Saturday, March 31, 2012

ዜና


ዜና
       የስልጤ ዞን 6ኛው የቋንቋ፣የታሪክና የባህል ሲምፖዚየም በወራቤ ከተማ በድምቀት ተካሄደ፡፡

ዜና፡- ሀሚኮ

ሐራ ሸይጣን ሐይቅ-ስልጤ
Haro Shetan lake


መጋቢት 23 ቀን 2004 ዓ.ም በወራቤ ለስድስተኛ ግዜ የተካሄደው ሲምፖዚየም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡበትም ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ወ/ሮ ራውዳ ሲራጅ በስልጥኛ ቋንቋ እደገት ዙሪያ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን ቋንቋው እንዳያድግ ሳንካ ተብለው ለጥናቱ በተዘዋወሩበት ወቅት ከብሄረሰቡ ሽማግሌዎች የተሰነዘሩትን አስተያየት ተቀብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በስልጤ ዞን የማይዳሰሱ ቅርሶች ዙሪያ በወ/ሪት ነኢማ አብዱራሃማን መሪነት የቀረበው ጥናትም በወፍ በረር ዞኑ ያሉትን የቅርስ ሃብቶች ያሳየ ነበር፡፡ በስልጤ ብሄረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ሥረዓት ዙሪያ አቶ ሸርፈዲን ሰርሞሎና አቶ ነስሮ አለሙ ያቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡

 በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል የአረብኛ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የነበሩ እስላማዊ ሱልጣኔት ላይ ሰፊ የታሪክ ጥናት በማጥናት የሚታወቁት አቶ መሃመድ ሰይድ መርተውታል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሳኒ ረዲ

"በስልጤ ባህል፣ቋንቋና ታሪክ ላይ ለሚያጠኑ እና ለሚደክሙ ባለሙያዎች ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና ሊሰጥ፣ሊሸለሙ ይገባል ….በቀጣይም ለዚህና ይህን መሰል ለሆኑ ተግባራት ቦርድ መቋቋም አለበት "ብለዋል፡፡

፡፡

Monday, March 26, 2012

ጡማኖ እና ፋቂሳ

ጡማኖ እና ፋቂሳ
ቴላሞ የጡማኖ  መታሰቢያ
sidma tomano memoraial
የጡማኖ መካነ መቃብር እና የሃገር ሽማግሌው አቶ ሲዳሞ ቢረጋ

ከለኩ ከተማ በስምንት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው ቴላሞ ነው፤ ቴላሞ የሲዳማ አድባር ነው ሲሉ የሃገር ሽማግሌዎቹ ይገልጻሉ፡፡ አረንጓዴ ምድር ምን ማለት እንደሆነ በቴላሞ ቅጥር ግቢ ያሉት ሃገር በቀል ግዙፍ የዛፍ ዝርያዎች ለትውልድ የቆሙ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መልከአ-ምድራዊ ውበቱ ይማርካል፤ ከደኑ መሃል በአጥር የተከበበ አንድ ቅጥር አለ፤ በዚህ ቅጥር ውስጥ የሲዳማ ነገድ አባት የሆነው የጡማኖ መቃብር ይገኛል፡፡ በስፍራው በየእጽዋቱ ስር የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች ይገኛሉ፤ እንደ አካባቢው ሽማግሌዎች ገለጻ እነዚህ የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች መቃብሮች ናቸው፡፡
ሲዳሞ ቢራጋ የሃገር ሽማግሌ ናቸው፤ በየግዜው ለተለያየ ጉዳይ ወደ ቴላሞ ይመጣሉ፤ ይህንን ስናጠናቅር በስፍራው ያገኘናቸውም ለተመሳሳይ ዓላማ በቴላሞ ውብ ቅጥር ግቢ ለውይይት አረፍ እንዳሉ ነው፡፡ የሲዳማ የሃገር ሽማግሌዎች የሚለብሱትን ባህላዊ አለባበስ የለበሱት አቶ ሲዳሞ ቢራጋ ስፍራውን በሚመለከት አንዳንድ ጥያቄዎችን ስናቀርብላቸው በማራኪ አተራረክ ለዛ መልሰውልናል…መነሻችን ደግሞ ቴላሞ ምንድን ነው የሚል ነበር አቶ ሲዳሞ በተረጋጋ ሁኔታ ረጃጅም የቅጥሩ ዛፎች ላይ አይናቸውን ተክለው አብራሩልን….
 

