Monday, December 24, 2012


አንድ ምሳ በማንኩሽ

Mankush
 ማንኩሽ በጣም ጥንታዊ ቀጠና ናት፤ እንደ አክሱም ሮሐ ጎንደርና ሸዋ አንድ ወቅት የሃገሪቱ የፖለቲካ ቀጠና ሆና አገልግላለች፡፡ ይህ ታሪኳ ከታላቁ የዳኣማት ስርወ መንግስት የሚጀምር ነው፡፡ የ2005 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀንን ያስተናገደው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የበዓሉን ተጓዦች ካስተናገደበት ስፍራ አንዱ ማንኩሽ ነበረች፡፡ ማንኩሽ ከመድረሳችን በፊት አሻግሮ ይመለከተን የነበረው ጉባ ተራራ ነበር፡፡ ማንኩሽ ስንደርስም ከተማዋን ቁልቁል እየተመለከተ ጠበቀን… የማንኩሽ ህዝብ በሆታ ሲቀበለን ጉባ ግን እንደተኮፈሰብን ተያየን፡፡ ከከተማዋ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጉባ ተራራ ለጉባ ወረዳ መጠሪያም ሆኗል፡፡

Tuesday, December 11, 2012


ካፋና ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ

በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ የለቅሶ፣ የሰርግ፣የጸሎትና የፍቅር ዘፈኖች አሉ፡፡  በለቅሶ ወቅት ሟችን የሚያወድሱ ጀግንነቱን የሚተርኩ ዘፈኖች ይዘፈናሉ፡፡ በተመሳሳይ የሸካዎች የሰርግ ሥነ-ሥረዓትም በባህላዊ ዘፈኖቻቸው የታጀበ ነው፡፡ እነዚህ ዘፈኖች እንደ ባህሉ በሚቃኙ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎች የሚደምቁ ናቸው፡፡ ጥቂቶችን እንቃኛቸው ከቲንቦ እንጀምር የትንፋሽ መሳሪያው ቲንቦ የካፋን የለቅሶ ሥረዓት በማድመቅ ወደር የሌለው መሳሪያ ሲሆን ከእንጨት የሚሰራ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለአዋጅ የሚጠቀሙበት ሲሆን ሃይል ያለው ድምጽ በማውጣት ይታወቃል፡፡

ያንጉ ዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ

የአዘሎ ስር ውበት

አዘሎ ውብና ግዙፍ ተራራ ነው፤ እንደ ሌላው ተራራ አዘሎን ከባህር ጠለል በላይ ይሔን ያክል ብሎ በሜትር በመለካት ርዝመቱን መተረክ አይቻል ይሆናል… ምክንያቱም የአዘሎ ውበቱ ከስሩ ሆኖ መታየቱ ነውና፤ ከመልካ ወረር ሜዳማ ምድር አልያም ከገዳማይቱ የተንጣለለ መስክ ሲታይ አዘሎ ርቆ የቆመ ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ አካባቢው ዝናብ ሲያገኝ አዘሎ አረንጓዴ ካባ ይለብሳል፡፡ ዝናብ ከራቀው ግን ከል ይለብሳል፡፡ አዘሎ ክረምትና በጋ ልቡስን የሚቀይር ተራራ፤

አብረሃ ወ አጽብሃ

Tigeray
ውቕሮ ከአዲስ አበባ በ829 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከውቕሮ ከተማ በስተ ምዕራብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ በአብረሃ ወ አጽብሃ ዘመነ መንግስት የታነጹ ናቸው፡፡ ከአክሱም ነገስታት በዝናቸው ገናና ስማቸው ዛሬም ድረስ ህያው ከሆኑ ነገስታት መካከል በጉልህ የሚጠቀሱት ወንድማማች ነገስታት አብረሃና ወ አጽብሃ ናቸው፡፡ ዒዛናና ሲዛን የተባሉትና በክርስትና ስማቸው በጉልህ ሚታወቁት እነኚህ ሁለት ወንድማማች ነገስታት ጥለዋቸው ያለፍት በርካታ የታሪክ ሰነዶች፣ የጹሑፍ ቅርሶችና የኪነ ህንጻ ውጤቶች ኢትዮጵያን የእድሜ ጠገብ መስህብ ሃብቶች ባለቤት ያደረጓት ናቸው፡፡

አንጎለላን በወፍ በረር                       

ሰሜን ሸዋ ብዙ ያልተነገረለት ምድር ነው፡፡ በሁሉም ወረዳዎች ከሶስት መቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠሩ ቅርሶች በርካታ ናቸው፡፡ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች የሚበዙበት ሰሜን ሸዋ ከስምጥ ሸለቆ ምድር እስከ ከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎችን ያካተተ መሆኑ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ ቀጠና ያደርገዋል፡፡ እንደ መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ የቱሪዝም ስፍራ ያሉ ቦታዎች ቱሪዝሙ ላይ ከተሰራ ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማከናወን እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡

የሀላላ ካብ

king halala wall
ብዙዎች ስለምን ይህን የመሰለ ቅርስ ሚስጥር ሆኖ ሳይወራለት ቀረ በሚል ይቆጫሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ቀኑ አልመሸም በሚል የኢትዮጵያውያን ድንቅ እሴት ማሳያ ነውና እንተርክለት ሲሉ ዝናውን ይናገሩለታል፡፡ የሁሉም ድምር ግን ከዳውሮዎች ምድር ያለው ድንቅ ቅርስ የኢትዮጵያውያንነታችን የኩራት ተምሳሌትነትን መዘከር ነው፡፡

የቻይናውን ግንብ የመሰለው ይህ ግንብ እንዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል ቢባል ለሰሚው ግራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያዊ ሰሚ፡፡ ምክንያቱም ይህ ከአምስት መቶ ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረው ካብ አንድ ዙር ርዝመት 170 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ነው፡፡ በዚህ ርዝመቱ የጎፋ፣ የወላይታን፣ የወላይታን፣ የካፋንና የጅማን ድንበር በሙሉ ያካልላል፡፡

Friday, December 7, 2012


7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን
የዋዜማ በዓል ዛሬ በድምቀት ይከበራል፡፡

ሀሚኮ፡-
ከባህር ዳር ከተማ
የአማራ ክልሏ መዲና ባህር ዳር እያስተናገደችው ያለው 7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ቀጥሏል፡፡ በባህር ዳር ዩንቨርስቲ ፔዳ ጊቢ አዳራሽና በአዲሱ የክልሉ ምክር ቤት መሰብሰቢያ እየተካሄደ ያለው ሲምፖዚየም ዛሬ ግማሽ ቀን በተናጥል ቀጥሎ ከሰዓት በኃላ 10፡00 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በወጣው መርሀ ግብር መሰረት ምሽቱን በጣና ሀይቅ ላይ የጀልባ ትርኢት የሚቀርብ ሲሆን በባህር ዳር ከተማ ጎዳናዎች ላይ የብሄር ብሄረሰብ ባህል ቡድን አባላት የባህል ትእይንት ያቀርባሉ፡፡ በባህር ዳር ስታዲየም ነገ የሚከበረውን አብይ በዓል በማስመልከት ዛሬ ምሽቱን ደማቅ የዋዜማ ዝግጅትና የርችት ተኩስ ይኖራል፡፡

Wednesday, December 5, 2012


 
ባህር ዳር በከፍተኛ ሁኔታ ደምቃለች፤

7ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ተጀምሯል፤

እንግዶች እየገቡ ነው፤ ምናልባትም እስከዛሬ በክልሉ ተዘጋጅተው ከነበሩ ኩነቶች የበለጠ ደማቁ ኩነት ሳይሆን አይቀርም፤

ከ100 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ታድመውበታል፤

የአማራ ክልል እርእሰ ከተማ የሆነችው የጣና ዳሯ ባህር ዳር በመብራት ባጌጡ ዘንባባዎቿ ተሞሽራ ከእስዛሬው የተለየ ደማቅ ሀገራዊ ኩነት እያስተናገደች ነው፡፡ 50 ሺ የሚደርስ ተመልካች የሚይዘው የባህር ዳር ስቴዲየም ለበዓሉ ማስተናገጃ ከተመረጡ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ አዲሱና አጠቃላይ ከ ግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚፈጀው የክልሉ የስብሰባ አዳራሽ የተወሰነው ክፍል ተጠናቋል፡፡ 2250 የሚበልጥ ታዳሚ በምቹ ሁኔታ ያስተናግዳል፡፡ የበዓሉ አካል የሆነው አንዱ ሲምፖዚየም በዚሁ አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

በዓሉን የሚታደሙትና ባህላዊ ትእይንት የሚያቀርቡት የብሄር ብሄረሰብ ልኡካን ቡድን ወደ ከተማዋ ሲገቡ በባህር ዳር ከተማ ህዝብ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በዓሉ በተለየ ሁኔታ ከነገ ህዳር 27 ጀምሮ በድምቀት ይከበራል፡፡