Tuesday, May 19, 2015



የምሁር አክሊል ወረዳ
ፎቶ፡-በገዝ ወንዝ
በጉራጌ ዞን ከሚገኙት ወረዳዎች አንዱ ሲሆን በ30 ቀበሌዎች እና በ1 የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ነው፡፡ ወረዳው በሰሜን ከኪር ገደባኖ ወረዳ፣ በምስራቅ መስቃን ወረዳ፣ በደቡብ እዣወረዳ እና በምዕራብ ቀቤና ወረዳዎች ያዋስኑታል፡፡ የወረዳው የህዝብ ብዛት 107.224 እንደደረሰ ከሥነ ህዝብ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ማህበረሰቡ በአብዛኛው የሚተዳደረው  በእንስሳት እርባታና በእርሻ ነው፡፡



የወረዳው ዋና ከተማ ሀዋርያት ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በከተማው ከሚገኘው የሀዋርያት ቤተክርስትያን እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ከተማው ከአዲስ አበባ በ207 ኪ.ሜ ከዞኑ ርእሰ ከተማ ከወልቂጤ ደግሞ በ52 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በ38.29 እና በ38.88 ምስራቅ ሎንግቲውድ  በ8.12 እስከ 8.33 ሠሜን ላቲቲዩድ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ከ1720 እስከ 3346 ሚ.ሊ ሲያገኘ በወይና ደጋ፣ ደጋና  በውርጭ የአየር ንብረት የተከፋፈለ ነው፡፡
ወረዳው በፊት እዣና ወለኔ ተብሎ ይተዳደር ነበር ሆኖም ከ1993 ዓ.ም እንደ አንድ ወረዳ ሆኖ ምሁርና አክሊል ተብሎ ሊሰየም ችሏል፡፡ ምሁር የሚለውን ስያሜ ያገኘው 1ኛ አቡነ ዜና ማርቆስ ህብረተሰቡን የክርስትና ሀይማኖት ለማሰተማር በሚመጡበት ወቅት የምሁር ህዝብ ያለምንም ተቃውሞ አስተምህሮአቸውን ስለተቀበለ ምሁር (የተማረ) ብለው እንደሰየሙት ሲነገር በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት ፖስታ ቤት ባልነበረበት ዘመን ደብዳቤ ለማፃፍም ሆነ ለማስነበብ  ምሁራን ወዳሉበት ወደ ምሁር እየሱስ ቤተክርስቲያን በመሄድ ደብዳቤ ያፅፉም፣ ያስነብቡም፣ ይለዋወጡም ስለነበር ምሁር (ምሁራን ጋ) እንሂድ በማለት የምሁራን ሀገር ነው ሲሁ ስያሜው ከዛ እንደተወሰደም ይነገራል፡፡
ወረዳው የተለያዩ ታሪካዊ ተፈጥሮአዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የመገራን ፏፏቴ፣ ዘቢዳር ተራራ፣ የግማር ወራ ፏፏቴ፣ በገዝ ወንዝ፣ የከሬብ ደን፣ የደነዛ ደን፣ የጎራንዳ ዋሻ፣ የከሬብ ዋሻ፣ የሀሰን ኢንጃሞ መቃብር፣ እምየ ጠቆንቦ (የመቃብር ስፍራ)፣ የትኩመር የብረት ጉድጓድ፣ ጀፎሮ፣ ጥንታዊው የምሁር እየሱስ ገዳም፣ ሽራር ቂርቆስ፣ ማጌ ጊዮርጊስ፣ መገራን ዜና ማርቆስ ቤተክርስቲያን፣ በገሽ አማኑኤል እና በውስጡ የሚገኙ የተለያዩ ቅርፆች፣ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዘርአያይቆብ የተተከሉ ስድስት አብያተ ክርስትያናት፣  ደንገዝ እየሱስ ቤተክርስቲያን የድንጋይ መንበርና ከበሮ፣  የድንጋይ ደወል፣ የግራኘ መሀመድ ትክል ድንጋዮች ተጠቃሾች ናቸው፤ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
ተፈጥሮአዊ መስህቦች
ደነዛ የተፈጥሮ ደን
ይህ ደን የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የተፈጥሮ ዛፎች የያዘ እና ሰፊ የሆነ የቆዳ ስፋት ያለው ነው፤ በግምት ከ20 -30 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ቦታ ላይ ሰፍሯል፤ ደነዛ ወንዝ የሚያካልላቸው ቀበሌዎች መነሻው አበጅ ቀበሌ ሲሆን ከሬብ ወንዝን ተከትሎ አቸና ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ልዩ ስሙ ዋዥራ ከተባለው መንደር ይደርሳል፡፡ ስፍራው ለተለያዩ እይታዎች ምቹ ከመሆኑ የተነሳም ተክለሀይማኖት ቀበሌ ጨመኘ ላይ በመሆን ከወንዙ ማዶ ሲመለከቱ የአበጀ እና መገራን ቀበሌዎች መልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸው ሰንሰለታማና ተራራማ የሆኑ ውብ ገፅታን በመመልከት ይደመማሉ፡፡ በውስጡም የተፈጥሮ ስጦታ በሆኑት ፅዋትና አእዋፋት፣  የዱር እንስሳት፣ የጅብ መኖሪያ ጉድገዋዶች፣ በኢትዮጵያ ዝርያው ጠፍቷል የሚባልለት ነብር … ሌሎችም ትሩፋቶች በቦታው ይገኛሉ፡፡ ቦታው በፊት ዘመን ከጠላት ጦር መሸሸጊያነት እንዳገለገለም ይነገራል፤ በአጠቃላይ ዓይምሮን ለማደስ የተፈጥሮን ለጋስነት ለመመስከርና የተለያዩ ጥናቶችን ለማድረግ በሚያግዘው ስፍራ መገኘት መታደልም ነው፡፡
የግማር ወራ ፏፏቴ

                 ፎቶ፡-የግማር ወራ ፏፏቴ
የግማር ወራ ፏፏቴ በኤቸና ቀበሌ እና በጨዛ ቀበሌ ድንበር በበገዝ ወንዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከወረዳው ዋና ከተማ ሐዋርያት 13 ኪ.ሜ እና ከዋናው ከመኪናው መንገድ በስተደቡብ 2 ኪ.ሜ ገባ ብሎ በያንዳሆ እና ወረነ ጎጥ ውስጥ ይገኛል፡፡ ፏፏቴው ርዝመቱ ከ15-20 ሜትር ይደርሳል፤ በአካባቢው የተለያዩ እንስሳትና አዕዋፋት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ጅብ፣ ጦጣ፣ ቀበሮ፣ ጉሬዛ፣ ሚዳቆ፣ ነጭ በጥቁር ቀለም ያላት ቁራ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ወደ መስህቡ ለመሄድ  ከሀዋርያት ከተማ በስተምስራቅ በኩል የሚገባ ሲሆን በመንገዱ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ መስህቦች እየተቃኘ መሆኑ ጉዞውን መሳጭ ያደርገዋል፡፡ መኪና እስከሚገባበት ድረስ በአፄ ሚኒሊክ ግዜ እንደተገነባ የሚነገርለ ጨዛ ደፈር የገጠር ከተማ፣ እንዲሁም በወረዳው ከሚገኙት ጎሳዎች ውስጥ ብዙ አባላት እንዳለው የሚነገርለት  የውድም አጠረ ጎሳ እናት የመቃብር ስፍራ፣ በአፄ ዘርአያቆብ ግዜ የተገነባው የጓባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያንን እየቃኙ የኤቸነ ቀበሌ ፅ/ቤት ወደ ሆነችው የቃ መሰራ (የሰረ) ይደርሳሉ፡፡ ከመኪና እንደወረዱም ዓይንን ሲያሻግሩ የበሬ ሻኛ ቅርፅ ይዞ የሚታየውን የቤጬ የሰርጌ መሬት፤ እድሜ ጠገብ ዛፎች፣ ባህላዊ ዳኝነት ይካሄድበት የነበረ የግራረት ጀፈሮን እና የለቅሶ ስርዓት የሚካሄድበትን ስፍራ በተጨማሪም የአካባቢው ምግብ የሆነው በየሳር ቤቱ ጀርባ አረንጓዴ ልብስ የለበሱ ሰራዊት መስለው ለአካባቢው ግርማ ሞገስ የሰጡትን የእንሰት ተክል እየቃኙ ሳያስቡት ፏፏቴው ጋ መድረስ ይቻላል፡፡
የመገራን ፏፏቴዎች
መገራን በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌዎች አንዱ ሲሆን ከሀዋርያት ከተማ በ32 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል ይህ ቀበሌ በፏፏቴ ቀጠናነት ይታወቃል፡፡ ፏፏቴዎቹም አራት ሲሆኑ የመገራን ፏፏቴዎች በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የ2 ዋሻና የአንድ ቤተክርስቲያን እንዲሁም ንፁህ አየርን በሚለግሱ ደኖች የተዋበና የታደለ ቀበሌ ነው፡፡ በመገራን ቀበሌ ወደ ቁርቁር ጎጥ በመሄድ የቁርቁር ሰፈር ጎጆ ቤቶች መካከል ባለው መንገድ ወደ ምዕራቡ ለመጓዝ ወደ አጊረ ወንዝ መውረጃ ቁልቁለት ወረድ ሲሉ እጅ ወደላይ የሚያስብሉ ሁለት ፏፏቴዎች ያገኛሉ፤ እነሱም የጉምራት ፏፏቴ በመባል ይታወቃል፡፡ የአንደኛው ፏፏቴ ቁመት ከአናት እስከ መሀል 30 ሜትር ሲሆን ከታች ተቀብሎ ሌላ ፏፏቴ በመፍጠር ከመሀል ተነስቶ የሚወርደው እስከ ውሀው ማረፊያ 15 ሜትር ይሆናል የሰውን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት ቅብብሎሽ፣ በፏፏቴዎቹ ድምፅና ውበት ተማርኮ ላልቀረ እና የመንቀሳቀስ አቅም ላለው በስተደቡብ ደግሞ  የውነት የተባለውን በግምት ከ45 እስከ 50 ሜትር ርዝመት ያለውን ሌላ ፏፏቴ ይገኛሉ፡፡ በተፈጥሮ ውበት ስካር እየተንገዳገዱ ሸለቆውን ተከትለው እልፍ ካሉም ቁልቁለቱን እንደወረዱ የግረ ወንዝን ሻገር ብለው ወንዙ ዳርዳር ሜዳውን ተከትለው በተፈጥሮ ተቦርቡሮ በተሰነጣጠቀው ቀጭን ዋሻ መሰል መንገድ በጥንቃቄ መጓዝ ከቻሉ 56 ሜትር ርዝመት ያለው አጫበቃ ፏፏቴ አቀባበል ያደርግሎታል፤ አካባቢው የከሬብ ወንዝ ማለፊያ ነው፡፡  ከወንዙ ዓይንን መንቀል ከተቻለ የዱር እንስሳት መኖሪያ በሆነው በደነዛ ደን እየተመሰጡ በአእዋፋት ዝማሬ ታጅበው  መመለስ ይችላሉ፡፡

ከሬብ ወንዝ
ከሬብ ወንዝ በምሁር አክሊል ወረዳ ከሚገኙ ወንዞች አንዱና ትልቁ ሲሆን አጠቃላይ የወረዳውን ተፋፈስ ከ64 እስከ 70 ፐርሰንት የሚሸፍን ነው፡፡ ከአበጅ ቀበሌ የሚነሳው የከሬብ ወንዝ ለዋቤ ወንዝ ከሚገብሩት ወንዞች ብዙውን ውሀ የሚያደርስ ነው፡፡
የበገዝ ወንዝ
በወረዳው ከሚገኙት ወንዞች በትልቅነቱ ከከሬብ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ወንዝ ሲሆን መነሻው ከችምቢ፣ ከፋርቻ፣ ከተክለሃይማኖት፣ ቀበሌዎች ውስጥ ከሚገኙ ትናንሽ ምንጮች ሲሆን እነዚህን ቀበሌዎች አቋርጦ የኮተ ቀበሌ ሲደርስ በትናንሽ ዛፎች እየታጀበ ኤቸነ እና ጨዛ ቀበሌ ይደርሳል፡፡ በነዚህ ቀበሌዎች መካከል የግማር ወራ ፏፏቴ የሚባል ማራኪ ፏፏቴን እየፈጠረ በደኖች በመታጀብ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ በተለይ ምሁር ገዳመ እየሱስ መሻገሪያ ድልድይ ጋር ሲደርስ የሶስት አብያተ ክርስትያናት ማለትም ምሁር ገዳም እየሱስ፣ ገሽ አማኑኤልና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የሀዋርያት  ቤተክርስቲያን ለጥምቀት በዓል ታቦታቱን በወንዙ ዳር በማሳረፍ ለመጠመቂያነት ይገለገሉበታል፡፡ ይህ ወንዝ በቆረር ቀበሌ ሶስት ወንዞች የሚገብሩት ሲሆን በመጨረሻም ከሬብ ወንዝን ይቀላቀላል፡፡
ታሪካዊ መስህቦች
የግራኝ አህመድ ትክል ድንጋዮች
በተለምዶ ግራኝ አህመድ ተብሎ የሚታወቀው የጦር መሪ ሙሉ ስሙ አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ ሲሆን የኖረውም ከ1508 እስከ ታህሳስ 21 ቀን 1453 ዓ.ም እ.ኤ.አ ነበር፡፡ በዘመኑ በእስልምና ሃይማኖት የኢማምነት ደረጃ የደረሰ ሲሆን የአዳል ግዛት ተብሎ ይታወቅ የነበረው የጥንቱን የኢትዮጵያ ክፍል በጦርነት በማነሳሳት እና በመምራት እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ ነገስታት በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍል በጦርነት በማነሳሳትና በመምራት እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ ነገስታት በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍል ለተወሰነ ግዜ መቆጣጠር ችሏል፡፡ ብዙ አብያተክርስቲያናትንና የዘመኑ የስልጣኔ ማዕከሎችንም በዚሁ ዘመን እንዳፈረሰ ታሪክ ይዘግባል፡፡
ይህ የጦር መሪ ኢትዮጵያን ከምስራቅ ወደ ሰሜን በተንቀሳቀስባቸው ዓመታት ጉራጌ ዞንን ጭምር እንዳሰሰ እና በተጓዘባቸው ቦታዎች የራሱ የሆነ እዳሪዎችን ጥሎ እንዳለፈ ታሪክ አዋቂ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ወደ ጉራጌ ዞን ሲገባ ከጅማ አንስቶ በቸሀ በኩል መቆርቆርን አቋርጦ ምሁር አክሊል በመምጣት ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ የራሱ ምልክት በማስቀመጥ ወደ ስልጤ ገብቷል፡፡ ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ አሻራዎችና ምልክቶቹ በአሁን ዘመን በጉራጌ ዞን በምሁር አክሊል ወረዳ ቀበሌዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአካባቢው አጠራር (ትክል እማኘ) ይባላል፡፡ የሚገኙባቸው ቀበሌዎች ውስጥ ጨዛ ቀበሌ ልዩ ስማቸው የገረፋ እና የገሬ በኤቸነ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆጠር መንደር እንዲሁም የኮተ ቀበሌ በልዩ ስሙ የዝሆን ፊንጨ(የዝሆንግንባር)በፊት የዝሆን መኖሪያ የነበረ  መንደር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ትክል ድንጋዮች የተለያየ ቅርፅ ያላቸው በመሆናቸው እንደየቦታዎቹ ይለያያሉ፡፡

 የታላቁ የጦር አባት የሐሰን እንጃሞ መካነ መቃብር
መካነ መቃብሩ የሚገኘው በምሁርና አክሊል ወረዳ ሴባ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ከዞኑ ርእሰ ከተማ ወልቂጤ 64 ኪ.ሜ ከወረዳው ርዕሰ ከተማ ሐዋርያት 12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሐሰን እንጃሞ ሀላባ አካባቢ ተወልደው ግዛታቸውን ለማስፋፋት ወደ ጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ በመሄድ እንዳረፉና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ስምምነት ባለመፍጠራቸው አዋቂ በመጠየቅ ሴባ የሚባል ቅጠል (ዛፍ) ያለበት ቦታ ሄደው ቢያርፉ እንደሚቀናቸው ይነገራቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ምሁር አክሊል ሄደው አሁን ያረፉበት ቦታ እንደኖሩና የቀበሌው ስያሜም ከዚያ ተክል እንዳገኘ ይነገራል፡፡ 
