Friday, March 27, 2015

የባህል ማዕከሉ ተመረቀ



የባህል ማዕከሉ ተመረቀ
   ከ 300 ሚሊዩን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የተሰራው የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ተመረቀ፡፡
          የኦሮሞ ባህል ታሪክና ቋንቋ ገላጭ የሆነውና ሰፊዋን ኦሮሚያ ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳየው የኦሮሞ ባህል ማዕከልን የመረቁት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዘዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሲሆኑ በስፍራውም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አፈጉባሄ ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
    በአዲስ አበባ እስታዲዮም አካባቢ የሚገኘው በ57,100 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የኦሮሞ ባህል ማዕከል ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ሲሆን በውስጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ታሪክ ጥናትና ምርምር ማዕከል ፣የኦሮሞ ብሄረሰብ ታሪክና ባህል የሚያሳይ ሙዚየም፣የስብሰባ ማዕከል፣ለኤግዚቢሽን፣ለፊልምና ቲያትር ማሳያ፣ለቱሪስቶች የመረጃ ማዕከል፣በባህል እቃዎች መሸጫ፣የማንበቢያ ስፍራ(አዳዲስ መፃህፍቶች የሚገኙበት)፣ ሌሎች ብሄረሰቦች ስለ ኦሮሚያ ብሄረሰብ ባህል ቋንቋ ታሪክ፣ እንዲያውቁ የሚረዳ በተጨማሪም ሌሎች ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን የሚሰጥ ነው፡፡
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዘዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንደገለፁት የባህል ማዕከሉ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መገንባቱ ተጨማሪ የባህል ማሳደጊያና የቱሪዝም ገቢ ማስገኛ ረገድ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ብሄራዊ መንግስት ይህንን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያለውን ዘመናዊ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ለመገንባት ያሳየው ተነሳሽነት ለኦሮሞ ባህልና ቋንቋ እድገት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ይህን የባህል ማዕከል ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸው የሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶች ለማቅረብ ሲፈልጉ እንደራሳቸው አድርገው የሚጠቀሙበት እንደሚሆን እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ባህል ማዕከል የኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ ከሚኖረው ወሳኝ ድርሻ ባሻገር ለህብረተሰቡ ምቹ የመዝናኛና ለጥሩ የጊዜ ማሳለፊያነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