Friday, April 24, 2015



ምዕራብ አርሲ ዞን
አብያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ
የምዕራብ አርሲ ዞን ከአዲስ አበባ በ250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ነው፡፡ 12409.99 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ይህ ዞን በሰሜን ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ በደቡብ ጉጂ ዞን፣ በምዕራብ የደቡብ ብሔረሰብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና በምስራቅ ባሌ ዞን ያዋስኑታል፡፡ አብዛኞቹ የዞኑ አካባቢዎች አማካኝ ከባህር ጠለል (ወለል) በላይ ከ1500 እስከ 3800 ሜትር ከፍታ አላቸው፤ የዞኑ ዋና ከተማ ሻሸመኔ ነው፡፡ ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት የዞኑ የህዝብ ቁጠር ከ2 ሚሊየን በላይ እንዲሚሆን ይገመታል፡፡


የበርካታ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት የሆነው የምዕራብ አርሲ ዞን ለአዲስ አበባ አቅራቢያ ለሆኑ በርካታ የክልል ከተሞች አመቺ የሆነ ርቀት ላይ የሚገኝና የሀገራችን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ቀጠና ነው፡፡ በመዝናኛ ቱሪዝም የገነኑት ላንጋኖ ሀይቅ፣ አብጃታ ሀይቅ፣ ሻላ ሀይቅ፣ ሀዋሳ ሀይቅ፣ አብጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ፣ አዳባ ዶዶላ ደን፣ ሄቦ ፏፏቴ፣ የሰንቂሌ መጠለያ ፓርክ፣ የተለያዩ ፏፏቴዎች፣ ወንዞች እና ሌሎችንም መስህቦች በምዕራብ አርሲ ዞን ከሚገኙ መስህቦች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
አብጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ
ከአዲስ አበባ በ210 ኪ.ሜ ያህል ርቀት ላይ ከላንጋኖ ደግሞ በስተቀኝ 5 ኪ.ሜ ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ በብዝሀ ህይወት ስብጥሩ እና በስፋቱ የበለጸገ የቱሪዝም መስህብ የሆነው ይህ ፓርክ በርካታ የውሀ ላይ አእዋፍ የሚታዩበት፤ በተለይ በክረምት ወቅት ወደ 50,000 የሚጠጉ የፍላሚንጎዎች ተከማችተው ለዓይን በሚስብ መልኩ የሚታዩበት ነው፡፡ ወፎችን ለሚያደንቁ ጎብኝዎች ተመራጭ ስፍራ የሆነው ይህ ፓርክ በአፍሪካም ግንባር ቀደም እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ 887 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው፡፡ ይህ ፓርክ ከባህር ጠለል በላይ ከ1540-2007 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ በብዛት እንደዣንጥላ የሚዘረጉ የግራር ዛፎች ይገኙበታል፡፡ የአብያታና ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ልዩ ልዩ አጥቢ የዱር እንስሳት የአእዋፍ እና የእፅዋት ዝርያዎችን ይዟል፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሜዳ ፍየልን፣ ብሆርን፣ ከርከሮና አጋዘን የመሳሰሉት የዱር እንስሳትን በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ አብያታ ሻላ እና ጩቱ ሀይቆች የብሔራዊ ፓርኩ ግርማ ሞገስ ናቸው፡፡ በፓርኩ ከሚገኙ አእዋፋት ውስጥ ሰጎን አንዱ ነው፡፡
