቃላይ ከ ግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚፈጀው የክልሉ የስብሰባ አዳራሽ የተወሰነው ክፍል ተጠናቋል፡፡ 2250 የሚበልጥ ታዳሚ በምቹ ሁኔታ ያስተናግዳል፡፡ የበዓሉ አካል የሆነው አንዱ ሲምፖዚየም በዚሁ አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

በዓሉን የሚታደሙትና ባህላዊ ትእይንት የሚያቀርቡት የብሄር ብሄረሰብ ልኡካን ቡድን ወደ ከተማዋ ሲገቡ በባህር ዳር ከተማ ህዝብ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በዓሉ በተለየ ሁኔታ ከነገ ህዳር 27 ጀምሮ በድምቀት ይከበራል፡፡

 

Thursday, November 15, 2012


ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን ዛሬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በሃገር አቀፍ ደረጃ ተከበረ!!!

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡

ዓለም በብዝሃነቷ የሚያውቃትን ያክል አብሮ የመኖርና የመተሳሰር እሴቶቿ ጎልተው ከወጡ ሃገራት መካከልም ትልቅ ስፍራ ይሰጣታል፡፡ ከመቻቻል ይልቅ  ከፍጹም ፍቅር በመነሳት አንዱ ለሌላው የሚኖርባት የወንድማማቾች ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ እነሆ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ሃገር አቀፍ የመቻቻል ቀንን አክብራለች፡፡

ዛሬ በብሔራዊ ቲያትር በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳውድ መሐመድ አለመቻቻል አስከፊነቱና የሚፈጥረውን ስጋት ለመቀነስ የሁሉንም ዜጎች ቁርጠኝነት በየጊዜው ለማደስ ይህን ዝግጅት ማዘጋጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ በእለቱ ዝግጅቱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

አቶ አውላቸው ሹምነካ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር ዘንድሮ የሚከበረው በዓል የመቻቻል ባህላችንን በማጉላት ለዓለም ተምሳሌት  እንሆናለን በሚል መሪ ቃል  እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በእለቱ ዶ/ር ሀሰን ሰይድ፣ አቶ ተመስጌን ዩሐንስ፣  አቶ መርከብ መኩሪያ፣ አቶ ተሾመ ብረሃኑ ከማል ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ውይይቱን መርተውታል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የታደመው እንግዳ ከወትሮው በተለየ በርካታ እና ዝግጅቱም በብሄራዊ ቲያትር ባህል ቡድን የተዋዛ ነበር፡፡

Tuesday, October 9, 2012


በባህል ዘርፍ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ሊመሰረት ነው፡፡

አመቻች ኮሚቴ ተዋቅሯል፤

በሃገራችን የባህል ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን የሚያካትት የምክክር መድረክ ለማቋቋም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጠራው ጉባኤ ላይ ከዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራ የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገው የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ተካፍለዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በቀረቡ የመነሻ ጽሑፎች የባህል ፕላት ፎርም ምስረታ ዓላማዎች፣ በቋንቋና ባህል እሴቶች እና በባህል ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሃገሪቱ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ውጥኑ የአለመቻቸውን ግቦች የተመለከቱ መነሻ ጽሑፎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በተለያየ አግባብ ለማህበራዊ ትርፍና ለኢኮኖሚያዊ ትርፍ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በጥቅሉ ባህል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን የሚሰሩ ባለድርሻ አካላትን በሙሉ ያካተተ የጋራ መድረክ ለመፍጠር እንዲቻል ስራውን የሚያከናውኑና የሚያመቻቹ አስራ አምስት አባላት በአመቻች ኮሚቴነት ተመርጠዋል፡፡

የተመረጠው ኮሚቴ አጠቃላይ የሆኑ የመመስረቻ ስራዎችን በማከናወን ብሔራዊ የባህል ባለድርሻ አካላት ምስረታ ጉባኤ አባላትን ለመጥራት አቅዷል፡፡

Wednesday, October 3, 2012


ማጫወት፣ መጋበዝ እና መውደድ የሚችለው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ

120 ሰዓታትን በደስታ

የ2005 ዓ.ም  የዓለም ቱሪዝም ቀን መስከረም 17 ቀን ተከብሯል፡፡ ሃገር አቀፍ ዝግጅት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተከበረ ሲሆን ከተከበረባቸው ስፍራዎች አንዱ ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ምድር ነው፡፡ ቱሪዝም ከዘላቂ የሃይል አቅርቦት ልማት ጋር ተቆራኝቶ እንዲከበር በመሪ ቃልነት የተከበረውን የዘንድሮ የቱሪዝም ቀን ለመታደም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከትመን ነበር፤

