Tuesday, February 21, 2012


የጭልጋ ወረዳዋ 
ላዛ ደብረ መንክራት ባታ ማርያም ገዳም 

Gondar Chilga werda- laza mariyam
በአንደኛው የጭልጋ ወረዳ ማዶ የምትገኝ ድንቅ የቱሪስት መስህብ ናት፡፡ የላዛ ደብረ መንክራት ባዕታ ማርያም ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳ የምትገኝ ጥንታዊት ገዳም ስትሆን ገዳሟ ከአዘዞ መተማ በተዘረጋው የአስፋልት መንገድ ከወረዳው ከተማ አይከል ከመግባታችን 7 ኪ.ሜ በፊት ለከተማው ህዝብ ውሃ ከሚሳብበት /ከውሃ ልማቱ/ ከዋናው የአስፋልት መንገድ በስተቀኝ በኩል ከ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኃላ የሚያገኟት ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ ናት፡፡
ወደ ገዳሟ ሲደርሱ ገዳሟ ያረፈችበት ቦታና መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ ይማርካል፡፡ በገዳሟ የሚገኙ የአብነት ተማሪዎች ዝማሬና ድምጽ ይቀበልዎታል፡፡ ገዳሟ የተቋቋመችው በአፄ ይኰኖ አምላክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ በአሁኑ ሰዓት በገዳሟ  የሚያገለግሉ የዕድሜ ባለፀጋ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳን ገዳሟ በአፄ ይኰኖ አምላክ ዘመን መንግስት ብትቋቋምም ገዳሟ የተገደመችው በአፄ ጻዲቁ ዩሐንስ ዘመነ መንግስት እንደሆነ የሚያስረዱ አባቶች አሉ፡፡ የላዛ ደብረ መንክራት ባዕታ ማርያም ገዳም በውስጧ ጥንታዊ የሆኑ የብራና ጽሁፎችን፣ የብርና የወርቅ መስቀሎችን እንዲሁም በርካታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መፅሃፍት የሚገኙባት ጥንታዊትና ታሪካዊት ገዳም ናት፡፡

ሎካ አባያ ፖርክ


ሎካ አባያ
ከኢትዮጵያ ህዳሴ ጋር አብሮ የተበሰረው ፖርክ
ከሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝም መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ጋር በመተባበር


ሎክ አባያ በምሽት
Locka abaya park
በውቡና ለምለሙ የሲዳማ ዞን የሚገኘው ሎካ አባያ ፖርክ ለዞኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚያ በአለፈ ከኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን የእድገት ጉዞ ብስራት ጋር አብሮ መበሰሩ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የወል የሆነ የደስታ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ሎካ አባያ ከሃዋሳ ከተማ ተነስተው ወደ ዲላ በሚወስደው መንገድ ተጉዘው አፖስቶ ሳይደርሱ በስተቀኝ ወደ ሎካ አባያ ወረዳ በመጓዝ የሚያገኙት ፖርክ ነው፡፡ ከፖርኩ በቅርበት የምትገኘዋ ከተማ ሐንጣጤ ትባላለች ከተማዋ ከሲዳማ ዞን ወረዳዎች አንዱ የሆነው የሎካ አባያ ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን ከሃዋሳ በ55 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የሎካ አባያ ወረዳ 40.000 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን የወረዳው ከፊል አካል በስምጥ ሸለቆ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከአጠቃላዩ የቆዳ ሽፋን ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነው ቆላማ (እርጥብና ደረቅ) የአየር ንብረት ያለው ነው፡፡ የወረዳው አማካኝ የሙቀት መጠን 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፡፡

ጉዞአችን ወደ ሎካ አባያ ፖርክ ነው መንገዱ ለተሸከርካሪ ምቹ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ግራና ቀኝ የሲዳማ ብሄረሰብ የቆላ ቤት ውበትና የህብረተሰቡን አኗኗር እየተመለከቱ በማይሰለች ተፈጥሮ መሀል እየበረርን ነው፡፡ ግራና ቀኝ የሚያምርና አስገራሚ መልከአ ምድር እየተመለከትን የምንጓዝበት የሎካ አባያ ወረዳ ዙሪያ ገባ ሎካ አባያ ፖርክ ከመድረሳችን በፊት እራሱ በብዙ መልኩ በተፈጥሮ እንድንደመም የሚያደርግ ነው፡፡ ከሃገራችን ፖርኮች በእድሜው ወጣት ነገር ግን የሚያድግ ልጅ ከመሰረቱ ያስታውቃል እንዲሉ ከጀማሬው በርካታ ጥሩ ስራዎች የተሰሩበት ፖርክ ነው፡፡ የፖርኩ ባለሙያዎች ወጣቶች መሆናቸው ደግሞ እንደ ልብ በረው የሚሰሩ የነብር ጣቶችን የተሞላ ፖርክ ያደርገዋል፡፡

