Wednesday, September 17, 2014


አፋር ያልተነገረላቸው ሁሉ አቀፍ የቱሪስት መስህቦች ቀጠና

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኢትዮጵያ ከሚገኙ 9 ክልሎችና 2 ከተማ መስተዳደሮች አንዱ ነው፡፡ ክልሉ ጂኦግራፊካሊ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በ39 14 እና 42 28 ሰሜን የኬክሮስ መስመርና በ8 49 እና በ14 30 ምስራቅ የኬንትሮስ መስመሮች ይገኛል፡፡
Afar-
 

የአፋር ክልል በ5 አስተዳደራዊ ዞኖች 31 ወረዳዎችና በ1 ልዩ ወረዳ የተዋቀረ ነው፡፡ የቆዳ ስፋቱም 96,256 ስኩየር ኪ.ሜ ነው፡፡  እንደ ኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ 2007 መረጃ መሰረት 1,411,920 ህዝብ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም 86.6% በገጠር ቀሪው በከተማ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ አፋርኛ ቋንቋ የክልሉ የስራ ቋንቋ ሲሆን 90.8% ተናጋሪዎች አሉት፡፡

በክልሉ 6.68%  አማርኛ፣ 0.74%  ትግረኛ፣ 0.68% ኦሮሞኛ፣ 0.4% አርጎብኛ እና 0.26% ወላይተኛ ተናጋሪዎች ይገኛሉ፡፡ በክልሉ 96% ሙስሊም፣ 3.68% የኦርቶዶክስ ክርስቲያን፣ 0.43% ፕሮቴስታንት፣ 0.09% ካቶሊክ እና 0.02% ሌሎች ሃይማኖት ተከታይ ህዝቦች ይኖራሉ፡፡ በክልሉ 90% ህዝብ የሚተዳደረው እንስሳት በማርባት የአርብቶ አደር ህይወት ሲሆን ቀሪው ሰብል በማምረት፣ በጨው ንግድ እና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ነው፡፡

ክልሉ የሚገኘው በታላቁ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ሲሆን አብዛኛው የክልሉ ክፍል ሜዳማ ነው፡፡ በክልሉ ከ116 ሜትር ከባህር ጠለል በታች እስከ 1600 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላቸው ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡

ሙሳ አሊ ተራራ 2063 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያለው ሲሆን በክልሉ ትልቁ የከፍታ ጫፍ ነው፡፡ ክልሉ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ዝቅተኛ ዓመታዊ የዝናብ መጠን የሚያገኝ ሲሆን ዓመታዊ የሙቀት መጠኑም ከ18-45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ  ይደርሳል፡፡

አፋር ክልል የበርካታ ማዕድናት መገኛ ነው፡፡ ጨው፣ ፖታሽ፣ ሰልፈር፣ ማግኒዝ፣ ቤንቶናይት፣ አልሙኒየም፣ እምነበረድ፣ ጂፕሰም እና ፔትሮሊየም ዋና ዋናዎቹ የክልሉ የማዕድን ሃብቶች ናቸው፡፡ ተንዳሆ ጂኦተርማል  እና የጸሃይ ኃይል የክልሉ አማራጭ የኤሌክትሪክ ምንጮች ናቸው፡፡

 ሁሉ አቀፍ የቱሪስት መስህቦች ቀጠና የሆነው አፋር ክልል ከሀገሪቱ አልፎ ዓለምን ያስደነቁ፣ ጠበብቶችን ያመራመሩ፣ የጉዞ ጸሐፍትን አፍዘው ያስቀሩ መስህቦች ምድር ነው፡፡ ከእነዚህ ልዩ የዓለማችን መዳረሻዎች መካከል ደግሞ በተፈጥሯዊ መስህብነት የሚጠቀሱት የምድራችን ድንቅ የተፈጥሮ ገጽታዎች የዳሉል ዝቅተኛ ቦታዎችና በህብር የደመቁ የተለያዩ ማዕድናት፣ ቅርፆች፣ የኤርታዕሌ እሳተ ጎሞራ፣ የአስዓለ ሐይቅ፣ የአፍዴራ የጨው ክምር ይገኙበታል፡፡ በታሪካዊ መስህብነት ደግሞ የነሉሲ መገኛ የሰው ዘር ምንጭ ስፍራ የሆነው ሐዳርና አካባቢው የተለያዩ የስነ ቁፋሮ ስፍራዎችና የምርምር ቦታዎች  ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ምንም ያልተነገረላቸው ቱባ የአፋር ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች ሌላው የክልሉ የቱሪስት መስህቦች ናቸው፡፡ በተለይም የአፋር ህዝብ አኗኗር፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጸጉር አሰራር፣ ሙዚቃ፣ ጭፈራ፣ የበዓል አከባበር፣ የግጭት አፈታት /መድአ/ እና ስፖርት /ኳዕሶ/ ይጠቀሳሉ፡፡ እነኚህ አኩሪ የክልሉ ባህላዊ እሴቶች ከአፋር ህዝብ መገለጫዎች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በዚህ አጭር ዳሰሳ ሁሉንም ዓይነት የአፋር ክልልን የቱሪስት መስህቦች ለማቅረብ አይቻልም፡፡ ካልተነገረላቸው ቱባ የአፋር ባህላዊ እሴቶች መካከል የአፋር ህዝብ ለዘመናት ሲጠቀምባቸውና እየተጠቀመባቸው ያሉ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶችን በወፍ በረር እንቃኛቸው፡፡

የአፋር ሴቶች ጥበባዊ እውቀታቸውን በመጠቀም ከእንሰሳትና እጸዋት ውጤቶች የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ይሰራሉ፣ መገልገያ ቁሳቁሶች  ወብና ያማሩ እንዲሆኑ ኡንጋን /ዘምባባን/ የተለያዩ ቀለማት በመንከርና በማቅለም ለስፌት ያዘጋጁታል፣ ኡንጋን ከማማቅለማቸውም ሌላ ለስላሳ ቆዳ፤የተለያዩ መልክ ያላቸው ስንድዶችና ዛጎሎችን በመጠቀም ያጌጡና ማራኪ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ይሰራሉ፡፡

ሙዴይና እና መካሮ የተባሉ መስፊያዎችን ለማያያዥነት ይጠቀማሉ እንጅ ሁሉም የስፌት እቃዎች ሲዘጋጁ በእጅ እንጂ ሌላ መሳሪያ አይጠቀሙም ፣የአሠራራቸው ትውፈታዊ የእደ ጥበብ እውቀትና ክህሎት ሲወርድ ሲዋረድ ቤተሰብ ቤተሰብን /እናት ልጇን/በማስተማር የመጣ የእወቀት ጥበብ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment