Wednesday, September 17, 2014


በናና ጸማይ…..


 
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ደቡብ ኦሞ ዞን ስር ከተዋቀሩት 8 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር መካከል የበናና ፀማይ ወረዳ አንዱነው፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቀይ አፈር ከዞኑ ዋና ከተማ ጂንካ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወረዳው በሰሜን ከደቡብ አሪ እና ማሌ፣ በደቡብ ከሐመር ወረዳ፣ በስተምስራቅ ከኮንሶ በምዕራብ ከማጎ ፓርክ እና ሳላማጎ ወረዳ ጋር ይዋሰናል፡፡ በዞኑ ከሚገኙት 16 ብሔረሰቦች ውስጥ በዋናነት ሶስቱ ብሔረሰቦች የሚገኙት በዚህ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህም የበና፣ የፀማይ እና የብራይሌ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡

የወረዳው የህዝብ ብዛት 68.6553 ሲሆን የብሔረሰብ ስብጥሩ ደግሞ በና 48.8 ‰ ፀማይ 36% ብራይሌ 0.02% ሌሎች ብሔረሰቦች ደግሞ 15%  ያቀፈ ነው፡፡ የወረዳው የአየር ንብረት  ደጋማ 1% ወይና ደጋ 13.7% ቆላ 81% ከፊል በረሀ አካባቢ 5% ይዟል፡፡ የመሬት አቀማመጡ ተራራማ፣ ሜዳማ እና ተዳፋት ሲሆን በ32 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡

በወረዳው ውስጥ የሚገኙት የበና የፀማይና የብራይሌ ብሔረሰቦች ለዘመናት ሲሸጋገር የመጣ  ድንቅና ታሪካዊ ሥርዓት ብዙ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተካተቱ፣ ለቱሪዝም መስህብ የሆኑ የተለዩ ባህላዊ እሴቶች እና የተፈጥሮ ሀብቶች  ባለቤት  ናቸው፡፡ በዚህ ዳሰሳ እነዚህን በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን፡፡

          I.      የፀማይ ብሄረሰብ የግጭት አፈታት ዘዴ ባልኮ /ባሌ/

በብሄረሰቡ (በአካባቢው) ሰው ከተፈነከተና ደም ከፈሰሰ ባልክ /የሀገር ሽማግሌዎች/ በመሰብሰብ የተደበደቡበትን ዱላ አስቀርቦ ባላ ያለው ብትር በመትከል ውሐ ይዞ ቡሎ የሚባል ፍሬ ወይም በግ በማረድ ፈርሱን ከአፈር ጋር በማነካካት እና በባላው ሥር በመድፋት እርቅ ይፈፅማሉ፡፡ በግጭቱ ነፍስ ከጠፋ ሽማግሌዎች /Elders/ ከጐሣው በጉዳዩ ይግባቡና የገዳይ ወገን ማለትም ለሟች ወገን ለሟቹ ተብሎ ልጃገረድ እንዲሰጥ ይደረጋል፤ አዲስ ሾርቃ ከቅል የተሠራ መጠጫ የእህል ዘር ይቀርብና ካብ ተቆፍሮ ሁለቱም ወገኖች በተቃራኒ አቅጣጫ ቆሞ ሾርቃውንና የበሎን ፍሬ እየለዋወጡ በመቀባበል እንዲነኩ ይደረጋል፡፡

በግ ታርዶ ሁለቱም ወገኖች ፈርስ ውስጥ እጃቸውን እንዲነክሩ ይደረጋል፡፡ በባህሉ ሰው ሲሞት በሟች ስም አዋልኮ የሚባል ሥርዓት ይፈፀማል፤ ይህም በስሙ ሚስት ትዳራለች፡፡ ከሟቹ ወንድሞች ብትወልድ የሚወለደው ልጅ በሟቹ ስም እንዲጠራ ይደረጋል፡፡ 

የፀማይ ብሄረሰብ የባህላዊ ኀሬ ሥርዓት /በእናትና አባት የሚሠራ ሥርዐት/

ጐሬ ማለት ብሄረሰቡ ለማግባት የደረሰ ወንድ ልጅ የምሠራለት ደንብ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ይህንን ደንብ ለመሥራት በመጀመሪያ ለጎሬ ክንውን ሥርዐት ደንቡን ለመሥራት ለአጐት ለእናት ወንድም አቢዮ ሎንጋቴ ይነገራል፡፡ የጎሬ አጐት ማለት ፈፃሚ ማለት ነው፡፡ በመቀጠል ለአድራጊው ይነገረዋል፡፡ በተስማማበት ለመሥራት እሺ ይላል፤ የልጁ ቤተሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን ወደ አጐቱ ይልኩና ያስማማሉ፡፡ አጐቱም እጅ መንሻ በሬና ማር ይቀበላል፡፡ ካልተስማማበት የሀገር ሽማግሌዎች ከጎሬ ከሠሪ ቤተሰብ ይላካል፡፡ እሺ እንዲል ማር ወይም በሬ ይሰጠዋል፡፡ በመቀጠል እስከ አንድ ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ጎሬ ሠሪው ደንቡን ለመሥራት ሲጀምር የተለያዩ የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት እንዲገኙ ይደረጋል፡፡ ቀጥሎም የባህላዊ የምግብ ዓይነቶችና ባህላዊ የመጠጥ ዓይነቶች ይዘጋጃሉ፤ ይበላል ይጠጣል፡፡ ጎሬ ከመታሰር እና ከመፈፀሙ በፊት አባትና እናት በመጋረጃ በተጋረደ ቃል ኪዳን ይገባሉ፡፡ ሥርዓቱን ከፈፀሙ በኋላ ሴት ልጅ ትመጣና በመጋረጃ ውስጥ ገብታ በወገቧ ላይ የታሰረውን ገመድ /ምርኮ/ በጥሣ ትጥላለች፡፡ እናትና አባት በህይወት ባይኖሩ እንኳን ከመቃብር አፅም በማውጣት ሥርዓቱ እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡

የፀማይ ብሄረሰብ አግቢው የጎሬ ስርዓት

በመጀመሪያ ወደ ስርዓቱ አድራጊ /አብ/ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ወንድ ልጅ በመጀመሪያ ይቀመጣል፡፡ በመቀጠል የሚቀጥለው በተራ ከተቀመጡ በኋላ ከለጌና ከዝንጀሮ ቆዳ የተሠራ የዝንጀሮው ቆዳ ግን ውሻና አውሬ ያልነካው መሆን አለበት፡፡ ከዝንጀሮ ቆዳ ትንሽ ትንሽ በመቁረጥ በላጊው /ገመድ/ ላይ በመብሣት የሥርዓቱ አድራጊ /አብዮ/ ጉርቴ/ በእጃቸው ላይ ያስራሉ፡፡ በመቀጠል ቀጠሮ የሥርዓቱ አድራጊ /አብዮ ሎንጋቴ/ ቀስት ይወስዳሉ፡፡ የቀስቱ ትርጉም ጀግና ናችሁ ማግባት ትችላላችሁ በማለት ይመርቋቸዋል፡፡

ለሴት ልጅ ግን ችግር የለውም፤ ወንድ ልጅ ግን ለአቅመ አዳም ከደረሰ ጐሬ ካልተሠራ /ሥርዓቱ/ ካልተሠራ ማግባት አይችልም፡፡ በብሄረሰቡ ዘንድ ጐሬ ካልተሠራ ከባድ የተለያዩ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ችግርና መከራ ይከሰታል፤ የሚወለዱት  ልጆችም አያድጉም ተብሎ ይታሰባል፡፡

የለቅሶ ሥርዓት /ኢልሜ/

አንድ ሰው ታምሞ ከሞተ በኋላ ዘመዶቹ የሆኑትና በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች የማህበረሰቡ አባላትም በአንድ ጥላ ሥር በመሠብሰብ ያለቅሣሉ፡፡ ጥይት ይተኩሣሉ፤ ሟቹ እድሜ ጠገብ ከሆነ ብዙውን ጊዜ አያለቅሱም፡፡ የተለያዩ የሀዘን መግለጫ ፉከራዎችን እያሰሙ ቦርዴ /ፈርሼ/ አዘጋጅተው ይጠጣሉ፤ ይጨፍራሉ፡፡ በትልቅ ማሰሮ /እንስራ/ ዝዕቴ/ ይቀቀልና ይበላሉ፡፡ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ጐልማሶች እየጨፈሩ ጥይት እየተኮሱ ሟቹ እስከሚቀበር ድረስ ይጠጣሉ፤ ይበላሉ፡፡ በርከት ያሉ ፍየሎችም ይታረዳሉ፡፡ ሟቹ ዕድሜ ጠገብ ከሆነ እስከ 2 ቀን ድረስ ሣይቀበር በቤት ውስጥ ይቆያል፡፡

ሟቹ ትንሽ ልጅ /ወጣት/ ከሆነ ሀዘኑ ይጠነክራል፡፡ ቦርዴ /ፓርሼ/ አይጠጣም፣ የማቹ እናትም ፀጉሯን ቶሎ ቅቤ አትቀባባም፣ አትሠራም፡፡ ሀዘኑ ከበድ ያለ ነው እንደአዛውንቶቹ ግን ቀብሩ አይቆይም፡፡ እንደሞተ ወድያውኑ ይቀብራል እንጂ ውሎ አያድርም፡፡ በበናና በሐመር ብሔረሰብ አብዛኛው ሥርዓት ተመሳሳይነት አለው፡፡ የሰርግ ሥነ ሥርዓቱ የሐመርን  ብሔረሰብ በተመለከተ ባለፈው እትም ከገለጽንው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን የለቅሶ ሥርዓቱን እንቃኛለን፡፡

የበና ብሔረሰብ የቀብርና የለቅሶ ሥርዓት

በበና ብሔረሰብ የሞተው ህፃን ከሆነና ከብት ያልዘለለ እንዲሁም ያልታጨች ሴት እንደ ሙሉ ሰው አይታዩም፡፡ የለቅሶና የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም የሁለቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ በከብት በረት አካባቢ ይቀበራሉ፡፡ እንብዛም ሥርዓት ያለው ለቅሶ አይደረግም፡፡ ከብት የዘለለና ለባሏ የታጨች /አዋቂዎች ሲሞቱ/ ነፍሱ የተለየው ቢሆንም ድግስ ለመደገስ የሚበቃ እህልና ከብት ከሌለው እንዳልሞተ እየተነገረ ለሥርዓቱ ማስፈፀሚያ የሚያስፈልጉ ነገሮች እስኪሟሉ ይጠበቃል፤ አይቀበርም ማለት ነው፡፡ አስክሬኑ ሳይቀበር የሚቆይበት ጊዜ እስከ 4 ቀን ሊደርስ ይችላል፡፡

አዋቂ ሰው ሲሞት ሙሾ እየተደረገለት ጥይት እየተተኮሰ ታሪክና ዝናው እየተነገረ አስክሬኑ ያለበትን ቤት ዙሪያውን በመዞር እና ብረታ ብረት በማቃጨል ይዘከራል ይጨፈራልም፡፡ አስክሬኑ የሚገነዘው የሁለት እጆች መዳፍ ጉንጮቹ ላይ በመደገፍ እግሮቹን እንዲያጥፍ በማድረግ ለማስቀመጥ እንዲያመች በማድረግ ነው፡፡ ከዚያም በራሱ በሬ ቆዳ ተጠቅልሎ ወደ መቃብሩ ይደርስና ራቁቱን ወደ መቃብሩ ይገባል፡፡ ፊቱንም ቀደም ብሎ የእሱ ጎሳዎች ወደ መጡበት አቅጣጫ አዙረው ይቀብሩታል፡፡ የሚቀበርበት የመቃብሩ ጥልቀት ቢበዛ አንድ ሜትር እና ከዚያ ባነሰ ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻም አፈር በማልበስ ከተደቀደቀ በኋላ በመቃብሩ እናት ላይ ድንጋይ ይከመርና ያበቃል፡፡

የአለባበስ ሁኔታ

የወንዶች አለባበስ

ወንዱ በወገቡ ላይ ግልድም ወይም አጠር ያለ /ሽርጥ/ ይታጠቃል፡፡ በላዩ ላይ ጀበርና ወይም ቀበቶ ያስርበታል፡፡ በእጆችና በእግሮች መገጣጠሚያዎች ላይ በአንድ ላይ የተሠሩ ጨሌዎቹን ያስራል፡፡ የፀጉር አሰራሩን በተመለከተ አንዳንዶች ሹሩባ ይሠራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከአፈር የተሠራ ጭቃ በማዘጋጀት በጭንቅላቱ አናት ላይ ፀጉሩን በመሰብሰብ በጭቃው ‘‘ዾሮ ’’ የተባለ አሠራር ይሠራል፡፡ በአንገቱ ላይ የተለያዩ ቀለም ያላቸው ጨሌዎችን ያጠልቃል በስተመጨረሻም በመርገጫው እግር ከመኪና ጐማ በተሠራ ‘‘ድንጉሪ’’ ጫማ ሠርተው ያደርጋሉ፡፡ በእጆች ክንድና በጣቶች ላይ የተለዩ አንባሮችን ያጠልቃሉ፡፡

የሴቶች አለባበስ  

ሴቶች በተለይ ያገቡና ያላገቡት አለባበሳቸው ይለያል፡፡ ያገቡ ሴቶች ከፊት ሰፋ ያለ ቆዳ ይታጠቃሉ፡፡ ያላገቡት ልጃገረዶች ከፊት ከጨሌና ከጥቂት ቆዳ የተሠራ ጠበብ የሚል ‘‘ስላ’’ ይታጠቃሉ፡፡ ያገቡ ሴቶች በደረታቸው ላይ ዳር ዳሩ ከዛጐል የተሠራ ቆዳ በአንገታቸው ላይ ያጠልቃሉ፡፡ ያላገቡት ልጃገረዶች አንዳንዶች ከኔቴራ ይለብሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ደረታቸውን ያሳያሉ፡፡ ያገቡት ሴቶች ፀጉራቸው ከጭቃ፣ ከዕጣን ከቅቤ ጋር አድርገው ቀይ አፈር በመጨመር የተጠቀለለ አሰራር ይሰራሉ፡፡ ያላገቡት ደግሞ  ፀጉራቸው ሽሩባ ይሰራል፡፡

የብራይሌ ብሔረሰብ /ኦንጐታ ብሄረሰብ/

  የብራይሌ ብሔረሰብ /ኦንጐታ ብሄረሰብ/  በበና ፀማይ ወረዳ በእንጨቴ ቀበሌ በልዩ ስሙ ገኤ ወንዘ ድሮ ነው በሚባል መንደር መንደር ተሰባስበው ይኖራሉ፡፡ ብራይሌዎች አንድም የብሔረሰቡ አባል ከተጠቀሰው ቀበሌ ውጪ በሌላ በየትኛውም ስፍራ አይገኝም፡፡

የብሔረሰቡ አመጣጥ

የብሔረሰቡን አመጣጥ በተመለከተ በተለያዩ አከባቢዎች ድርቅና ረሀብ በመከሰቱ ምግብ ፍለጋ /ከረሀብ ሽሽት ከሰባት ከማያንሱ አካባቢዎች/ ኮንሶ፣ ገዋዳ፣ ማሌ፣ በና፣ ጋቦ፣ ቦረና እና ኤርቦሬ/ የመጡ ቡድኖች የበራይሌን ብሔረሰብ እንዲመሠረቱ የብሔረሰቡ እድሜ ጠገብ አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡

ወቅታዊ ሁኔታ

በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የብሔረሰቡ ብዛት /ከ61/ የማይበልጥ ሲሆን በትክክል ቋንቋውን የሚናገሩት ደግሞ 12  ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ በደንብ የሚናገሩት ደግሞ 6 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ የብሄረሰቡ ቋንቋ “አንጐታ” ሲሆን ከተናጋሪዎች አህዝ በመነሳት ቋንቋው አደጋ ተጋርጦበታል፡፡

ግጭት አፈታት

ብራይሌዎች በግጭቶች ምከንያት ደም ከፈሰሰና የሰው ህይወት ካለፈ የእርቅ ሥርዓታቸውን የማፈፅሙት እንደሚከተለው ነው፡፡ የእንቧይ ፍሬ ለሁለት ይከፍሉና ደንብ /ባህላዊ አምልኮ/ ሥርዓት ከተፈፀመ በኋላ የእርቅ ሥነ-ሥርዓቱ ይፈፀማል፡፡

       I.      ጋብቻ /ሰርግ

የብራይሌዎች ጋብቻ ሦስት ዓይነት ነው፡፡

1ኛ. “ኢፋም” ይህ ዓይነቱ ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም ነው፡፡

2ኛ “ኣይሳት ሻዳል ቤት” ይህ ደግሞ የውርስ ጋብቻ በመባል ይታወቃል፡፡

3ኛ. “እዴ ባደጂካ ኢስማ” የዚህ ዓይነት ጋብቻ የሚፈፀመው በተጋቢ ወላጆች ስምምነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወንዱ ለአቅመ አዳም በሚደረስበት ወቅት ለሴቷ ጥሎሽ የሚሰጠው ዓሳ፣ ማርና ልብስ /ጋቢ/ ነው፡፡

አመጋገብ ስርዓቶች

ብራይሌዎች የሚመገቡት ልዩ ምግብ /ዓሳ/ ሲሆን ከወይጦ ወንዝ አውጥቶ /ይዘለዘላል/ እንደቋንጣ ይሰርሌ /በመዘልዘል/  ይመገባሉ፡፡

No comments:

Post a Comment