እዚሁ ወረዳ ውስጥ ሐሰን እንጃሞ የሚኒሊክን ግዛት ማስፋፋት በመቃወምና በአካባቢው የእስልምና ሀይማኖት በማስፋፋት ብዙ ጦርነቶች አድርጓል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች አስተምህሮቻቸውን ተቀብለው እስልምናን ሲቀበሉ የምሁሩ አበጋዝ ሸበታ ግን እኔ ቅርብህ ነኝ ሌሎቹን ካሳመንክ  በእኔ በኩል ያሉትን ችግር የለም ብለው ከዘየዷቸው በኋላ ከአፄ ሚኒሊክ ዘንድ በመሄድ ሃይማኖቴን የሚቀይር የእምነት ቦታዎቼን የሚያቃጥል ንጉስ ተነስቶብኛልና እንድትረዱኝ ብለው ጠየቁዋቸው፡፡ ከዚያም እሳቸውም ራስ ጎበናን በመስጠት የሐሰን እንጃሞ ጦርና የአበጋዝ ሸበታ ጦር በአሁኑ ወቅት ኤቸና ቀበሌ በሚገኘው በገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ እና መገራን ቀበሌ ዞያን ወንዝ አካባቢ ጦርነት ተጀመረ፡፡ በሁለቱም ወገን ብዙ ህዝብ አለቀ ፈቀቅ ብሎ ወደ ብሽእጋ ኦሮምያ ክልል በሚገኘው ወንዝ አካባቢም የራስ ጎበና ጦር እና የሐሰን እንጃሞ ጦር ተገናኝተው የራስ ጎበና ጦር በወቅቱ የዘመነ ጦር ስለነበር የሐሰን እንጃሞ ጦር ተሸንፎ ወደ እንጌ ሚባል ቦታ ሸሸ፤ ከዚያም እኚህ የጦር አርበኛ ወደ ጅማ ሸሽተው በመሄድ ከጅማው አባጅፋር ጋር በመገናኘት የጦር ሀይል እርዳታን ጠይቀው እንደነበርና የጅማው አባጅፋር የሚኒሊክ ወዳጅ ስለነበሩ የጦር ሀይል እንደማይሰጧቸውና አብረዋቸው ከሄዱት ሰው ጋር ግዛት ተሰጥቶአቸው እንደሚኖሩ ሲነገራቸው የሚፈልጉት ቀርተው ሌሎቹ ግን ከእሳቸው ጋር አብረው ሲመጡ መንገድ ላይ በወባ በሽታ ህይወታቸው በማለፉ ሴባ ቀበሌ ተቀብረዋል፡፡ የመቃብር ስፍራቸው  ለጎብኝዎች ክፍት ነው፡፡
የሀረግ ድልድይ
የሀረግ ድልድዩ የከሬብ ወንዝ ላይ የተሰራ ሆኖ ወደ መቆርቆርና ሆረር ቀበሌ የሚያሸጋግር ነው፡፡ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መንገድ ባልነበረበት ሰዓት የተሰራው ይህ ድልድይ ርዝመቱ 10 ሜትር አካባቢ  ስፋቱ ደግሞ 1 ሜትር ከ50 ይሆናል፡፡ በአንድ ግዜ ከ5 እስከ 10 ሰዎችን የማሻገር አቅም አለው፡፡ በአሁን ሰዓት በየዓመቱ ሁለቱ ቀበሌዎች ተራ በተራ እደሳ ያደርጉለታል፡፡
የኔጌጃን ባህላዊ ድልድይ
አጣጥ ቀበሌ መውጫ ላይ የሚገኘው ይህ ድልድይ በታሪክ እንደሚነገረው አባቶች ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ውሀ ይሞላና መሻገር አቅቷቸው ሊመለሱ የዶቅማ እንጨት እንደድልይ ሆኑ በመዘርጋቱ ተሻግረዋል፡፡ ድልድዩን (እንጨቱን) የዘረጋው ራሱ ገብርኤል ነው ተብሎም ይታመናል፡፡ ይህን ድልድይ ተከትሎ ዳገቱን ለመውጣት የአካባቢው ሰው ከተለያዩ እንጨቶች የተሰራ መሰላል በማዘጋጀት እስከአሁን ድረስ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
መንፈሳዊ መስህቦች
ገሽ አማኑኤል ቤተክርስቲያን እና የድንጋይ ደወል
ከዞኑ በ55 ኪ.ሜ ከወረዳው ርዕሰ ከተማ ሀዋርያት በ3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ጥንታዊው የገሽ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ከ840 ዓ.