Tuesday, December 11, 2012


አብረሃ ወ አጽብሃ

Tigeray
ውቕሮ ከአዲስ አበባ በ829 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከውቕሮ ከተማ በስተ ምዕራብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ በአብረሃ ወ አጽብሃ ዘመነ መንግስት የታነጹ ናቸው፡፡ ከአክሱም ነገስታት በዝናቸው ገናና ስማቸው ዛሬም ድረስ ህያው ከሆኑ ነገስታት መካከል በጉልህ የሚጠቀሱት ወንድማማች ነገስታት አብረሃና ወ አጽብሃ ናቸው፡፡ ዒዛናና ሲዛን የተባሉትና በክርስትና ስማቸው በጉልህ ሚታወቁት እነኚህ ሁለት ወንድማማች ነገስታት ጥለዋቸው ያለፍት በርካታ የታሪክ ሰነዶች፣ የጹሑፍ ቅርሶችና የኪነ ህንጻ ውጤቶች ኢትዮጵያን የእድሜ ጠገብ መስህብ ሃብቶች ባለቤት ያደረጓት ናቸው፡፡


አብረሃ ወ አጽብሃ ክርስትናን ከተቀበሉ በኃላ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ፍልፍል ገዳማትንና ኪነ ህንጻዎችን አሰርተዋል፡፡ በስማቸው የተሰየመውና በውቅሮ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በተራሮች ከተከበበ አካባቢ ያረፈ ግማሽ አካሉን ከምድር ውስጥ የሸሸገ አስገራሚ መስህብ ነው፡፡

ከአለት ተጠርቦ የተሰራው እና ከተፈለፈለበት አብይ አለት ጋር ሳይላቀቅ የቆመ አለት ይሁን እንጂ የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው፡፡ 16 ሜትር በ13 ሜትር ስፋት ያለው ይህ ቤተ ክርስቲያን የጣሪያው ቁመት ሰባት ሜትር ይደርሳል፡፡ 13 የሚሆኑት ጣሪያውን ደግፈው የቆሙት አምዶች ግዙፍና ድንቅ ናቸው፡፡ በሃረግ ሥነ-ጥበብ ያጌጠው ጣሪያ ቀና ብሎ ለሚመለከተው ሰው አድናቆትን ያጭራል፡፡

የአብረሃ ወ አጽብሃ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ሶስት አብያተ መቅደሶች ያሉት ሲሆን በቀኝ የቅዱስ ሚካኤል በግራ የቅዱስ ገብርኤልና መካከል ላይ የቅድስት ማርያም ታቦተ መንበሮች ያሉበት ነው፡፡ አስደናቂ የሆነው ውቅር ውስጣዊ ውበቱ ከተሰራበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ተአምር ሲሆን በአንዳንድ የውጪ ጸሐፍት ዘንድ በትግራይ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚበልጥ እንደሆነ ተገምቷል፡፡

በውቅሩ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሳሉት መንፈሳዊ ስዕሎች በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጥንታዊና እና እጹብ የሥነ ሥእል ውጤቶች መካከል የአባ ሰላማ ፍሬምናጦስ ስእል ይገኝበታል፡፡ በተመሳሳይ በቅኔ ማህሌቱ የሚታዩት ስእሎችም የጻድቃን፣ የመላእክትና የሰማእታትን ገድሎች ያሳያሉ፡፡

አንዳንዶች የተሰራበት ዘመን ላይ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም በዋናነት ከአባቶችና ከቤተ ክርስቲያን የተገኙ መረጃዎች ግን በ4ኛው ክፍለ ዘመን የተሰራ እንደሆነ ያትታሉ፡፡ ይህም በራሳቸው በአብረሃ ወ አጽብሃ ዘመነ መንግስት ማለት ነው፡፡ ይህ ኪነ ህንጻው ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ገጽታው የሚያስደንቀው ውቅር በውስጡ አያሌ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ በዋናነትም የአባ ሰላማ መስቀልን ጨምሮ በርካታ ጥንታዊ ንዋየ ቅድሳትን የያዘ ነው፡፡ ለትራንስፖርት ምቹ የሆነው የአብረሃ ወ አጽብሃ ውቅር ቤተ ክርስቲያን እንግዳ በአግባቡ ተቀብለው የሚያስተናግዱ አገልጋዮች ያሉበት መሆኑ እንደልብ እንዲጎበኙት ያግዝዎታል፡፡

No comments:

Post a Comment