ወደ ፖርኩ የምናደርገው ጉዞ ቀላል ቀልጣፋና አስደሳች የመሆኑ ሚስጥር የፖርኩ ባለሙያዎች አብረውት ማደግ ለሚፈልጉት ፖርክና ለሥራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ሥፍራ ከአዲስ አበባ በ340 ኪ.ሜትር ከሃዋሳ ከተማ ደግሞ70 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከሚባሉት ፖርኮች አንዱ ከሆነው የሎካ አባያ ፖርክ እንገኛለን፡፡ በቅርቡ በክልሉ አዲስ ከተከለሉ ፖርኮች አንዱ ሆኖ የተከለለው የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ሰፊ ጥናት ተደርጐበት በሲዳማ ዞን ውስጥ በአባያ ሃይቅ ደቡባዊ አቅጣጫ ላይ የተዘረጋ ነው፡፡ 500 ኪ.ሜትር ስኩየር ቦታ የሚሸፍነውን የሎካ አባያ ፖርክ ለመከለል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ መሰራቱን አቶ በዛብህ በየነ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ አስተባባሪ ይገልፃሉ፡፡ እንደ አቶ በዛብህ ገለፃ ህብረተሰቡን በማወያየት ዘላቂ ጠቀሜታውን በማስረዳት በማካለሉ ሥራ አሳታፊ ሥራ ለመስራት ተችሏል፡፡ የፖርኩ ክፍል በሰሜን በኩል ከአባያ ሃይቅ፣ በደቡብ በኩልም እንደዚሁ የአባያ ሃይቅና የጉዶቦ ወንዝ በምዕራብ በኩል የብላቴ ወንዝ ያዋስኑታል፡፡ ሰፊው የፖርኩ ግዛት ከዚህ ቀደም በመኖሪያ መንደሮች የተሞላ አለመሆኑ ፖርኩን ከጅምሩ ጥብቅ ክልል የማድረጉ ሥራ የሰመረ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ተፈጥሮ


የእግዜርን አዳራሽ ማን ሰራው
አርባ ምንጭ ከተማ ስሟ ራሱ መስኸብ ነው፡፡ ከተማዋን የማያውቋት ብዙ ሰዎች ስሟ ሲጠራ በምናባቸው የሚስሉት ቱሪዝምን ነው፡፡ ውበትና ተፈጥሮ ይታያቸዋል አርባ ምንጭ እንኳን በእውን በምናብም ታምራለች፡፡ የስሟ መጠሪያ ከግርጌዋ ከተዘረጋው ሰፊ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የመሸጉት ብዙ ምንጮች ናቸው፡፡ የእነዚህ ምንጮች ቁጥር ከአርባም እንደሚዘል ይነገራል፡፡ ከጥቅጥቁ ደን መሽገው ለቆጣሪ ቢያስቸግሩና በየቦታው ቢንፎለፎሉ በአርባ ተወስነው ለዚህች ውብ የጐብኚዎች መዳረሻ ከተማ ስያሜ ሆኑ፡፡ እነዚህ ውብ እልፍ ምንጮች የተሸሸጉበት ጥቅጥቅ ደን ነጭ ሳር ብሔራዊ ፖርክ ሲያቀኑ የሚያቋርጡት ነው፡፡ ስፍራው ለአርባ ምንጭ ከተማ ቅርብ በመሆኑ ለጐብኚዎች ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ በስፍራው ጐብኚዎች የሚኖራቸው ቆይታ ከተፈጥሮ ጋር የሚዋደዱበት እድልን ይፈጥራል፡፡

ከጥቅጥቁ ደን መሀል አንድ ልዩ ቦታ አለ፡፡ ልዩ ስሙ የእግዜር አዳራሽ ነው ረጃጅም ዛፎች በእቅድ የተተከሉ ይመስል እንደ ምሰሶ በረድፍ ቆመዋል ቅርንጫፎቻቸው ደግሞ ከአናት ተቆላልፈው አንዱ በአንዱ ላይ ተኝቷል፡፡ በዚህ ትስስር ውስጥ ሾልኮ የሚገባ የፀሐይ ጨረር መሬት ሲያርፈ ጉልበቱ በነፋሻማ አየር ይዋጣል፡፡ ከዚህ ገላጣ ግዙፍ የተፈጥሮ አዳራሽ ዙሪያ እንደ ሌላው የደኑ አካል ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎች ቆመውበታል፡፡ የመሬቱ ወለል ከዛፎቹ ቅርንጫፎች በሚረግፍ ቅጠሎች ተሞልቶ ከምድር በላይ ሌላ ወለል ሰርቷል፡፡ ይህ ተፈጥሮ ያበጀችው ድንቅ አዳራሽ ነው፡፡ ውበቱ ተፈጥሮ ከምታሰማው ድንቅ ድምፅ ጋር ተዳምሮ እልፍ ትእይንት ነው፡፡ ተፈጥሮ የሰራችው ከውስጥ የሚቆራኝ ሃሴት እንደሚፈጥር ማሳያ ነው፡፡

የእግዜር አዳራሽ የሚለው ስያሜ ይህንን ውብ የተፈጥሮ ቅጥር ማንም እንዳልሰራው ለማሳየትና የራሷ የተፈጥሮ ገፀ በረከት እንደሆነ ለመግለፅ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡ በእርግጥ እግዜር ካልሆነ ፍጡር እንዲህ ያለውን ውበት ከእንዲህ ያለው ደን ውስጥ በምን ተአምር ሊያበጀው ይችላል፡፡ የሰው ልጅ እጆች መጥረቢያ ይወዳሉ ልባቸው በተፈጥሮ ይጨክናል፤ ተፈጥሮ ግን አትሰስትም እንዲህ ያለውን ድንቅ ስፍራ በእራሷ የአፈጣጠር ክህሎት አቀናብራ ለሰው ልጅ ትቸራለች፡፡ የእግዜር አዳራሽ ሰፊ ነው፡፡ የ2002 ዓ.ም የአለም ቱሪዝም ቀን በሃገራችን ሲከበር በሃገር አቀፍ ደረጃ የተከበረውን በዓል ያስተናገደ ድንቅ ስፍራ ነው፤ ብዙ እንግዶችን በሚያምረው ጥላው ከልሎ የአእዋፋትን ዜማ እየጋበዘ ንፁህ አየር እየሳበ እንግዶችን የተቀበለ አዳራሽ ነው፡፡ የእግዜር አዳራሽ በአማረ ተፈጥሮ ውስጥ መሞሸር ለሚፈልጉ ድል ያለ ሰርግ ማስደገስ የሚችል ከተዘጋጀው ድግስ መሃል የራሱን ንፁህ አየር የሚጋብዝ አስደናቂ ስፍራ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ከደረሱ የእግዜር አዳራሽ የት ነው? ብለው ይጠይቁ፡፡

Monday, February 20, 2012


ዜና





በጎንደር ከተማ ሁለት የአብነት ት/ቤቶች ተቃጠሉ



በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ጎንደር ከተማ በሳምንት ልዩነት በሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በተነሡ የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች አንድ ጥንታዊ የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤት ሌላ የቅኔ ቤተ ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ወደሙ፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኘው የሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምእት መጻሕፍተ መነኮሳት ትርጓሜ ት/ቤት ሙሉ በሙሉ የወደመው የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ላይ መንሥኤው ባልታወቀ አኳኋን በተነሣ የእሳት ቃጠሎ መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ ተናግረዋል፡፡ የትርጓሜ ት/ቤቱ በኢትዮጵያ ከአራቱ ጉባኤያት አንዱ የሆነውን መጻሕፍተ መነኮሳትን ብቻ የሚያሄድ ቤተ ጉባኤ እንደነበር ተገልጧል፡፡

 በእሳት ቃጠሎው የተማሪዎች ማደሪያዎች እና የመምህሩ መኖሪያ የነበሩ በአጠቃላይ ዘጠኝ ክፍሎች በውስጣቸው ከሚገኙ በ1714 ዓ.ም ከተጻፉ የብራና መጻሕፍተ መነኮሳት(ማር ይሥሓቅ፣ ፊልክስዩስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ) እና ሌሎች የኅትመት መጻሕፍት ጋራ ጨርሶ መቃጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእሳት አደጋ መከላከል መኪኖች እና የከተማው ምእመናን የተረባረቡ ቢሆንም ጉዳቱን ለመቆጣጠር የተቻለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት በማድረግ ብቻ ነበር፡፡

የመጻሕፍተ መነኮሳት ቤተ ጉባኤው በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በማኅበረ ቅዱሳን በጀት የተተከለላቸው በአጠቃላይ 15 መደበኛ ደቀ መዛሙርት እና ከከተማው አድባራት እየመጡ ትምህርቱን በግላቸው የሚከታተሉ በርካታ ተማሪዎች እንደነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰጣቸው በታወቁት የአራቱ ጉባኤያት ሊቁ አየለ ዓለሙ በ1929 ዓ.ም የተመሠረተው ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ጉባኤው ማሄድ (መቀጠል) ያልቻለ ሲሆን መምህሩ ተሾመ ታደሰ እና ደቀ መዛሙርቱ በየምእመናኑ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ ቤተ ጉባኤው የሚገኝበትና በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ በኒቂያ በተሰበሰቡ 318ቱ ርቱዓነ አበው ሊቃውንት ስም የተሠራው - የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን በ1880 እና በ1881 ዓ.ም በወራሪው ድርቡሽ ጦር ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ከተቃጠለ በኋላ ተመልሶ አልተሠራም፡፡

በተያያዘ ዜና በዚያው በጎንደር ከተማ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውና በዐፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት(17ኛው መ.ክ.ዘ) በኖሩት የቅኔ ሊቅ መምህር ክፍለ ዮሐንስ የተመሠረተው የገለአድ የቅኔ ቤተ ጉባኤ የካቲት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተገልጾአል፡፡
በዕለቱ ከቀትር በኋላ ከተማሪዎች ጎጆ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው መንሥኤ ለጊዜው ያልታወቀ ቢሆንም ተማሪዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው የገባውን ጉንዳን ለማራቅ የተጠቀሙበት እሳት እንደሆነ ተገምቷል፡፡ በቃጠሎው 26 የቅኔ ደቀ መዛሙርቱ መኖሪያዎች የሆኑ ጎጆ ቤቶች በውስጣቸው ከሚገኙ የተማሪዎቹ አልባሳት፣ መጻሕፍት እና ጥሬ ብሮች ጋር መውደማቸውን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

Thursday, February 16, 2012


የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ
በስሩ ከሚገኙ የ11 ዞንና የሶስት ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎች ጋር በ2004 ዓ.ም ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ዙሪያ መከረ

ጎንደር በግማሽ አመቱ አፈጻጸም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ መሪነቱን ይዛለች፣
የክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ የጎንደር ከተማን አስተዳደር እና የቱሪዝም ልማት ስልቱን አወድሰዋል፡

ዜና- ቱባ የካቲት 9/2004 ዓ.ም

አቶ ሙሉጌታ ሰይድ
የአማራ ብ/ክ/መ/ ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ ኃላፊ
Ato mulugata side ANRS tourism,calture and park dev.office hade 



 የካቲት 7 እና 8/2004 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በዳንግላ ከተማ በተካሄደውና ቢሮው የየዞንና ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎችን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም በገመገመበት በዚህ ጉባኤ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያም ምክክር ተደርጓል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባህል እና ቱሪዝም ልማቱ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ በመጣው የአማራ ክልል በተለይም በቢሮው እና በክልሉ ባሉ ዞንና የከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎች መካከል ያለው ግንኙነት እየጠነከረ መጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እርስ በእርስ ሴክተሩን ለማልማት የሚደረገው ውድድር የሃገሪቱ ቱሪዝም ላይ በተጨባጭ የሚታይ አሻራውን እያሳረፈ እንደሆነ ለማየት ተችሏል፡፡ የጎንደር ካርኒቫል፣ አሸንዳና በቅርቡ የተደረገው የአዊ የባህል ትእይንት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
የ2004 ዓ.ም ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ በአማራ ክልል የሚገኙ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በደረጃ እንዲቀመጡ አስችሏል፡፡በዚህም መሰረት ከ11 የዞንና ከ3 ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎች፡-
<!--[if !supportLists]-->Ø      <!--[endif]-->የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ 1ኛ
<!--[if !supportLists]-->Ø      <!--[endif]-->የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ 2ኛ
<!--[if !supportLists]-->Ø      <!--[endif]-->የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ 3ኛ
<!--[if !supportLists]-->Ø      <!--[endif]-->የዋግኽምራ ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ 4ኛ
<!--[if !supportLists]-->Ø      <!--[endif]-->የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ 5ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ ደረጃውን የተጎናጸፉት  በግማሽ ዓመቱ ባከናወኑት ተግባር ነው፡፡
በጉባኤው የራሳቸውን ምርጥ ተሞክሮ እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት ወረዳዎች መካከል አንዱ በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው የጭልጋ ወረዳ አስተዳደር ነበር፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ ወጣት አስቻለው አቡሃይ ጭልጋ ላይ በተለይም የቁንጅና ውድድርን ከማካሄድ ባለፈ ወደ ማህበራዊ ችግር ፈቺነት ያሸጋገሩበትን ስልት፣በአገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻቸው ላይ የሰሩትን የሱፐር ቪዥን ስራና መሰል የተሳኩ ተግባሮቻቸውን ለጉባኤው አካፍሏል፡፡
የክልሉን የቱሪዝምና ባህል ልማት በተመለከተ በርካታ ሃሳቦችን ለጉባኤው ያካፈሉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ በተለይም የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴክተሩ እንዲለማ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አወድሰው የግምገማ መድረኩ የተሳኩ ተሞክሮዎችን የሚለዋወጡበት እንዲሆን ጠቁመዋል፡፡   

Tuesday, February 7, 2012

አንፋርጌ እና ደብረ እንቁ


ቅምሻ ከሰማዳ መስኽቦች ሁለቱን
ስማዳ በአማራ/ብ/ክ/መ በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ መዛግብት የቀድሞ የአካባቢው መጠሪያ ሀገር ቢዝን እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ የአሁኑ ስያሜ ፃዲቁ ዮሐንስ የተባሉት ንጉስ ወደ ስፍራው ከሄዱ በኃላ የመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከአዲስ አበባ በ 767 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የወገዳ ከተማ የስማዳ ወረዳ መዲና ናት፡፡ 40 በመቶ የሚሆነው የወረዳው መልከአ ምድር ወጣ ገባማ ሲሆን ለእይታ ማራኪ ነው 25 በመቶው መልከአ ምደር ሜዳማ ሲሆን አመታዊው አማካኝ የዝናብ መጠን 1000 እስከ 1500 ሲሆን  አማካኝ የሙቀት መጠኑ 23 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ይደርሳል፡፡
እንደ 2001 ዓ/ም ስታስቲክሳዊ መረዳ 239.618 የሚደርሰ ህዝብ የሚኖርበት ስማዳ በርካታ ባህላዊ ታሪካዊ የተፈጥሮ ሰው ሰራሽ መስኸቦችን የታደለች ምድር ናት፡፡
አንፋርጌ ጊዮርጊስ
አንፋርጌ ጊዮርጊስ ሙጃ ሮቢት በሚባለው የስማዳ ገጠር ቀበሌ አቅራቢያ የሚገኝ መስኽብ ነው፡፡ አንፋር የሚለው ዛፍ ስም ለአንፋርጌ ስያሜ መነሻ እንደሆነ አበው ይናገራሉ፡፡
ከወረዳው ርዕስ ከተማ ከወገዳ 80 ከ.ሜትር ርቀት ላይ ቀበሌ 26 በሚባለው ስፍራ የሚገኘው ይህ ደብር በ1335 ዓ.ም በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግስት ዘመን ጭምር የቤተ መቅደስነት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ጥንታዊው የቤተ መቅደስ ፍራሽ ከቀይ ሸክላ ድንጋይ ተጠርቦ የተሰራ እንደነበር ዛሬም ድረስ የቆሙት ፍርስራሾች ማስረጃ ናቸው::
አንፋርጌ በየዘመናቱ ከነበሩ ጥቃቶች የተጠበቀ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት ስፍራ ሲሆን ከ 600 ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠሩ ትውፊቶች ማዕከል ነው፡፡ በአንፍርጌ ጊዮርጊስ ዙሪያ የሚደረጉ ጥናቶች መቀጠል ከቻሉ ተጨማሪ ትኩረት የሚሰጡ ክስተቶች ማዕከል ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
                               ///////                                          

ደብረ እንቁ ማርያም
ከወገዳ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገነው ደብረ እንቁ ማርያም ከተማ 5 ኪ.ሜትር ያክል በአርሶ አደር ማሳ ላይ ከተጓዙ በኃላ በውብ መልከአ ምድር ለአይን ትንግርት በሆነ ስፍራ የሚያገኟት ጥንታዊት ደብር ናት፡፡
ደብረ ዕንቁ ማርያም ቀበሌ 35 በሚባለው የስማዳ ወረዳ ስትገኝ የአረፈችበት ስፍራ በራሱ መስኽብ ነው፡፡ ደብረ እንቁ እና ዙሪያ ገባው መልከአ ምድር በተወሰነ መልኩ ከግሸን ማርያም ጋር የሚመሳሰል ገፅታ ሲኖረው ምናልባትም የደብረ ዕንቁ ማርያም ዙርያ ገባ ተፈጥሮአዊ መልክ የበለጠ ሳቢ የፈጣሪን ጥበብ የሚተርክ የጎብኚን ቀልብ የሚገዛ ስፍራ አድርጎታል፡፡
ከ 485 – 515 ባለው ግዜ በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግስት በአቡነ ፊሊጶስ እንደተተከለች አባቶች ይናገራሉ፡፡