የሰንቀሌ መጠለያ
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ በ310 ኪ.ሜ ገደማ ከሻሸመኔ በ35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የሰንቀሌ መጠለያ በ1974 ዓ.ም በ200 ስኩየር ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የተቋቋመ ይሁን እንጂ በተለያዩ ግዜያት በተከሰቱ ሠው ሰራሽ ጫናዎች ምክንያት በአሁኑ ወቅት የመጠለያው ስፋት 54 ስኩየር ኪ.ሜ ብቻ ነው፡፡ መጠለያው የተቋቋመበት ዓላማ የሀገራችን ብቸኛ ሀብት የሆነው የስዌን ቆርኪን ለመታደግ ነው፡፡ መጠለያው ከባህር ጠለል በላይ ከ2007 እስከ 2224 ሜትር ከፍታ አለው፤ የአየር ፀባዩም ወይና ደጋ ሲሆን አማካይ የሙቀት መጠኑ ዝቅተኛው 9 ከፍተኛው ደግሞ 28 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል፡፡ የመጠለያው መታወቂያ የሆነው የስዌን ቆርኪ ከሌሎች ሀገራት የሚለየው በቀለሙ ነው፡፡ ቀለሙ ቸኮሌታማ ቡኒ ሆኖ ወደታፋውና ከኋላው አካባቢ ነጣ ያለ ቀለም አለው፤ ቆዳውም ቀላ ያለና አብረቅራቂ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመጠለያው ውስጥ 191 የአእዋፍ ዝርያዎችና 20 የተለያዩ አጥቢ የዱር እንስሳት ይገኛሉ፡፡
ሻላ ሀይቅ
                              ሻላ ሐይቅ /lake Shalla/
ሀይቁ 266 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው በውሀ ክምችቱ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሀይቆች ትልቁ ነው፡፡ 37 ሚሊየን ኪዩብ በላይ ጥልቀት 27 ኪ.ሜ ርዝመትና 16 ኪ.ሜ ስፋት ሲኖረው በአጠቃላይ 314 ሰኩየር ኪ.ሜ የቆዳ ስፋት አለው፡፡ 


ጪቱ ሀይቅ
ከሻሸመኔ 37 ኪ.ሜ በስተቀኝ ሲጓዙ ከአብያታ ሻላ ሀይቅ ተቆርጦ 1 ኪ.ሜ በማይሞላ ስፍራ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሀይቅ የሚታወቀው በተራሮች ተከቦ ትሪ በመሰለ ቅርፅ በጥቁር ሰማያዊ የሀይቁ መልክ ላይ ኢትዮጵያ የአእዋፍ መናህሪያ መሆኗን ይመለከቱበታል፡፡ ይህን ስፍራ አንዳንዶች የአፍሪካ የአእዋፍ ገነት ብለው ይጠሩታል፡፡ ከአውሮፓ ተነስተው በሜዲትራንያን ባህር ላይ ሰንጥቀው ወደ አፍሪካ ሰማያዊ ጣርያ ስር ከሚገኘው ደን ልምላሜ እንዲሁም የተፈጥሮ አካባቢ ክረምት ከበጋ ለምለም የሆነ የሚሰፍሩበት ስፍራ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
ጌምቤላ ዋሻ
ይህ ዋሻ በሻሸመኔ ወረዳ በአዋሾ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲገኝ ከሻሸመኔ ወደ ባሌ በሚወስደው መንገድ ዳር ላይ የሚገኝና በጣሊያን ጦርነት ግዜ ከብቶቻቸውን በመያዝ እስከ 3000 የሚደርሱ ሰዎች ይሸሸጉበት እንደነበር ይነገራል፡፡
የአዳባ ዶዶላ ከተሞች
ይህ ስፍራ ከአዲስ አበባ በ312 ኪ.ሜ ከዞኑ ዋና ከተማ ከሻሸመኔ ደግሞ በ71 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ አዳባ እና ዶዶላ ከባህር ጠለል በላይ ዝቅተኛ 2400 ሜትር ከፍተኛ ደግሞ 3700 ሜትር የሚጠጉ ስፍራዎችን ይዘዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች በተለይ ተፈጥሮን ለሚያደንቁና (አድቬንቸር ቱሪዝም) የሚባለውን ፈልገው ለሚመጡ ጎብኝዎች ተመራጭ ነው፡፡ በእግርም ሆነ በፈረስ በመረጡት እየተጓዙ ተፈጥሮን ማድነቅ ይችላሉ፡፡ ይህ ቦታ በበጋ በተለይም ከጥቅምት እስከ ግንቦት ያሉት ወራቶች ተመራጭ ነው፡፡ ማራኪውን የአዳባ ዶዶላ የተፈጥሮ መስህብ ለመጎብኘት ሲያስቡ ባርኔጣ የፀሀይ መከላከያ ሞቅ ያሉ አልባሳትን፣ ለጉዞ የሚሆኑ ጫማዎችን እና የዝናብ ልብሶችን ቢይዙ ይመረጣል፡፡ በአካባቢው የሚኒሊክ ድኩላ፣ ደጋ አጋዘን፣ የኢትዮጵያ ተኩላ እና ሌሎች የዱር እንስሳት፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የአእዋፍ ዝርያዎችም ይገኛሉ፡፡

የደነባ ሠው ሠራሽ ዋሻ እና መናፈሻ ስፍራ

ደነባ ዋሻ /Deneba Cave/
ይህ ሠው ሰራሽ ዋሻ እና መናፈሻ በሻሸመኔ ወረዳ ከከተማው በ4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፤ ስያሜውን ያገኘው ከአካባቢው መጠሪያ ሲሆን ከ1 ሄክታር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ይህን ዋሻ በራእይ ታይቷቸው ጥር 20 ቀን 1971 ዓ.ም ቁፋሮውን እንደጀመሩት የሚናገሩት አቶ ቀይሶ መሀም ዋሻውን ለመቆፈር 36 ዓመት እንደፈጀባቸው ይገልጻሉ፡፡ በአሁን ሰዓት 80 በመቶ ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ስራ ብቻ ይቀረዋል፡፡ በውስጡ በርካታ የተለያዩ አገልግሎት የሚሠጡ ክፍሎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ውሀ ማቆሪያ ሰው ሰራሽ (ኩሬ)፣ ለጫጉላ ቤት፣ የሙሽሮች መቀመጫ፣ ለካፍቴሪያ፣ ለቢሮ፣ ነጠላ እና ጥንድ የመኝታ ክፍሎች፣ የዶክመንት ማስቀመጫ በዋሻ ተፈልፍለው የተሰሩ ክፍሎች፣ ችሎት፣ የባለ ጉዳይ ማስቀመጫ፣ ሞተር ሳይክል ማስቀመጫ፣ ቡና ማፍያና እንግዶች መቀመጫ … ሌሎችም በርካታ አገልግሎት የሚሰጡ ብዛት ያላቸው ክፍሎች በሚያስገርም እና በዘመናዊ ፕላን የተቀረፀ ሲሆን ያለምንም ትምህርት የተሰራ አስገራሚ ሰው ሰራሽ ዋሻ ነው፡፡ ግቢው በተለያዩ የአበባ ዝርያዎች የተዋበ ሲሆን የምግብና መጠጥ አገልግሎቱ ቢጠናከር ለእንግዶች ምቹ ማረፊያ ነው፡፡
የሽምግልና  ሂደት
አቴቴ
አቴቴ በኦሮሞ ብሔር ከገዳ ስርዓት ቀጥሎ በማንኛውም ማህበራዊ ሁኔታ፣ ሠላምን፣ የሴቶች መብትንና ሌሎችንም ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ጉልህ ድርሻ ያለው የሴቶች ሚና ነው፡፡ አቴቴ ማለት እናትነት ሲሆን (የእናት አምላክ)  በእናትነት የሚገለፅ የሚለምኑበትና የሚያመልኩበት ስርዓት ነው፡፡ የመጀመሪያዋ የኦሮሞ ሴት እንዲሁም ሁሉም ያገቡ የኦሮሞ ሴቶች አቴቴ በመባል ይታወቃሉ፡፡
አቴቴ ሶስት ስርዓቶችን ነው የሚያከናውነው እርሱም
1.     እናትነት
2.    የሴቶች ማስከበሪያ ሀይል ነው
3.    እርቅ ሰላምን ለማውረድ ልዩ አቅም አለው፡፡ እናት ከፈጣሪ ቀጥሎ ትልቅ ቦታ ያላት ናት፡፡ የመጀመሪያዋ የኦሮሞ እናትም አቴቴ ትባላለች፤ ወዮ እጅግ የተከበረ ማለት ነው፡፡ የሴቶች ወዮ አራት ሲሆኑ እነሱም እናት ወዮ ናት፣ ወላድ ሴት ወዮ ናት፣ አማት ወዮ ናት፣ ሚዜ ወዮ ናት፤ በገዳ ስርዓት ውስጥ ካሉት 7 ወዮዎች አራቱ የሴቶች ናቸው፡፡
