Tuesday, August 26, 2014


         አሸንዳ - የሰሜናዊቷ ኮከብ ከተማ ኮከብ ኩነት

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የጾመ ፍልሰታ ፍጻሜን ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ የአሸንዳ ባህላዊ ጨዋታ መጠሪያ የኾነው ቄጤማ ረዥምና ለምለም እንደ ቅጠል ሰፋ ያለ ሲሆን ቁመቱ 80 እስከ 90 . ይኾናል፡፡

የአሸንዳ በዓል በትግራይ ብሔራዊ ክልል የሚከበር በሀገራችን ከሚገኙ ኩነቶች አንዱ ነው፡፡ አሸንዳ ጥንታዊና የልጃገረዶች ባህላዊ በዓል ነው፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ በ783 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የክልሉ መዲና መቐለ በየዓመቱ የምታስተናግደው ይህ ፌስቲቫል ከትግራይ ወጣቶች ባለፈ ጎብኚዎችም በጉጉት የሚጠብቁት ባህላዊ ትዕይንት ሆኗል፡፡
   

የአሸንዳ ባህላዊ ጨዋታ መሰረት ኃይማኖታዊ ነው፡፡ መንፈሳዊ መነሾውም ከሔዋን፣ ከድንግል ማርያም ልደት እና ትንሳኤ፤ ከክርስቶስ ትንሳኤ ከመጥመቁ ዩሐንስ አንገት መቆረጥና ከዘመን መለወጫ ታሪኮች ጋር ተያይዞ ይገልፃል፡፡ የአሸንዳ ባህል አከባበር ከዘመን መለወጫና ከቅድስት ማርያም ትንሳኤ ጋር የተያያዘው ታሪክ ከሌሎች ይልቅ ሚዛኑ የደፋ ነው፡፡ በመሆኑም አሸንዳ ከነሐሴ 16 - 21 ቀን ድረስ ይቆያል፡፡

የ2006 ዓ.ም የአሸንዳ በዓል ከነሐሴ 15-18 በመቐለ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ መቐለ በልጃገረዶች ውበት የፈካችበት ታላቅ ኩነትም ሆኖ አልፏል፡፡ ነሐሴ 15 ቀን ከሰዓት በኋላ በመቐለ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የተበሰረው የአሸንዳ በዓል የጎዳና ላይ ትዕይንት ከአጼ ዩሐንስ ቤተ መንግስት ጀምሮ መቐለ አሮጌው ስታዲየም የተጠናቀቀ የካርኒቫል ዝግጅት ነበር፡፡

በእርግጥ አሸንዳ የመቐለ ተስፋ የሆነ ኩነት ነው፡፡ ተወላጆቿን በዓይነ ስጋ ልታይ የምትችልበት ታላቅ አጋጣሚም ነው፡፡ በሌላ በኩል መቐለ የአሸንዳ ዋና ከተማ ትሁን እንጂ ከትግራይ ክልል ሰባት ዞኖች አምስቱ በታላቅ ድምቀት የሚያከብሩት ክልላዊ በዓል ነው፡፡ ስድስተኛው ዞን ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ለማክበር እናቶች በርካታ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ከበደ አማረ ገልጸውልናል፡፡

 

አሸንዳ እንደ መንፈሳዊ አስተምሮት ሴቶች በድንግል ማርያም አማካይነት እኩልነታቸው የተመለሰበትና ከጨለማ ወደ ብርሀን የተሸጋገሩበት እለት ነው፡፡ የትግራይ ልጃገረዶችም የአሸንዳን በዓል በጣም በታላቅ ናፍቆት ይጠብቁታል፡፡ የዚህ ናፍቆት መገለጫም አንዱ ማሳያ ነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በመቐለ አሮጌው ስታዲየም የነበረው ደማቅ ዝግጅት ነው፡፡

ዝግጅቱን ከመቐለ ክፍለ ከተሞች እና ከተለያዩ ዞኖች የመጡ እንስት የባህል ተጫዋጮች በማይማዊ ትዕይት አጅበው አድምቀውታል፡፡ መቐለ በፍጹም ሐሴት ውስጥ የነበረችባቸው ቀናት ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ማንም ቢያየው ትዝታውን ከውስጡ ሊፍቅ አይቻለውም፡፡

የመቐለ ስታዲየሙ የነሐሴ 16 ቀን ትዕይንት ሁሉም የአሸንዳ ጨዋታ አቅራቢዎች ያስዋቡት ቢሆንም በአቀራረብ ረገድ የማዕከላዊ ዞኖቹ ማለትም የአክሱምና አካባቢው ልዑካኖች የተዋጣለት አቀራረብ ይዘው ነበር፡፡ እኒህ የቡድን አባላት በማይም ትዕይንት አያሌ ባህላዊ እሴቶችን ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡

አሸንዳ የሚነግስበት የመቐሌው ሮማናት አደባባይ ነሐሴ 16 ቀን ምሽት ጠጠር መጣያ ቦታ አልነበረውም፡፡ ይልቁንስ በልጃገረዶች ውበት ተጥለቅለልቆ የዜማቸው ድምጽ ሰማይ የደረሰበት ልዩ ስፍራ ሆኗል፡፡ ከሁሉም የመቐለ አቅጣጫዎች በቡድን በቡድን ሴቶች ከበሯቸውን እየመቱ እንደ ወንዝ ፈሰው እንደ ውቅያኖስ የሰመጡበት ባህር ሆኗል፤ ሮማናት አደባባይ መቐለ፤

ይህ ዘመን ያስቆጠረ ባህላዊ ትዕይንት የመቐለ ጌጥ በመሆን ዳግም ያንሰራራው ከ1995 ዓ.ም በኋላ ነበር፡፡ አሁን ሊቆም የማይችል የህዝብ ሀብት ነው፡፡ ማንም ሰው ቢያየው ዓመቱ መቼ ነው በሚል በጉጉት ዳግም የሚጠብቀው ኩነት ለመሆን በቅቷል፡፡ መቐለ ትልቁ እሴቷ አሸንዳ ነው፡፡

አሸንዳ የዜማ ብቻ ሳይሆን የውበትም በዓል ነው፡፡ የትግራይ ሴቶች ለጨዋታው የሚያስፈልጉ አልባሳትና ጌጣጌጥ የማሟላት ቅድመ ዝግጅት ለበዓሉ ሁለት ሳምንት አካባቢ ሲቀረው ጀምሮ ያከናውናሉ፡፡ በባህላዊ አልባሳት የደመቁ ማለትም /በተጠለፈ ቀሚስ/፣ ነጠላ፣ መቀነትና ጌጣጌጦች፣ መስቀል፣ ድሪ፣ አምባር፣ ድኮት ትልቅ ቀለበትና ጉትቻ፣ ኩል ወዘተ በማድረግ በተዋበ መልኩ አምረው ያደምቁታል፡፡ ውበት ከጎዳና ላይ የሚፈስበት፤ ኪነት በአደባባይ የሚቀርብበት ልዩ በዓል አሸንዳ፡፡

መቐለ ለአሸንዳ ወደር የለሽ መዲና ናት፡፡ ለውጪና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በቂ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ የሚገኝባትና ምቹ የአየርና የየብስ ትራንፖርት የሚገኝባት መሆኗ በየዓመቱ እንግዶቿን በነሐሴ አጋማሽ ለመቅጠር ያስችላታል፡፡ አሸንዳ በጎዳና ላይ ጭምር የሚቀርብ የጭፈራ ትዕይንትን ያካተተ መሆኑ ይበልጥ ሳቢ አድርጎታል፡፡ 

አሁን አሸንዳ በሀገራችን ከሚካሄዱ የፌስቲቫል ቱሪዝም ምርቶች አንዱ ሆኗል፡፡ የዘንድሮ የአሸንዳ በዓል ድምቀት መቐለ ለአሸንዳ ትኩረትን ትሰጥ ዘንድ ግድ ይላታል፡፡ እኛም መቼ ይሆን ዳግም ትግራይ ዘልቀን እንደ ጎብኚ መቐለ ላይ የሚደገሰውን ድግስ ዳግም የምንታደመው በሚል እንናፍቃለን፡፡ የሚያውቁት ሀገር እንዲናፍቅ አሸንዳን በመቐለ ለ2007 ቀጠሮ ይያዙ፡፡

No comments:

Post a Comment