ም በፊት አባቶች ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ  የሚገኙት ዛፎችና የቤተክርስቲያኑ የውስጥ ቁሳቁሶች እድሜ ጠገብነቱን  ይመሰክራሉ፡፡ ከነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች መካከል የድንጋይ ደወል አንዱነው፡፡ ይህ ደወል ዘመን ባልተራቀቀበት ብዙ ቴክኖሎጅዎች ባልተስፋፉበት ዘመን የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ለቤተ- ክርስቲያን መገልገያነት እንዲሆን ብለው የድንጋይ ደወል ሰርተው ለመገልገያነት አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥንታዊ ድንጋይ በአካባቢው ካሉት ድንጋዮች ምንም ዓይነት መመሳሰል የሌለው ሲሆን ላየውና ላዳመጠው ድንጋይ ድምፅ ያወጣል እንዴ የሚል ግርምታን ይፈጥራል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው እድሜ ጠገብ አባቶች ሲናገሩ ድንጋዩ ቤተክርስቲያኑ ሲመሰረት አባቶች ከየት እንዳመጡት አይታወቅም ይላሉ፡፡ ከአካባቢው ድንጋዮች ምንም ምስስሎሽ የሌለው ይህ ድንጋይ የአካባቢው ተወላጅ አዛውንቶች ሲናገሩ ብዙ በመልክ የሚቀራረቡ ድንጋዮችን ከወንዝ ፈልጠን በማምጣትን በድንጋይ ስንመታው አይጮህም የዚህ ጥንታዊ የድንጋይ ደወል ድምፅ ግን ያስገርማል በማለት ይናገራሉ፡፡ ጥንታዊና ተፈጥሮአዊ የድንጋይ ደወሎቹ ሁለት ሲሆኑ መልካቸው ግራጫ ሆኖ የራሳቸው የድንጋይ መምቻም አላቸው፡፡ በአንድ እጅ መምቻውን በመያዝ አባቶች ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ለመጀመርም ሆነ ቤተክርስቲያን ችግር ሲያጋጥማት በፅድ ጉቶ ላይ በክብር የተቀመጡትን የድንጋይ ደወሎች ይመቱ ነበር፡፡ በአሁን ሰዓት የብረት ደወል በመቀየሩ ከጥንታዊነቱና ታሪካዊነቱ በዘለለ አገልግሎት እየሰጠ ዓይደለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ ቤተክርስቲያን ውጪ በሁለት ቤተክርስቲያን የዚህ ጥንታዊ ድንጋይ ዓይነት የድንጋይ ደወል ይገኛል፡፡
ምሁር እየሱስ ገዳም
በወረዳው ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ሀይማኖታዊ፣ ታሪካዊና  ባህላዊ ቅርሶች አንዱ ሲሆን ወደ ገዳሙ የሚያስገባው መንገድ ከከተማው በ3ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲገኝ በ8ኛው ክ/ዘመን ወይም በ840 የተሰራ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊው ፃድቅ በአቡነ ዜና ማርቆስ በ1340 ዓ.ም ገዳም ተብሎ በገዳምነት ተሰይሟል፡፡ ፃድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ 40 ዓመት የፆሙበት ዋሻ እና በፈዋሽነቱ የሚታወቀው ፀበላቸውም በዚህ አካባቢ ይገኛል፡፡ ገዳሙ በዚያን ግዜ የነበሩትን ቅርሶችም ይዟል ፡፡
 በገዳሙ ስር የተለያዩ አገልግሎቶች ሲኖሩ
ለምሳሌ፡- የሙዚየም አገልግሎት
          የአብነት ትምህርት ቤት
          1ኛ ደረጃ ት/ቤት
          የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል 
          የእደጥበብ ውጤቶች ማምረቻና መሸጫ ይገኛል፡፡
የምሁር እየሱስ ገዳም ሙዚየም
ፎቶ፡-ምሁር እየሱስ ገዳም
ፎቶ፡-ምሁር እየሱስ ገዳም ሙዚየም
