Friday, July 20, 2012


ቱሪዝም በዳዉሮ
ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ


የዳዉሮ ዞን  ከኢትዮጵያ ዉብ ገፅታ ማሳያዎች አንዱ ነዉ፡፡ ዞኑ በደቡብ ክልል የሚገኝ ሲሆን የዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ ትባላለች፡፡ ታርጫ ገስጋሽ ነገር ግን በሚሌኒየሙ ከተወለዱ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ከሐዋሳ በ282 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በሻሸመኔ አድርገዉ በወላይታ ሶዶ የሚጓዙ ከሆነ 455 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ በሌላኛዉ መንገድ በጅማ አርገዉ የሚጓዙ ከሆነ ደግሞ በ479 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚያገኟት ከተማ ስትሆን ከተማዋ በየግዜዉ እያስመዘገበች ባለዉ እድገት ሳቢያም የብዙዎችን ትኩረት ስባለች፡፡

      በደቡብ ከጋሞ ጎፋ በምዕራብ ከኮንታ ልዩ ወረዳ በሰሜን ምዕራብ ከኦሮምያ ክልል በሰሜን እስከ ሰሜን ምስራቅ ከከንባታ ጠንባሮ ዞን በምስራቅ ከወላይታ ዞን ይዋሰናል፡፡ ከሰሜን ምዕራብ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በጎጀብና በኦሞ ወንዞች ተፋሰስ የተከበበዉ የዳውሮ ዞን የብዙ እሴቶች ማዕከል እና እንብርት ነዉ፡፡ ከአምስት በላይ በሆኑ ብሄረሰቦች መከበቡ ዳውሮን ልዩ የባህል አምባ ያደርገዋል፡፡

Wednesday, July 4, 2012


ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ገመገመ

ብዙዎቹ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡

ፓርኮችን በመጎብኘት ረገድ የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የባህል ልውውጥና ግንኙነት አፈጻጸሙ 108 በመቶ ሆኗል….

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በመገምገም የአፈጻጸም ልኬቱን በቁጥርና በመቶኛ አስቀምጧል፡፡ በዘጠኝ ወሩ አስራ ሶስት የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ሲሆን አስራ አራት ለማከናወን በመቻሉ ከእቅዱ ያለፈና 108 በመቶ የሆነ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ብቻ 9 የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታስቦ 11 ለማከናወን ሲቻል አንድ ባህላዊ የሙዚቃ ኪነት ቡድን በውጪ ሃገር ትርኢት ለማቅረብ በታሰበው መሰረት በህንድ ሶስት ከተሞች ትርኢቱን በማሳየት ሃገሪቱንና የህዝቦቿን እሴት በሚገባ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡

በዘጠኝ ወራቱ አፈጻጸም የቱሪስቶች ቁጥር 474,249 ደርሷል፤ ይህም ከእቅዱ አንጻር 88 በመቶ ሲሆን በቋሚ ኤግዚቢሽን ጎብኚዎች ረገድ 106,084 የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች በብሄራዊ ሙዚየም የቋሚ ኤግዚቢሽን የማስጎብኘት እድል ተፈጥሯል፡፡ በሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ገረድም በተለይም ፓርኮችን በመጎብኘቱ አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን 30,110 የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች የሃገሪቱን ፓርኮች ጎብኝተዋል፡፡ የሴቶቹ ቁጥር ደግሞ 12,405 ነው፡፡ ይህ ቁጥር 42,246 የውጪ ጎብኚዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ፓርኮችን የመጎብኘት ባህል እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ በአለፍት ዘጠኝ  ወራት ከቱሪስቶች 371,811,216 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ የአንድ ቱሪስት አማካኝ የቆይታ ግዜ 6.5 ሲሆን የቀን ወጪው ደግሞ 120.6 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ያገኘንው መረጃ ያመላክታል፡፡