Monday, March 19, 2012

ዜና
የአዊ የፈረስ ትርኢት-ለቱሪዝም
ዜና-ሀገሬ ሚዲያ

አዊ ባንጃ ወረዳ
awi festival
ፈረስ ለአዊ ሁለንተናው ነው….ለእርሻ ስራው ጉልበቱ በመሆኑ ይወደዋል….በክፉም ሆነ በደግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መጓጓዣ ትራንስፖርቱ ነውና ሁሌም ያስፈልገዋል….አዊ በደስታውም ቢሆን በዓሉን የሚያደምቀው በፈረስ ነው….ሰርጉ ጭምር በፈረስ ይዋባል፤ሞቶ ወደ መቃብር ሲሸኝም ፈረስ መሸኛው ነው…..
በ1933 ዓ.ም በመሰባሰብ አብሮነትን በተደራጀ መልኩ አንድ ያለው የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ዘንድሮ 71ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ጠላትን ከሃገር ለማስወጣት አንድነትን ለመፍጠር በሚል በአንድ የተደራጀ ነበር ያኔ….. ዛሬ ደግሞ የአዊን እሴት ለማስተዋወቅ በአንድ ያበረ አንድ ህብረት ሆኗል፡፡
አቶ አቡኑ ይግረም ይባላሉ የወቅቱ የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀ-መንበር፤22,275 አባላት ያሉት ይህ ማኀበር በየዓመቱ ዓመታዊ በዓል ያከብራል፤ይህ በዓል የአዊ ፈረሰኞች ቀን ይባላል፡፡ በዚህ የባህል አከባበር ደንብ አመታዊው በዓል ከወረዳ ወደ ወረዳ እየተዘዋወረ የሚከበር ነው፡፡ አዊ ዞን አስር ወረዳዎች አሉት፤አንድ ወረዳ በአስር አመት አንዴ የአዊ ፈረሰኞች ቀንን የማዘጋጀት እድል ይገጥመዋል፡፡

Thursday, March 15, 2012


ዜና

ዓመታዊው የበርሊኑ የቱሪዝም ንግድ ትርኢት በደማቅ ሥነ-ሥረዓት  ተካሄደ

ኢትዮጵያ ከእስከዛሬዎቹ በተሻለ እራሷን ያስተዋወቀችበት ዝግጅት ነበር……

ዜና-ሃገሬ ሚዲያ

በየዓመቱ በጀርመን በርሊን የሚደረገው ዓለም አቀፉ የበርሊን የቱሪዝም ትርኢት ዘንድሮም  ለ46ኛ ግዜ በበርሊን ከማርች 7 እስከ11 2012 በድምቀት ተከናውኗል፡፡

ከ185 ሀገራት በላይ በተሳተፍበት በዚህ የቱሪዝም ንግድ ትርኢት ሀገራቱን የወከሉ ከ11 ሺ በላይ የአስጎብኚ ወኪልነትና የጎዞ ስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል፡፡ በዚህ ዝግጅት የተለያዩ የዓለም ሀገራት ይወክለናል በሚሉት የቱሪዝም ሃብታቸው እራሳቸውን እየገለጹ መስኽብ ሃብታቸውን በማስተዋወቅ  በቱሪዝም ገበያው ውስጥ ሲፎካከሩ ሰንብተዋል፡፡
በዚህ ዓለም አቀፋዊ የቱሪዝም የንግድ ትርኢት ላይ ኢትዮጵያም ተካፋይ ስትሆን እነ ዶክተር ብረሃኔ አስፋው በሚመሩት ዘርፍ ሁለት ቅሪተ አካላትን በርሊን ይዛ ገብታለች፡፡ አንደኛዋ ሉሲ ስትሆን ሌላኛዋ ቅሪተ አካል እ.ኤ.አ 2011 ዓ.ም በሳይንስ መጽሄት ላይ በመውጣት የዓለምን ትኩረት የሳበችው 4.4 ሚሊዮን ዓመት እድሜን ያስቆጠረችው ቅሪተ አካል ናት፡፡

በበርሊኑ ትርኢት ተሳታፊ የነበሩና ኢትዮጵያን ወክለው ከተገኙ አስጎብኚዎች መካከል አንዳንዶቹ በስፍራው ተገኝቶ ላነጋገራቸው ለጀርመኑ ሬድዮ ጋዜጠኛ ከታክስ ጋር በተያያዘ ያላቸው ቅሬታ እንዳልተፈታ ገልጸውለታል፡፡

በሌላ በኩል የዘንድሮ የበርሊን የቱሪዝም ትርኢት የተለየ ክስተት የነበረው በአዘጋጅ አካላቱ የተዘጋጀውና ሀገራት ስለሃገራቸው ዲሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ አቋም ለጎብኚዎች መረጃ የሚሰጡበት መድረክ መዘጋጀቱ ሌላው አዲስ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ዓለም አቀፋዊ የቱሪዝም ትርኢት ላይ አማራ ብሄራዊ ክልል ባህል ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ ሰፊ ዝግጅት አድርጎ መሳተፉን የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡      

