Friday, July 20, 2012


ቱሪዝም በዳዉሮ
ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ


የዳዉሮ ዞን  ከኢትዮጵያ ዉብ ገፅታ ማሳያዎች አንዱ ነዉ፡፡ ዞኑ በደቡብ ክልል የሚገኝ ሲሆን የዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ ትባላለች፡፡ ታርጫ ገስጋሽ ነገር ግን በሚሌኒየሙ ከተወለዱ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ከሐዋሳ በ282 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በሻሸመኔ አድርገዉ በወላይታ ሶዶ የሚጓዙ ከሆነ 455 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ በሌላኛዉ መንገድ በጅማ አርገዉ የሚጓዙ ከሆነ ደግሞ በ479 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚያገኟት ከተማ ስትሆን ከተማዋ በየግዜዉ እያስመዘገበች ባለዉ እድገት ሳቢያም የብዙዎችን ትኩረት ስባለች፡፡

      በደቡብ ከጋሞ ጎፋ በምዕራብ ከኮንታ ልዩ ወረዳ በሰሜን ምዕራብ ከኦሮምያ ክልል በሰሜን እስከ ሰሜን ምስራቅ ከከንባታ ጠንባሮ ዞን በምስራቅ ከወላይታ ዞን ይዋሰናል፡፡ ከሰሜን ምዕራብ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በጎጀብና በኦሞ ወንዞች ተፋሰስ የተከበበዉ የዳውሮ ዞን የብዙ እሴቶች ማዕከል እና እንብርት ነዉ፡፡ ከአምስት በላይ በሆኑ ብሄረሰቦች መከበቡ ዳውሮን ልዩ የባህል አምባ ያደርገዋል፡፡


      4403 ስኩዌር ካሬ ኪ.ሜትር የቆዳ ስፋት ያለዉ የዳውሮ ዞን የተሰባጠረ መልከአ-ምድር ያለዉ ሲሆን ወይና ደጋማዉ የአየር ንብረት ሰፊዉን ድርሻ ይይዛል 38 በመቶ ቆላማ እና 21 በመቶው ደጋማ ነዉ፡፡ ከዝቅተኛዉ የኦሞና የዝግና ወንዞች ምድር እስከ ከፍተኛዉ የቱታ በተጫ ወረዳ ከ500-2820 ሜትር ከባህር ወለል በላይ የሚደርስ መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ አለዉ፡፡ በየዓመቱ 2.9 በመቶ እድገት ያሳያል የተባለዉ የዞኑ የህዝብ ብዛት በ2002 ዓ.ም አጠቃላይ የዞኑ ህዝብ ብዛት 539 ሺ በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡



ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ

ከሃያ ዘጠኝ የሚበልጥ አጥቢ የዱር እንስሳትን በዉስጡ የያዘዉ እና ማራኪዉ የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ መጥቷል፡፡ በደቡብ ክልል ከሚገኙ አምስት ብሄራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነዉ የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ በዳዉሮ ዞን አሰራርና ቶጫ ወረዳዎች የሚገኘዉን ሰፊ ጋሻ መሬት እና አረንጓዴ ዉብ ሰፊ ደን ጨምሮ እስከ ኮንታ ልዩ ወረዳ የሚዘልቀዉን የጨበራ ጩርጩራን ደን ያካተተ ነዉ፡፡

በፓርኩ ዝርያዉ እየተመናመነ የመጣዉ የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ እንደ ጎሽ ዲፋርሳ ከርከሮ ሳላ እና አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት ነዉ፡፡ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ በደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ስሙ የሚነሳ ፓርክ ነዉ፡፡ በፓርኩ ዉስጥ የሚርመሰመሱት እና እነኚህን ጥቅጥቅ ደኖች የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ዝግና የተባለዉ ታላቅ ወንዝ የፓርኩን ክፍል ለሁለት የከፈለ ወንዝ ነዉ፡፡ በፓርኩ ደን ዉስጥ ከአምስት ያላነሱ ሃይቆችም ይገኛሉ፡፡ ጨበራ ጩርጩራ ለአረንጓዴ ቱሪዝም ማሳያ የሚሆን የሃገሪቱ ታላቅ መስኽብ ነዉ፡፡

የሶሎ ተፈጥሮ ደን

ቃራዎ ከተማ የሶሎ በጌና ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ ከከተማዋ 20 ኪ.ሜ ገደማ ከጋዞ ኮይሻ ቀበሌ ምስራቃዊ ጫፍ ጀምሮ ወደ ሰሜን የተዘረጋ ዉብ ደን ነዉ፡፡የብዙ ብዝሃ ህይወት መጠጊያ የሆነዉ የሶሎ ደን ዝርያቸዉ ብርቅ የሆኑ ልዩ የዛፍ እና የአዕዋፍ ዝርያዎችን የያዘ ነዉ፡፡ እንደ ጥቁር እንጨትና ኮሶ ያሉ ዛፎችም ይገኙበታል፡፡ ይህ ደን ተጠብቀ በስፋት ቢተዋወቅ የብዙ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል፡፡

ከሃላላ ካብ (ሃላለ ኬላ) እስከ ካቲ ሁሉቋ

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ጭምር እየሳበ የመጣዉ ረጅሙ የንጉስ ሃላላ ድንጋይ ካብ መገኛ ዳዉሮ ዞን ነዉ፡፡ ሃላላ ካብ ከ175 ኪ.ሜትር በላይ ርዝመት ያለዉና አሰራሩ አስገራሚ የሆነዉ ይኽዉ የድንጋይ ካብ ከቀደምት የዳዉሮ ነገስታት መናገሻ ወይም ስርዓተ-መንግስት የሚያከናዉኑበት ካቲ ጋዷ በዋናነት በሎማ ወረዳ ሲገኝ የመንፃት ስርዓት የሚፈፀምበት ዋሻ ሌላዉ የቱሪስት መስኽብ ነዉ፡፡ በዳዉሮ ዞን አስራ አራት የሚደርሱ የተፈጥሮ ዋሻዎች ቢኖሩም ካቲ ሁሉቆ ዋሻ ግን በርካታ ልዩ የሚደርጉት ነገሮች አሉ፡፡ ከስያሜዉ ብንነሳ ካቲ ሁልቆ ማለት የንጉስ የመንፃት ስረዓት የሚፈፀምበት ማለት ነዉ፡፡ ዋሻዉ በሎማ ወረዳ ሸምቢ ቀበሌ ሻሌ በተባለ ልዩ ቦታ የሚገኝ ሲሆን ከዛሬ 242 ዓመት በፊት ከ1757-1782 ዓ.ም ዳዉሮን ሲያስተዳድሩ በነበሩ ንጉስ ሃላላ ዘመን የተሰራ ንጉሱ እራሳቸው ይጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ የካቲ ሁሉቆ ዋሻ መግቢያና መዉጫ በር ያለዉና የንጉስ ሃላላ ባህላዊ የመንፃት ስነ-ስርዓት ያከናወኑበት ዋሻ በመሆኑ በበለጠ ስሙ ጎልቶ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡

      የዋሻዉ የላይኛዉ መግቢያ በር ገደላማ ሆኖ ስፋቱ 29 ሜትር ቁመቱ ደግሞ 12 ሜትር ነዉ፡፡ የታችኛዉ መዉጫ በር ደግሞ ሜዳማ ሆኖ ስፋቱ 46 ሜትር ቁመቱ ደግሞ 21 ሜትር ነዉ፡፡ ዉስጥ ለዉስጥ ስልሳ ዘጠኝ ሜትር ርዝመት ሲኖረዉ ከአንዱ ግድግዳ እስከ ሌላዉ ያለዉ የዉስጥ ስፋት ሀያ ስምንት ሜትር ነዉ፡፡ ከወለሉ እስከጣራዉ ደግሞ 7 ሜትር ርዝመት አለዉ፡፡

 የዳዉሮ ዞን ከአስር የሚበልጡ ፍል ዉሃዎች ፏፏቴዎች ትክል ድንጋዮች የተፈጥሮ ዋሻዎች ጥንታዊ ቤተ መንግስቶችና አበያተ ክርስቲያናት እና ሌሎችም መስኸቦች በሚገባ መልማት እና መተዋወቅ ከቻሉ ለሃገሪቱ ቱሪዝም ልማት ሌላ ተጨማሪ አቅምን መፍጠር ይችላሉ፡፡

2 comments:

  1. ሃላላ ካብ ከ175 ኪ.ሜትር በላይ ርዝመት ያለዉና አሰራሩ አስገራሚ የሆነዉ ይኽዉ የድንጋይ ካብ ከቀደምት የዳዉሮ ነገስታት መናገሻ ወይም ስርዓተ-መንግስት የሚያከናዉኑበት ካቲ ጋዷ በዋናነት በሎማ ወረዳ ሲገኝ የመንፃት ስርዓት የሚፈፀምበት ዋሻ ሌላዉ የቱሪስት መስኽብ ነዉ፡፡

    ReplyDelete