ከመተከል ዞን የጀመረው የሞቀ አቀባበል፣ እስከ ኦሮምያ ክልል ድንበር በዘለቀው የሽኝት ሥነ-ሥረዓት የ120 ሰዓታት እድሜ ነበረው፡፡ በዚህ እድሜ ውስጥ በዙምባራ ጥኡም ዜማ ታጅቦ የጉምዝ አያሌ ባህሎች ከልባችን ገብቷል፡፡ የበርታ እንግዳ አቀባበል፣ የኮሞ ጨዋታ የማኦ መስተንግዶ ስለቤኒሻንጉል ጉምዝ የምናወራውን እልፍ አድርጎታል፡፡

የቦሮ ሽናሻ ብሄረሰብ ከድንቅ ውዝዋዜው ጋር ቁርጡን እየመተረ መስቀሉን አብረንው እንድንታደም አድርጎናል፡፡ የማንኩሽ መስተንግዶ፣ የደጃዝማች ባንጃው ድንቅ እልፍኝ፣ የህዳሴው ምድር ውሎ አያሌ ትዝታዎች የታጨቁበት ጉዞ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ሀብታሙ ክልል አረንጓዴ ምድር እና ገና ያልተነገረ ታሪክ ያለው ነው፡፡

ተጫዋቹ፣ ተግባቢውና ለሰው ቅርብ የሆኑት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከተገናኘንበት ቀን ጀምሮ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንግዳ ተቀባይ አመራር እንዳለ አብነት ሆነው አሳይተውናል፡፡ ያዓ መሰራ እኩል ቀን ከገደልንባቸው መዳረሻዎች አንዱ ነበር፡፡ የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት ጉብኝት የማንጎ ሎጅ መስተንግዶ እና መሰል የመዝናኛ ጊዜዎች አይረሴና መልካም ነበሩ ዓመቱን እንደ ወቅቱ እየቆነጠርን ለመተንተን እድሜና ጊዜ ይስጠን፡፡  

Saturday, September 22, 2012


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎችና ጽ/ቤቶች በባህር ዳር ከተማ ከትመው የዓመቱን አፈጻጸም ገመገሙ!

ጎንደር 1ኛ ደረጃነቷን  አስጠብቃለች፡፡

ምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡


ከመስከረም 7 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም ባህርዳር የተሰበሰቡት የባህልና ቱሪዝም ሴክተር ተቋማት በዋናነት ዓመታዊውን አፈጻጸማቸውን የገመገሙ ሲሆን መርሀ-ግብሩ በክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ነው፡፡

በአፈጻጸም ደረጃ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ቀጥሎ የቱሪዝም ዳይሮክተሪዋን ባስመረቀች ማግስት የጎንደር ከተማ አስተዳደር አንደኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ በተያዘው ዓመት አያሌ የተለዮ ተግባራትን ያከናወነችው ጎንደር ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የሙዚየም ቀን ተከብሮባታል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋ ባሻገር በትግራይ በነበረው የከተሞች ቀን ላይ በትግርኛ ቋንቋ በተዘጋጁ የፕሮሞሽናል ቁሳቁሶች እራሷን ያስተዋወቀችው ጎንደር፤ በዚሁ ዓመት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻዎችን ያካተተ የቱሪዝም ገቢ አመንጪ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ የገባችበት ዓመት ነበር፡፡


Friday, September 14, 2012

tuba

መስቀል በአዲግራት

መስቀል በአዲግራት
 
መስቀል በሃገራችን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በተለይም የደመራ በዓል ከፌስቲቫል ቱሪዝም ሀብታችን ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህንን በዓል የሰው ልጆች ሁሉ እሴት ለማድረግም ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ መስቀልን በዩኔስኮ ለመመዝገብ በቅቷል፡፡

መስቀል እንደ የኢትዮጵያውያን እሴትና ባህል ከዳር ዳር የሚከበር ከአደይ ጋር አብሮ የሚፈካ፣ ከዘመን ጋር የሚጠባ በዓል በመሆኑ ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን አድርገዋለል፡፡

በድንቅ እሴት የተሞላውና ብዙ ሳይነገርለት የኖረው የምስራቃዊ ትግራይ ዞን የመስቀል በዓል አንዴ ሌላ የባህል ሃብት መስህባችን ነው፡፡

Tuesday, August 21, 2012


ኢትዮጵያ በብሄራዊ ሀዘን ላይ ትገኛለች፤

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስክሬን ትናንት ምሽት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፤

መንግስት መደበኛ የመንግስት ስራ ሳይዘጋ የሃዘን አዋጁ እንዲቀጥል አውጇል፤

ላለፍት 21 ዓመታት ሃገሪቱን በግንባር ቀደምነት ሲመሩ የነበሩት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአህጉሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን የሚታደሙት፤የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር፤ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የሃገራችን መንግስት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም ለህዝቡ አስታውቋል፡፡

ሰኞ ለማክሰኞ ዋዜማ ከእኩለ ለሊቱ በፊት መሞታቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው 21 ዓመታት የሚመሩት መንግስት ሀገራችን የቱሪዝምና የባህል ፖሊሲዎች እንዲኖሯት በማድረግ፣በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ፣ አዳዲስ ፓርኮች እንዲለሙ፣ ቅርሶች የቅርሱ ባለቤት የሆነው ህዝብ እንዲያስተዳድራቸው በማድረግ እና የቱሪዝም ልማቱን የሚያግዝ የብድር ስምምነት በማድረግ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ላይ በማተኮር፣ በርካታ የባህል ልውውጥ መድረኮችን ሀገራችን እንድትሳተፍ በማስቻል ያበረከቷቸው ተግባራት የሚወደሱ ናቸው፡፡

የሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን እና የቱባ መጽሔት ባልደረቦች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማንን ሀዘን እየገለጽን ለባለቤታቸው፣ለትግል ጓዶቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

Monday, August 20, 2012


ብጹእ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማይ፤ ፓትረያሪክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ሊቀ-ጳጳስ ዘ አክሱም፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት፤ የዓለም ሐይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፤ የሰላም አምባሳደር በተወለዱ በ76 ዓመታቸው አረፍ፤



ለሃገሪቱ ቱሪዝም ልማት እና ለሙዚየሞች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጾ ማበርከት የቻሉ አባት ነበሩ፤



የዛሬ 76 ዓመት በአድዋ ከተማ አቅራቢያ በአባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ..  ከካህን ቤተሰብ፣ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ አራደች ተድላ ተወለዱ፤ የያኔው ገብረ መድኅን የአሁኑ  አቡነ ጳውሎስ፣ከዚያም  በጥንታዊው አባ ገሪማ ገዳምና በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በማቅናትም ከሩሲያው የቅዱስ ቭላድሚር ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ በኦርየንታልና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የነገረ መለኮት ይትበሐል (ትምህርት) 1954 . ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በየል ዩኒቨርሲቲ በኦሪየንታል፣ በምሥራቅና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከትና ልዩነት ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪን 1958 . ሲያገኙ፣ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማስተርስ ኦፍ ቴኦሎጂ ዲግሪን 1964 .. ተቀብለዋል፡፡ በዚያው ዩኒቨርሲቲ 1980 .. የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪያቸውን ያገኙት ስለእግዚአብሔር ህልውና እና ስለፍልሰታ ማርያም በጻፏቸው የጥናት ድርሳኖች ነው፡፡

Thursday, August 9, 2012


የሲዳማ ዘመን መለወጫ /ፍቼ/ በአል አከባበር

ከይረጋዓለም ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር


ፍቼ በዓል በሲዳማ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

“ፍቼ” በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዘመን መለወጫ በአል ነው፡፡ በአሉ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሂደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አድምታ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ፍቼ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን ከዚህም በሰፋ መልኩ በባህላዊ አደባባይ /ጉዱማሌ/ በጋራ በድምቀት የማክበር ሂደትን ያካትታል፡፡ ለአከባበሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቅድሚያ እንደ አቅሙ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ አንጻር የቤቱ እመቤት ለበአሉ ቅቤ ታጠራቅማለች ወተት በታጠነ ማለፊያ “ቁሹና” /የወተት እቃ/ ታከማቻለች የእንሰት ውጤት የሆነውን ቆጮ ለበአሉ በሚሆን መጠንና ጥራት ከወዲሁ ታሰናዳለች፡፡

Friday, July 20, 2012


ቱሪዝም በዳዉሮ
ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ


የዳዉሮ ዞን  ከኢትዮጵያ ዉብ ገፅታ ማሳያዎች አንዱ ነዉ፡፡ ዞኑ በደቡብ ክልል የሚገኝ ሲሆን የዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ ትባላለች፡፡ ታርጫ ገስጋሽ ነገር ግን በሚሌኒየሙ ከተወለዱ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ከሐዋሳ በ282 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በሻሸመኔ አድርገዉ በወላይታ ሶዶ የሚጓዙ ከሆነ 455 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ በሌላኛዉ መንገድ በጅማ አርገዉ የሚጓዙ ከሆነ ደግሞ በ479 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚያገኟት ከተማ ስትሆን ከተማዋ በየግዜዉ እያስመዘገበች ባለዉ እድገት ሳቢያም የብዙዎችን ትኩረት ስባለች፡፡

      በደቡብ ከጋሞ ጎፋ በምዕራብ ከኮንታ ልዩ ወረዳ በሰሜን ምዕራብ ከኦሮምያ ክልል በሰሜን እስከ ሰሜን ምስራቅ ከከንባታ ጠንባሮ ዞን በምስራቅ ከወላይታ ዞን ይዋሰናል፡፡ ከሰሜን ምዕራብ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በጎጀብና በኦሞ ወንዞች ተፋሰስ የተከበበዉ የዳውሮ ዞን የብዙ እሴቶች ማዕከል እና እንብርት ነዉ፡፡ ከአምስት በላይ በሆኑ ብሄረሰቦች መከበቡ ዳውሮን ልዩ የባህል አምባ ያደርገዋል፡፡

Wednesday, July 4, 2012


ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ገመገመ

ብዙዎቹ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡

ፓርኮችን በመጎብኘት ረገድ የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የባህል ልውውጥና ግንኙነት አፈጻጸሙ 108 በመቶ ሆኗል….

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በመገምገም የአፈጻጸም ልኬቱን በቁጥርና በመቶኛ አስቀምጧል፡፡ በዘጠኝ ወሩ አስራ ሶስት የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ሲሆን አስራ አራት ለማከናወን በመቻሉ ከእቅዱ ያለፈና 108 በመቶ የሆነ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ብቻ 9 የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታስቦ 11 ለማከናወን ሲቻል አንድ ባህላዊ የሙዚቃ ኪነት ቡድን በውጪ ሃገር ትርኢት ለማቅረብ በታሰበው መሰረት በህንድ ሶስት ከተሞች ትርኢቱን በማሳየት ሃገሪቱንና የህዝቦቿን እሴት በሚገባ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡

በዘጠኝ ወራቱ አፈጻጸም የቱሪስቶች ቁጥር 474,249 ደርሷል፤ ይህም ከእቅዱ አንጻር 88 በመቶ ሲሆን በቋሚ ኤግዚቢሽን ጎብኚዎች ረገድ 106,084 የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች በብሄራዊ ሙዚየም የቋሚ ኤግዚቢሽን የማስጎብኘት እድል ተፈጥሯል፡፡ በሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ገረድም በተለይም ፓርኮችን በመጎብኘቱ አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን 30,110 የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች የሃገሪቱን ፓርኮች ጎብኝተዋል፡፡ የሴቶቹ ቁጥር ደግሞ 12,405 ነው፡፡ ይህ ቁጥር 42,246 የውጪ ጎብኚዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ፓርኮችን የመጎብኘት ባህል እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ በአለፍት ዘጠኝ  ወራት ከቱሪስቶች 371,811,216 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ የአንድ ቱሪስት አማካኝ የቆይታ ግዜ 6.5 ሲሆን የቀን ወጪው ደግሞ 120.6 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ያገኘንው መረጃ ያመላክታል፡፡


Sunday, June 24, 2012


በመሰሮ ኢበሌን በሰሮ

እንደ ስልጤ ያያም ኢልቅ/ የዘመን አቆጣጠር/ መሰሮ 1/ ሰኔ 20/

 የስልጤ የዘማን ኢጋኘ አያም/ዘመን መለወጫ

ያያም ኢልቅ ይሉታል የቀን አቀማመር ስልት ዘዴአቸውን፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኙት ስልጤዎች የራሳቸው የቀን አቀማመር ካላቸው የሃገራችን ህዝብ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ወቅት የዓመቱ የመጨረሻ ወር ነው እንደ ስልጤዎች የቀን አቀማመር ሰኔ 20 ዓዲስ አመታቸው ነው፡፡ መሰሮ 1 ይሉታል እነሱ፡፡ ዘንድሮም በእለተ አርጴ/ረዕቡ/ ሰኔ 20 የሚውለው የስልጤ የዘመን መለወጫ ለስልጤዎች አዲስ አመታቸው ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዘመን አቆጣጠሩ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች የተጀመሩ ሲሆን የዘመን ቀመሩ መነሻ..መሰረት ያደረጋቸው ዋና ዋና መገለጫዎችና ሌሎች ሚስጥራቱ  ዙሪያ ካተኮሩት ጥናቶች በመነሳት ስለ አቀማመሩ ሰፊ መረጃ ይገኛል የሚል እምነት አለ፡፡




                                                           ለመላው የስልጤ ህዝብ ሀበይ ለሀጂሲ ዘማን በወገሬት አጄጄሙ! ብለናል

Tuesday, June 19, 2012


ብሄራዊ የቱሪዝም መማክርት ጉባኤ ውይይቱን አካሄደ

ወቅታዊ ጉዳዮች ተነስተዋል፤

የቱሪዝም ሥነ-ምግባር መምሪያው ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ዜና፡- ሀሚኮ

ትናንት ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ሙሉ ቀን በአዲሱ ራንድ ሰን ብሉ ሆቴል የተካሄደው የብሄራዊ የቱሪዝም መማክርት ጉባኤ በዋናነት በዓለም ባንክ አማካኝነት የተዘጋጀውንና የሃገራችን ቱሪዝም አጠቃላይ ጠቀሜታዊ ይዘት ላይ ያተኮረው የጥናት ጥቅል ውጤት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

Friday, June 15, 2012

አሁን አየ ዓይኔ     
የቱሪዝም ንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ
የሃገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለዘመናት ይጓዝበት ከነበረው ከርፋፋና ቀርፋፋ አካሄድ ወጥቶ ያለፍትን ጥቂት ዓመታት ሶምሶማ ወደሚባል ፍጥነት እየገባ መጥቷል፡፡ የሁልም ጊዜም ቁጭታችን ባለን ነገር ባለመጠቀም ከሌላቸው ህዝቦች ውራ ቁጥር መግባታችን ነበር፡፡ ስለአለን ነገር እንኳን ስናስብ ከሌላው የምንልቅበት በርካታ ነገር አለ፤ እኛ ያለን ሃብት እውቀት ገንዘብና ቴክኖሎጂ ሊያመጡት አይችሉም፤ ብዝኃ- ህይወትን ከባህል ጋር፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ሃብቶችን ታድለናል፡፡ ለጥቁር ህዝብ ተምሳሌት የሚሆን ትናንትና ያለን ህዝቦች ነን፤ ይህንን ተጠቅመን መጠቀም አቅቶን ኑሯል፤ እንደውም አናወራውም ስለራስ ማውራት መታበይ ነው የሚል ብሂል አለን፤ ስለራስ ካልተወራ ውጤት የማይገኝበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልባችንን የምናሳርፍበት አልሆን ያለውም ለዚህ ነው፡፡

Thursday, June 7, 2012


                                       ራስ ግንብ
ይህ ቤተመንግስት የተገነባው በከፍታ ቦታ ላይ ሲሆን ከፋሲል ቤተ-መንግስት በስተሰሜን በኩል 300 ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡  ይህ ቤተመንግስት ባለሁለት ፎቅ ሆኖ ከመሰረቱ ሰፊና ወፍራም ግንባታ ያለው ሲሆን ወደላይ እየቀጠነ የሚሄድ ነው፡፡

ሁለት ወታደሮች (ማማዎች) ሲኖሩት ሶስተኛው ግን በባለ አራት ማዕዘን ማማው መሐል ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት የአሰራር ስልቶች በዘመኑ ሰቀላ ግንብ ወይም ከበሮ ግንብ በመባል ታወቃሉ፡፡ በተለይ አራተኛውና ትልቁ ማማ (Tower) ይህ ቤተመንግስት ግርማ ሞገሱ የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ ይህ ሁሉ ውበትና የአሰራር ጥበብ የፈሰሰበት ቢሆንም  ከአፄ  ፋሲል  ቤተመንግስት (ግንብ) በመጠኑ ያነሰነው፡፡ ነገር ግን በቅርጹና በአሰራር ጥበቡ ተመሳሳይነት አለው፡፡

                  ራስ ግንብ  ሙዚየም
               RAS GENB MUSUME