ሙዚየሙ የገዳሙ የበላይ ጠባቂ በነበሩት በአቡነ መልከ ፀዲቅ ከአካባቢው ማህበረሰብ ባሰባሰቧቸው ቅርሶች ነው የተመሰረተው፡፡ ከዛም በኋላ በተደራጀ መልኩ በ1997 ዓ.ም ተመርቆ ስራውን ጀምሯል፡፡ ሙዚየሙ በውስጡ ጥንታዊ ቅርሶችን የያዘ ሲሆን ከነዚህም፡- የአቡነ መልከፀዲቅ በህይወት እያሉ የሚገለገሉባቸው አልባሳት፣ ይይዙት የነበረ በትረ ሙሴ፣ አክሴማዎች፣ መስቀሎች እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተበረከቱላቸው ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም ከግብፅ ሀገር የተበረከተላቸው ማህደር በወርቅ የተለበጠ ተአምረ ማርያምና መዝሙረ ዳዊት፣ ከእንግሊዝ ሀገር የተሸለሙት የብር ፅዋ፣ የወርቅ ቅብ ወንጌሎች፣ እንዲሁም ከግሪክ ሀገር የተበረከተላቸው እና በቤተክርስቲያን ትልቅ ሚስጥር ያለው የሰጎን እንቁላል ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ግብፅ ሀገር ይኖሩ የነበሩት ወንድማቸው አባ ፈቃደ እየሱስ በሳቸውና በራሳቸው ስም አሰርተው ያበረከቱት ዘውድ (አክሊለ በረከት )፣ ከአፄ ሚኒሊክ የተበረከቱ የተለያዩ የብራና መፅሀፍት፣ የቤተክርስቲያኒቷ ይዞታ ከሆነውና ሀላባ ከሚገኘው መሬት ላይ የሚመረተውን እህል አጅበው የሚመጡበት የጦር መሳሪያ፣ ከባልቻ አባነፍሶ የተበረከቱ የነሀስና የብር መስቀል፣ እንቢልታ፣ እንዲሁም ከፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የተሰጡ ልዩ ልዩ መፅሀፍት በቤተክርስቲያኑ ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም የአፄ ሀይለስላሴ እና የእቴጌ መነን ደብዳቤዎችና መባዎች፣ ከራስ ደስታ ዳምጠው የተበረከተ የመፆር መስቀል፣ ከአፄ ዘርአያቆብ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ቅርሶች፣ የባልቻ አባነፍሶ ሁለት ፎቶዎች፣ እዛ ብቻ የሚገኝ ግዕዝን በግዕዝ የሚተረጉም (የሚያብራራ) የብራና መፅሀፍ እና……. ሌሎችም ቅርሶች ይገኛሉ፡፡


የአብነት ትምህርት ቤት
ትምህርት ቤቱ 72 ተማሪዎች ሲኖሩት 7 የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች (ቤቶች) አሉት፡፡ እነዚህም የንባብ ቤት፣ የቅዳሴ ቤት፣ ፆመ ድጓ (ዜማ ቤት)፣ መፅሀፍት ትርጓሜ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤትና  ቤተ በገና (ቤተ እንዚራ) ቤት ይባላሉ፡፡ በያንዳንዳቸውም ቤት አስር አስር ተማሪዎች ይስተናገዱበታል፡፡
የወረዳው የኢንቨስትመንት አማራጮች
በወረዳው በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ይገኛሉ፡፡ በተለይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው  አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ትኩረት በመስጠት በሎጅ ግንባታ ቢሰማሩ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ በፍራፍሬ ምርት በማንጎ በተለይ ጥራት ያለው የፖም ምርት ማምረት የሚቻልበት 11 የደጋ ቀበሌያት መኖራቸው፣ ለእንስሳት እርባታ በወረዳው በቂ መኖ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ምቹ ሁኔታ መኖሩ፣ ለዘመናዊ የንብ እርባታ፣ ለበቆሎና ማሽላ ሰብሎች አመቺ ነገሮች መፈጠራቸው ኢንቨስተሮች ወደወረዳው በመሄድ ኢንቨስት ማድረግ ቢችሉ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡



No comments:

Post a Comment