Tuesday, June 2, 2015



በአፋር ክልል 3.3-3.5 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠረ የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካል ተገኘ
ኢትዮጵያ ለሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ቅሪተ አካላት የተገኙባት አገር በመሆኗ በሰው ዘር ምንጭነት (Cradle of Human kind) በመላው ዓለም ትታወቃለች፡፡እስካሁን ከተገኙ ከሀያ የማያንሱ የቅድመ ሰው ዝርያዎች መካከል አስራ ሶስቱ መገኛቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡


አዲሱ ቅሪተ አካል የተገኘው በኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶ/ር ዩሐንስ ኃይለ ስላሴ በሚመራው አለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በተከናወነው በወራንዞ ሚሌ የቅድመ ታሪክ ጥናት ፕሮጀክት ነው፡፡
ግኝቱ በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ ቡርተሌና ዋይታሌይታ በመባል በሚታወቁት አካባቢዎች የተገኘ ሲሆን ቅሪቶቹም ሁለት የላይኛው መንጋጋና ሁለት የታችኛው መንጋጋ ናቸው፡፡ ቅሪቱ አውስትራሎፒቴከስ ደይረመዳ (Australopithecus deyiremeda) የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡ ስያሜውም ከሁለት አፋርኛ ቃላት የተወሰደ ሲሆን ‹‹ደይ›› ማለት ቅርብ ሲሆን ‹‹ረመዳ›› ማለት ደግሞ ዘመድ የሚለውን ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ ስያሜው በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች የቅድመ ሰው ዝርያዎች የበለጠ የቅርብ ዘመድ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡
ዝርያው በወቅቱ በስፍራው ከነበረው አውስትራሎፒቴከስ አፋረንሲስ በመባል ከሚታወቀው ከድንቅነሽ (ሉሲ) ከጥርሶቹ መጠንና በመንጋጋዎቹ ቅርፅ የተለየ በመሆኑ ቅሪተ አካሉን ወደ አዲስ የቅድመ ሰው ዝርያ ሊመደብ መቻሉን ግኝቱ ለሰው ዘር አመጣጥ ጥናት አዲስ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ኢትዮጵያ በእርግጥም የሰው ዘር ምንጭ እንደሆነች ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሆነና የቱሪዝም እድገት እንዲጨምርና ለወደፊቱ ያሉንን የቅድመ ታሪክ ቦታዎችን እንዴት ነው አስፋፍተን የምንጠቀምበት እንዴት የገቢ ማስገኛ ማድረግ አንችላለን የሚለውን ትኩረት ሰጥተን እንድንሰራ ያደርገናል በማለት ዶ/ር ዩሐንስ ኃይለስላሴ ገልፀዋል፡፡
ግኝቱ ለመገናኛ ብዙሃን ሲታወጅ በስፍራው የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር ግኝቶቹ የሰው ዘር ምንጭነታችን የሚመሰክሩ ብቻም ሳይሆኑ ለሀገራችን የቱሪስት ፍሰት መጨመርና ለዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በቀጣይም ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ ሚ/ር መ/ቤቱ የሚጠበቀውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment