Tuesday, February 21, 2012


የጭልጋ ወረዳዋ 
ላዛ ደብረ መንክራት ባታ ማርያም ገዳም 

Gondar Chilga werda- laza mariyam
በአንደኛው የጭልጋ ወረዳ ማዶ የምትገኝ ድንቅ የቱሪስት መስህብ ናት፡፡ የላዛ ደብረ መንክራት ባዕታ ማርያም ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳ የምትገኝ ጥንታዊት ገዳም ስትሆን ገዳሟ ከአዘዞ መተማ በተዘረጋው የአስፋልት መንገድ ከወረዳው ከተማ አይከል ከመግባታችን 7 ኪ.ሜ በፊት ለከተማው ህዝብ ውሃ ከሚሳብበት /ከውሃ ልማቱ/ ከዋናው የአስፋልት መንገድ በስተቀኝ በኩል ከ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኃላ የሚያገኟት ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ ናት፡፡
ወደ ገዳሟ ሲደርሱ ገዳሟ ያረፈችበት ቦታና መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ ይማርካል፡፡ በገዳሟ የሚገኙ የአብነት ተማሪዎች ዝማሬና ድምጽ ይቀበልዎታል፡፡ ገዳሟ የተቋቋመችው በአፄ ይኰኖ አምላክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ በአሁኑ ሰዓት በገዳሟ  የሚያገለግሉ የዕድሜ ባለፀጋ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳን ገዳሟ በአፄ ይኰኖ አምላክ ዘመን መንግስት ብትቋቋምም ገዳሟ የተገደመችው በአፄ ጻዲቁ ዩሐንስ ዘመነ መንግስት እንደሆነ የሚያስረዱ አባቶች አሉ፡፡ የላዛ ደብረ መንክራት ባዕታ ማርያም ገዳም በውስጧ ጥንታዊ የሆኑ የብራና ጽሁፎችን፣ የብርና የወርቅ መስቀሎችን እንዲሁም በርካታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መፅሃፍት የሚገኙባት ጥንታዊትና ታሪካዊት ገዳም ናት፡፡