የአቴቴ ልዩ ምልክቱ ሲንቄ ነው፡፡ በሲንቄ የሚከናወኑ 3 ጉዳዮች
1ኛ. ፀሎት፡- እናቶች ሩህሩህና ሆደ ሰፊ፣ በወሊድ ግዜም ተጨንቀው አምጠው ሰው ያስገኙ በመሆናቸው ፀሎታቸው ይሰማል ተብሎ ይታመናል፡፡ እናቶች አንድ ችግር ሲፈጠር፣ በድርቅ ሰዓት፣ መልካም አስተዳደር ሳይኖር ሲቀር፣ ተፈጥሮአዊ አደጋ ሲከሰት ሲንቄያቸውን ይዘው ወጠው በአንድ ላይ ይፀልያሉ፡፡ ስብስቡ (ቡድኑ) ስምንት (ሰደታ) መሪ አለው፡፡ ሰዴታ ሴቶችን የሚመራ ኮሚቴ ነው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ከሁሉም ጎሳ የተውጣጡ ሴቶች ይሳተፉበታል፡፡ በችሎታ፣ በእውቀት፣ በእድሜ፣ በአንጋፋነት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ ሲመረጡ የምትመረጠው የአባገዳ ባለቤት ልትሆንም ትችላለች፡፡
ተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮች ሲደርሱ ሰዴታው በመሰብሰብ ይፀልያሉ፡፡ የሚሰበሰቡበት ቦታ የተለየ ሲሆን መልካ በመባል ይታወቃል፡፡ መልካ ማለት ከብቶች ውሀ የሚጠጡበት እና ሰው የሚሻገርበት ወንዝ ነው፡፡ ሁለት ወንዞች የሚገናኙበት ቦታም ይመረጣል፡፡
2ኛ. (አቴቴ ጎራ) ሠላማዊ ሠልፍ የሚወጡበት ስርዓት
ለሰላማዊ ሰልፍ የሚያስወጡ ምክንያቶች
1.     አራስ ሴት በባልዋም ሆነ በማንኛውም ሠው ስትመታ
2.    እናት፣ አማት፣ ሚዜ በማይገባቸው ጉዳይ ሲመቱ እና ማንኛዋንም ሴት ሞራሏን የሚነካ ስድብ ስትሰደብ
አራስ ሴት የአራስነቷ ምልክት የሆነ ቀነፋ የሚባል በግንባሯ ላይ የሚታሰር መለያ አላት፡፡ ቀነፋው በግንባሯ ላይ እያለ ትንሽም ቢሆን ከመታት እልልታዋን ታቀልጠዋለች፡፡ ያለማቋረጥ እልልታዋን የሰሙ ሰዎች እየተቀባበሉ ያስተጋባሉ፡፡ ያንን እልልታ የሰማች ሴት ምንም ዓይነት ስራ ብትይዝ ስራዋን ጥላ ህፃን እንኳን ብትይዝ ህፃኗን ጥላ ሲንቄዋን በመያዝ ትወጣለች፡፡ ፊት ለፊት ይሰበሰባሉ፤ ከመሀከል ሰዴታ ካለ ሁኔታውን ያጣራሉ፤ ካረጋገጡ በኋላ በሰውየው በር ፊት ለፊት መዝሙራቸውን እያዜሙ ክብ ሰርተው ይዞራሉ፡፡
ለዚህ የተለየውን ዜማ ሲያዜሙ ይህን የሰማ ወንድ ሁሉ የሀገር ሽማግሌዎች ተጠራርተው ወዲያውኑ ወጥተው ሽምግልና ይቆማሉ፡፡ ጉዳዩን ካጣሩ በኋላ ያልወጣች ሴት ካለች ገብተው በግድ ያስወጧታል፡፡ ውሀ እየቀዳች ከሆነ ውሀውን ደፍተው እንስራውን ሰብረው ይዘዋት ይወጣሉ፡፡ የሚበላ ነገር ካለ ይዘሽ ውጪ ትባላለች፤ ሠላማዊ ሰልፍ ለወጡት ሴቶች ምግብ ይዛ ትወጣለች፤ ባል ምንም መናገር አይችልም፤ ከተናገረ ለሱም ሠላማዊ ሰልፍ ይወጣበታል፡፡
አቴቴ ገርቡ ዳከቱ     
አቴቴ እህልሽን ትፈጫለሽ
ገርቡ አመዳከታ               
እህልሽን ትፈጫለሽ
ማፍና ዋከታ          
እኛን ለምን ትክጃለሽ፤ በማለት ወደኋላ የቀሩትን ሴቶች ያስወጣሉ፡፡
እርቅ ካልተፈጠረ ውለው ያድራሉ፡፡ ስለዚህ ሽማግሌዎች በፍጥነት ማድረግ የሚገባቸውን አድርገው መፍትሄ ይፈጥራሉ፡፡ ባለቤቷ ከጠፋ እንኳን የአካባቢው ሰዎች ከብት አርደው ይቅርታ ያስተናግዳሉ፡፡ ያ ሰውዬ ተፈልጎ መጥቶ እንደገና ከብት አርዶ ማር በጥብጦ እንዲክሳቸው ይደረጋል፡፡ እግራቸውም ላይ ወድቆ ይቅርታ ይጠይቃል፤ ተመርቆ ይገባል፡፡ ሴቶቹ እናት የምትሆንለትን ከሰደበ (ከመታ) እርቁ በእርድ ብቻ ሳይሆን ቡሉኮውን አልብሶ ጠጅ ጠምቆ ነው እርቅ የሚወርደው፤ የከብት በማረድ የመካስ ስርዓቱ ለሁሉም ዓይነት ጥፋት አለ፡፡ የታረደውን ስጋውን ጠብሰው እዛው ይበሉና ቀሪውን በመያዝ መርቀው እርቅ አውርደው ሠላም አስፍነው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ቆዳው ተሸንሽኖ ሲንቄያቸው ላይ ያንጠለጥላሉ፤ እሱም (ጎንፋ) ይባላል፡፡ የአርሲ ሴቶች ሲንቄ ይዘው ሲሄዱ በተንጠለጠለው ቆዳ ቁጥር እርቅ ፈፅመዋል ተብሎ ይታወቃል፡፡
እናት (አማት) ሚዜም ስትመታ ከአራሷ እርዱ እና ሌላው ስርዓት እንዳለ ሆኖ የሚለየው ቡሉኮ ያለብሳል፤ ጠጅ ጠምቆ እርቅ ይፈፅማል፤ ለአራስ ከሚደረገው በተጨማሪ ቀላ ገያ፣ መራ ገያ (ማልበስ)፣ ነቃ ገያ (ማልበስ) ቀላ (እርድ) በየትኛውም አይቀርም፡፡ ማንኛውም ሴት ሞራሏን የሚነካ ስድብ ስትሰደብ እንደ ስድቡ ክብደት መራና ነቃ ማልበስና ማጥመቅ ሊቀር ይችላል፡፡
3.   አቴቴ ለገላጋይነት
በአካባቢው ችግር ሲፈጠር ሽማግሌዎች መሀል ገብተው ማስታረቅ መገልገል ካልቻሉ ጉዳዩ ወደ አቴቴ ይላካል፡፡ አቴቴዎች ወዲያውኑ በእልልታ ተጠራርተው ግጭት በተፈጠረበት ቦታ ሄደው ሲንቄ (ብትራቸውን) ይዘው በመካከል ይገባሉ፡፡ ማንም ጀግና፣ ማንም ተበዳይ፣ ማንም ተፈንካች (ተወጊ) እነሱን ገፍትሮ ሊጣላ አይችልም፤ መሀል ገብተው እርቅ ያወርዳሉ፤ በእልልታ የብትሩን ጫፍና ጫፍ እየያዙ ተደርድረው መሀል ይገባሉ፡፡ ይሄንን ገፍቶ ሽሮ የሚጣላ ካለ ሊወጋ፣ ሊጣላ፣ ሊያጠፋ እነሱን ጥሎ በእናት ላይ ሲንቄን ሰብሮ (ገፍትሮ) ለጦርነት ከገባ በከፍተኛ ደረጃ ይረገማል፤ እርቁም በጣም እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ በገዳ ስርዓት ህግ ከፍተኛ ቅጣት ይበየንበታል፣ ከማህበራዊ ኑሮ ይገለላል፡፡
የዞኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች
ዞኑ ካለው ምቹ ሁኔታ በአግሮ ኢንዱስትሪ በፍራፍሬና በአትክልት፣ በስጋና የስጋ ውጤቶች፣ በአሳና የአሳ ውጤቶች፣ በፓስታና መኮሮኒ ምርት የሚሰማራ ባለሀብት ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፡- በባለ ኮከብ ሆቴሎች፣ ኢንተርናሽናልና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ እንዲሁም በሎጂና በሪዞርት ግንባታ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የቱሪዝም መዳረሻ ዞን ከመሆኑና በቂ ቦታ ከመኖሩ አንፃር ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ከዞኑ ኢንቨስትመንት መምሪያ ባገኘነው መረጃ መሰረት በዶዶላ ወረዳ ለከብት እርባታ 41 ሄክታር፣ በሻላ ወረዳ 7 ሄክታር ለመስኖ፣ ቆሬ ወረዳ 1100 ሄክታር ለሪዞርት በሳይት ፕላን የተደገፈ ቦታ የተዘጋጀ ሲሆን ቢሻን ጉራቻ በ2 ሳይት በድምሩ 4.3 ሄክታር፣ አርሲ ኔጌሌ በ2 ሳይት በድምሩ 20 ሄክታር ለሎጅ የተዘጋጀ ሲሆን ኢንቨስት በማድረግ ራስዎንና ሀገርዎን እንዲጠቅሙ ተጋብዘዋል፡፡




                  
                                                                      

No comments:

Post a Comment