Monday, March 5, 2012

ዜና

የመጀመሪያው የባህል ኢንዱስትሪ የንግድ ፌስቲቫል ከነገ ማክሰኞ የካቲት 27-2004 ዓ.ም
ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ከአርባ በላይ የክልል ተሳታፊዎች ለዝግጅቱ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ዝግጅቱ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሮክተሬት የተዘጋጀ ነው፡፡
ዜና-ሀገሬ ሚዲያ
   በዓይነቱ የተለየ የባህል ኢንዱስትሪ ልማትን ያቀፈ የመጀመሪያው የባህል ኢንዱስትሪ የንግድ ፌስቲቫል ከነገ ማክሰኞ የካቲት 27 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ዝግጅቱን ለመካፈል የክልል ተሳታፊዎች አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች በድምሩ ከመቶ በላይ ተሳታፊዎች ሲሳተፉ፤ ከአምስት ኪሎ እስከ አራት ኪሎ ባለው ቦታ የሚዘረጋው ይህ ለአራት ቀናት የሚቆየው ዝግጅት የባህል ኢንዱስትሪ ምርቶች የሚቀርቡበት ንግድ ትርኢት፣ የባህል አልባሳት ሾው እና ሲምፖዚየም ያካተተ ሲሆን ያዘጋጀው በኢፊዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሮክተሬት ነው፡፡
   ነገ የሚከፈተው ይህ ዝግጅት በነገው ዕለት በብሄራዊ ሙዚየም አዳራሽ በጉዳዩ ላይ የሚመክር ሲምፖዚየም እንደሚያስተናግድም  አቶ አካሉ ወልደማርያም  በኢፊዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሮክተሬት አስተባባሪ ገልጸውልናል፡፡

Sunday, March 4, 2012

ቅርስ

የኢማም ሱጋቶ መኖሪያ ቤት…..
ወራቤ የስልጤ ዞን ርእሰ ከተማ ናት፡፡ ስልጤ ዞን በስራ ወዳድነታቸው የሚታወቁት የስልጤ ብሄረሰብ ምድር ነው፡፡ 2537.50 ኪ.ሜትር ስኩዌር የሚሰፋው የስልጤ ዞን ከ950.000 በላይ ህዝብ ይኖርበታል፡፡
ምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በስልጤ ዞን ከሚገኙ 8 ወረዳዎች አንዱ ነው፤ይህ ወረዳ ከዞኑ መዲና ከወራቤ 83 ኪ.ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሌራ የምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ማእከል ከተማ ናት፡፡ በወረዳው በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ በአጭሩ የኢማም ሱጋቶ ታሪካዊ ቤትን እንቃኝ…..
silta zone attraction

   ኢማም ሱጋቶ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ስልጤንና አካባቢውን ጎጎት የሚባል አደረጃጀት በመፍጠር ያስተዳድሩ የነበሩ በሳል መሪ ነበሩ፤ ከእኒህ መሪ ታሪክ ጀርባ ብዙ ያልተወራላቸው የጀብድ ታሪኮች እንዳሉ በአፍ ከሚወረሱ የአበው የታሪክ ሽግግሮች ለመረዳት ይቻላል፡፡
ኢማም  ሱጋቶ ዘይኔ በአካባቢው ላይ የሚቃጡ ግጭቶችንና ጥቃቶችን በመመከት በጦረኝነታቸው የሚታወቁ ጀግና መሪ ናቸው፤ስልጤዎች ይህንን ጀግንነት አድንቀው ለኢማም ሱጋቶ አዚመዋል፣ተቀኝተዋል፡፡ ከጀብድ ተግባራቸው ጋር አብሮ ለሚነሳው ፈረሳቸው ጭምርም ቅኔ ቀርቦለታል፡፡
ኢማም ሱጋቶ ዘይኔ ከስልጤ አካባቢዎች በአለፈ ሃላባ እና ሃድያ ጭምር ያስተዳድሩ እንጂ እንደ መናገሻ ማእከላቸው ሆኖ ያገለገለውን የሚያምረውን መኖሪያ ቤታቸውን ያነጹት በምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ነው፡፡
ባለ ፎቁ የኢማም ሱጋቶ መኖሪያ ቤት ከሌራ ከተማ 4 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ ዱና ከሚባለው ስፍራ ይገኛል፡፡ በተዋበ አረንጓዴ ዙሪያ ገባ ተጅቦ ያረፈው ይህ ባለ አንድ ፎቅ ህንጻ ቤት በዙሪያው ያሉ እድሜ ጠገብ ዛፎች አሳምረውታል፡፡ የቤቱ አሰራር ከጅማው አባ ጅፋር ቤተ መንግስት አስተናነጽ ጋር መመሳሰል ይታይበታል፡፡
ይህ አንድ ምእት ዓመት እድሜን ያስቆጠረው ቅርስ የስልጤዎች ብቻ እሴት ሳይሆን የሃገርም ቅርስ ነው፡፡ ከቤቱ ጀርባ የቤት አሰራሩ ጥበብ ከዚያም ሲያልፍ የኢማሙ ሱጋቶ የጀግንነት ታሪኮችና ታሪኮቹ የፈጠሩት ሥነ-ቃል አንዱን መስህብ ብዙ ያደርገዋል፡፡