እንደ አካባቢው ማህበረሰብ እምነትና በርካታ ገዳሟን የሚያውቁ አባቶች እንደሚያስረዱት በገዳሟ በርካታ ተአምራቶች እንደተደረጉ ይነገራል፡፡
    በድርቡሽ ወረራ ወቅት 3 ጊዜ ድርቡሽ በመተማ እየዘለቀ እስከ ጎንደር ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን በሙሉ ሲያቃጥላቸው ደብሯን ለማቃጠል የመጣውን የጠላት ጦር በነጭ ንብ ተነድፎ በመመለሱ ደብሯ ሳትቃጠል ቀርታለች፤ከዚህ በተጨማሪም ደጅ አዝማች አቩ ቅልጣ የተባለ የጦር መሪ በላዛ ቦታ ማርያም ገዳም አውራ መንገድ ጦሩን አስከትሎ ነጋሪት እያስጎሰመ በሚካሄድበት ወቅት ደብሯ ሁካታ አትወድም ብሎ የደብሯ ቄስ ገበዝ ቢነግረው እስቲ ታጉራ ብሎ እንደሰደባት ከበቅሎው ተሸቀንጥሮ ወድቆ በገዛ ሰይፉ ተመትቶ ሞቷል የሚለው ሌላው የገዳሟ ታሪክ ነው ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ድረስ የመቃብር ቦታ ታጉራ መቃብር እየተባለ እንደሚጠራ የአካባቢው ማህበረሰብ ይናገራሉ፤
     ከጅብ ጋር ተያይዞ የሚነገረው ታሪክ ደግሞ በርካታ ምዕመናን ደብሯን እንዲጎበኙ ያነሳሳ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሰው በርሃብ ደክሞ በየቤቱ ሲያንቀላፋ አንድ ጅብ ከቤተክርስቲያኗ ቅድስት ገብቶ የነጋሪቱን ቆዳ በልቶ ቀዳዶ ጥሎ ሊወጣ ሲል ወገቡ ታስሮ እየተንቀጠቀጠ ከቤተክርስቲያኗ ሳይወጣ አድሮ ማለዳ የደብሯ ምዕመናን ቀጥቅጠው ገድለውታል፤ እነዚህ ሁሉ ታሪኮች ገዳሟ የብዙ ጎብኚዎችን ቀልብ እንድትስብ አድርጓል፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረበት ጊዜ አስፋህ ደበሳ የተባለ የኢጣሊያ ባልደረባ አያሌ ወታደር ይዞ መጥቶ የደብሩን ሕዝብ ለመያዝና ወታደር ለመመልመል እና ልዩ ልዩ ሥራ ለማሰራት በመጣ ጊዜ ሕዝቡ አስቀድሞ በማየት ደብሯ አካባቢ ከሚገኝ ጫካና ደን /ገዳሙ/ በገባ ጊዜ ከደብሩ ዙሪያ ያለውን ጫካና ደን በእሳት አቃጠለው በዚያን ጊዜ የእሳቱ ወላፈን ቤተክርስቲያኗን ሊበላው ነው ብሎ ለማጥፋት ወጣቱ ከጫካው ሲወጣ ከአንድ መቶ ሰው በላይ ወጣት ይዞ ወደ አውራጃው ከተማ ወደ አይከል ሲጓዝ ቲውድባ ከተባለው ተራራ ሲደርስ አንድ ቀይ ነገር ሰውን ተመስሎ በመንገድ ላይ ወጋኝ ብሎ በበነጋው ሞቶ ተቀብሯል፤
ሌላው በተለይም ለሃይማኖታዊ ቱሪዝም ትልቅ ስፍራ ካሰኛት አንዱ ገዳሟ ከተተከለችና ከተገደመች በኋላ በምስራቅ በኩል በቤተልሔሟ አካባቢ ጸበል ፈልቆ ድውያንን ሁሉ ስትፈውስ በመሰማቱና በማየቱ ከጎጃም ከበጌምድር፣ ከትግራይ እየተነሳ የሚመጣው ሕዝብ በርከት ያለ ስለሆነ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ በሽተኛ ስለአሰቀቀው ማሕበረሰቡ መክሮ ጸበሏን አጥፍቷት ነበር፡፡ በኋላ ጸበሏ ከነበረችበት ላይ አንዲት ስሟ የማይታወቅ እጽ እንጨት በክረምት ወራት ከሳሩ ጋር በቀለች፡፡ በመስከረም ወር ቤተክርስቲያኗን ለማጽዳት በወቅቱ የነበሩ የደብሯ መሪጌታ ቦታውን ሲመነጥሩ አንድ ባህታዊው ተሰውሮ እሷን እንጨት እንዳትቆርጣት አላቸው እርሳቸውም ሰምተው ይህችን እንጨት ከልለው ተዋት፡፡ ከዛ በኋላ እጿ አድጋ የባታ ቅጠል እየተባለች በአሁኑ ሰዓት ብዙ ድውያን እየፈወሰች ትገኛለች፤ቀደሞ የጠፋቸው ጠበል በ1949 ዓ.ም ከፈለሰ አለት ላይ ፈልቃ ዛሬም አብዛኛውን ሕሙማን ስትፈውስ ትገኛለች በማለት የወረዳው ባህልና ቱሪዝም መረጃውን አድርሶናል፡፡

3 comments:

  1. እባካቹህ እውነቱን ፃፉ።
    አንደኛ ቤተክርስቲያኗ ገዳም አይደለችም
    ሁለተኛ የተፃፉት ታምራቶችና ታሪኮች እንዲሁም መገለጫዎች የጎረቤት ቤተክርስቲያናት ታሪክ ናቸው።ለምሳሌ በሰይፉ የሞተው መኳንንት የአውራርዳ ማርያም ታሪክ የድርቡሹ ታሪክ የጃይድ ሚካኤል ታሪክ ናቸው በአጠቃላይ ከቤተክርስቲያኗ መገኛ ውጭ ሌላው ሁሉ ውሸት ነው።

    ReplyDelete
  2. ይህ መረጃ እውነት ነው የሚል እምነት አለን፡፡ የተገኘውም ከጭልጋ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ነው፡፡ መረጃውን እንደ ሚዲያ ለማስተናገድ ህጋዊ መብት ያለው እና መረጃ መስጠት የሚችለው ተቋም የሰጠነንን ተጠቅመናል፡፡ የተለየ ችግር ካለም ከየቤቱ የሚነሳውን ማረሚያ ሳይሆን ሃላፊነት የሚወስደውን አካል አስተያየት ነው ማስተናገድ የምንችለው፡፡ ለአስተያየቱ ግን እናመሰግናለን፡፡

    ReplyDelete
  3. ይህ መረጃ እውነት ነው የሚል እምነት አለን፡፡ የተገኘውም ከጭልጋ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ነው፡፡ መረጃውን እንደ ሚዲያ ለማስተናገድ ህጋዊ መብት ያለው እና መረጃ መስጠት የሚችለው ተቋም የሰጠነንን ተጠቅመናል፡፡ የተለየ ችግር ካለም ከየቤቱ የሚነሳውን ማረሚያ ሳይሆን ሃላፊነት የሚወስደውን አካል አስተያየት ነው ማስተናገድ የምንችለው፡፡ ለአስተያየቱ ግን እናመሰግናለን፡፡

    ReplyDelete