Wednesday, September 17, 2014


የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ሙዚየም
የልጅ እያሱ አልጋ
 

አዲስ አበባ ከሚገኙ 14 ሙዚየሞች አንዱ የቀጨኔ ሙዚየም ነው፡፡ ቀጨኔ ሙዚየም በአስተዳደር ጊዜያቸው ለህብረተሰቡ ኑሮ ምቹ ከመሆናቸው የተነሳ አቤቶ (ማር) የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ልጅ እያሱ ከመቶ ዓመት በፊት  ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ካሳነፁ በኋላ የተቋቋመ ሙዚየም ነው፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች ብዙዎቹ የልጅ እያሱ የግል መገልገያ እቃዎች፣ ነዋየ ቅድሳት፣ አልባሳት እና የተለያዩ ነገስታት ስጦታዎች ይገኛሉ፡፡


ሙዚየሙ በጽዳት ተይዦ ጎብኚዎች ሲመጡ የሚከፈት ሲሆን ማንኛውም ወደ ሙዚየሙ የሚመጣ ሰው ወደ ውስጥ ሲገባ ጫማውን ያወልቃል፡፡ ውስጡን ስለ ቅርሶቹ በሚያስረዱት አባት ታግዘው ይጎበኛሉ፡፡ በሙዚየሙ ያሉትን ቅርሶች ስንቃኛቸው በመጀመሪያ የምናገኘው 1960 ዓ.ም. ልጅ እያሱ ይተኙበት የነበረውን የጠፍር አልጋ፣ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሰራ ከበሮ፣ በመጠኑ ተለቅ ያለ አገልግል፣ የልጅ እያሱ ሰደርያ፣ ድባብ (ታቦተ ህጉ) ወደ ውጪ ሲወጣ የሚያዝ፣ የልጅ እያሱ ወርቃማ ቀበቶ፣ ከቆዳ የተሰራ ማህደር /የብራና ማስቀመጫ/፣ ሞዓ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ የሚል ፅሁፍ ያለበት በጥልፍ የተሰራ ጌጥ፣ በሙካሽ የተሰራ የንግስት ዘውዲቱ ካባ፣ ታቦት የሚሸከሙ ቄሶች የሚለብሱት ሱሪ፣ መያዣቸው ብር የሆነ የሙካሽ ጥላዎች፣ 1930 ዓ.ም ለአገልግሎት ስንጠቀምባቸው የነበሩ የኢትዮጵያ የብር ኖቶች፣ የጣሊያን እና የኬንያ ብር፣ ከጣሊያን አገር የመጡ ለቤተክርስቲያኑ የተበረከቱ ጥላዎች፣ በቆዳ የተሰራ የአፄ ቴዎድሮስ ምስል፣ በብር የተለበጠ መሶበ ወርቅ፣ አቤቶ እያሱ በፈረስ ላይ ሆነው የሚያሳይ ስዕል፣ ወርቅ ቅብ አውድ ከነ አጎበሩ፣ በ1918 ዓ.ም ከአጼ ኃይለ ስላሴ የተሰጠ የመጾር መስቀል እናገኛለን፡፡

መካከል ላይ ባለው መስታወት ከፊትና ከኋላ የተደረደሩ ቅርሶች ውስጥ የብር አክሊል ከላይ ዕቴጌ መነን የሚል ፅሁፍ ያለበት ከዕቴጌ መነን የተሰጠ፣ የልጅ እያሱ እና የእቴጌ መነን ምስል፣ 1915 ዓ.ም. ከንግስት ዘውዲቱ የተበረከተ የብር አክሊል፣ ከእቴጌ መነን የተሰጠ ወርቅ ቅብ አውድ ከነ አጎበሩ፣ በ1918 ዓ.ም ከአጼ ኃይለ ስላሴ የተሰጠ የመፆር መስቀል፣ የራስ ቆብ ያለው የግብፅ ጳጳሳት ካባ፣ ከነሀስ የተሰራ መስቀል፣ ጥንታዊ የሆኑ ግብጻዊያን ለቅዳሴ አገልግሎት የሚያደርጉት አክሊል በስጦታ መልክ የተሰጠ፣ በሌሎች ነገስታትና በልጅ እያሱ የሚለበሱ ካባዎች፣ ኮሞር መጎናፀፊያ፣ የሙካሽ ቆብ፣ 1982 ዓ.ም በወርቅ የተሰራ ሙካሽ፣ ታቦት የሚሸከሙ ቄሶች ቆብ፣ ቀበቶ፣ የሊቀ ጳጳሳት መቀደሻ አልባሳት፣ ከመዳብ የተሰራ መቅረጽ፣ ከንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ የተሰጠ የብር ጽንሐ፣ ከልጅ እያሱና ከንግስት ዘውዲቱ የተሰጡ የነሐስ መቁረርቶች፣ የተክሊል ኮፍያ፣ በብር የተሰራ የዕጣን ማቅረቢያ፣ በ1912 ዓ.ም ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የተበረከተ የብር ፅዋ፣ የተለያዩ የብር፣ የነሀስ፣ የአልሙኒየም እና የቆርቆሮ ባለ ሻኩራ ጽዋዎች፣ የብራና ላይ መፅሀፍት፣ ስንክሳር፣ አርባዕቱ ወንጌል፣ በ1992 ዓ.ም ከእቴጌ ጣይቱ የተሰጠ መፅሀፈ ኤርሚያስ፣ ግብረ እማማት፣ መፅሀፈ ድጓ፣ ከብራና ወደ ወረቀት የተቀየሩ መፅሀፍቶች፣ ማህደር (የብራና መያዣ በጥንቃቄ እንዲቀመጥ የሚያገለግል) እና በአድዋ ጦርነት ጊዜ ሚኒሊክ ይዘው የሄዱት የብራና መፅሀፍ እንመለከታለን፡፡

በሙዚየሙ ግርግዳ በኩል በጽሐፊ ትእዛዝ ኃይለ ወልደ ሩፋኤል 1930 ዓ.ም የተሳለ የቀድሞዋን የኢትዮጵያ ሙሉ ካርታ ያካተተ ስዕል፣ የብር ፅናፅንና መቋሚያ፣ በ1914 ዓ.ም ከግሪክ ሀገር በስጦታ መልክ የመጡ ጽንሐዎች፣ በቆዳ ላይ የተሰራ የእቴጌ መነንና የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ምስል፣ የብር መቋሚያ፣ የጥንታዊው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ታቦት ይነሳበት የነበረ መጎናፀፊያ፣ የአዲስ አበባን ካርታ የያዘ በጨርቅ ላይ የተሳለ ምስል፣ የሊቀ ጳጳሳት መቀደሻ አልባሳት፣ ከመዳብ የተሰራ መቅረዝ፣ በጨርቅ ላይ የተሳለ የአዲስ አበባ ካርታ፣ ከግሪክ፣ ከእየሩሳሌም እና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጽዋዎች፣ የመፅሀፍ ቅዱስን ትምህርት የሚገልጹ በቆዳ ላይ የተሳሉ ስዕሎች፣ ፓትሪያርኩ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ የሚቀመጡበት ዙፋን እና የተለያዩ ቅርሶች በዚህ ሙዚየም ውስጥ ይገኛሉ፡፡

 ይህ ሙዚየም የታሪክ ማስረጃ የሆኑ ቅርሶች የሚገኙበት ቢሆንም ጎብኚዎች በስፍራው ተገኝተው ሲጎበኙት አይስተዋልም፤ ብዙዎቻችንም በቤተ-ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚገኝ አናውቅም፡፡ በአገራችን የሚገኙ  ሙዚየሞችን መጎብኘት እና ታሪካችንን ማወቅ ባህላችን ማድረግ አለብን፡፡ ቀጨኔ መድኃኒዓለም ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ሙዚየም ህብረተሰቡ እንዲያውቀውና እንዲጎበኘው ቤተክርስቲያኑን የሚያስተዳድሩ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩት ይገባል፡፡ ሙዚየሞቻችን ማንነታችንን የሚያሳውቁ ስፍራዎች ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment