Tuesday, February 21, 2012

ተፈጥሮ


የእግዜርን አዳራሽ ማን ሰራው
አርባ ምንጭ ከተማ ስሟ ራሱ መስኸብ ነው፡፡ ከተማዋን የማያውቋት ብዙ ሰዎች ስሟ ሲጠራ በምናባቸው የሚስሉት ቱሪዝምን ነው፡፡ ውበትና ተፈጥሮ ይታያቸዋል አርባ ምንጭ እንኳን በእውን በምናብም ታምራለች፡፡ የስሟ መጠሪያ ከግርጌዋ ከተዘረጋው ሰፊ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የመሸጉት ብዙ ምንጮች ናቸው፡፡ የእነዚህ ምንጮች ቁጥር ከአርባም እንደሚዘል ይነገራል፡፡ ከጥቅጥቁ ደን መሽገው ለቆጣሪ ቢያስቸግሩና በየቦታው ቢንፎለፎሉ በአርባ ተወስነው ለዚህች ውብ የጐብኚዎች መዳረሻ ከተማ ስያሜ ሆኑ፡፡ እነዚህ ውብ እልፍ ምንጮች የተሸሸጉበት ጥቅጥቅ ደን ነጭ ሳር ብሔራዊ ፖርክ ሲያቀኑ የሚያቋርጡት ነው፡፡ ስፍራው ለአርባ ምንጭ ከተማ ቅርብ በመሆኑ ለጐብኚዎች ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ በስፍራው ጐብኚዎች የሚኖራቸው ቆይታ ከተፈጥሮ ጋር የሚዋደዱበት እድልን ይፈጥራል፡፡

ከጥቅጥቁ ደን መሀል አንድ ልዩ ቦታ አለ፡፡ ልዩ ስሙ የእግዜር አዳራሽ ነው ረጃጅም ዛፎች በእቅድ የተተከሉ ይመስል እንደ ምሰሶ በረድፍ ቆመዋል ቅርንጫፎቻቸው ደግሞ ከአናት ተቆላልፈው አንዱ በአንዱ ላይ ተኝቷል፡፡ በዚህ ትስስር ውስጥ ሾልኮ የሚገባ የፀሐይ ጨረር መሬት ሲያርፈ ጉልበቱ በነፋሻማ አየር ይዋጣል፡፡ ከዚህ ገላጣ ግዙፍ የተፈጥሮ አዳራሽ ዙሪያ እንደ ሌላው የደኑ አካል ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎች ቆመውበታል፡፡ የመሬቱ ወለል ከዛፎቹ ቅርንጫፎች በሚረግፍ ቅጠሎች ተሞልቶ ከምድር በላይ ሌላ ወለል ሰርቷል፡፡ ይህ ተፈጥሮ ያበጀችው ድንቅ አዳራሽ ነው፡፡ ውበቱ ተፈጥሮ ከምታሰማው ድንቅ ድምፅ ጋር ተዳምሮ እልፍ ትእይንት ነው፡፡ ተፈጥሮ የሰራችው ከውስጥ የሚቆራኝ ሃሴት እንደሚፈጥር ማሳያ ነው፡፡

የእግዜር አዳራሽ የሚለው ስያሜ ይህንን ውብ የተፈጥሮ ቅጥር ማንም እንዳልሰራው ለማሳየትና የራሷ የተፈጥሮ ገፀ በረከት እንደሆነ ለመግለፅ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡ በእርግጥ እግዜር ካልሆነ ፍጡር እንዲህ ያለውን ውበት ከእንዲህ ያለው ደን ውስጥ በምን ተአምር ሊያበጀው ይችላል፡፡ የሰው ልጅ እጆች መጥረቢያ ይወዳሉ ልባቸው በተፈጥሮ ይጨክናል፤ ተፈጥሮ ግን አትሰስትም እንዲህ ያለውን ድንቅ ስፍራ በእራሷ የአፈጣጠር ክህሎት አቀናብራ ለሰው ልጅ ትቸራለች፡፡ የእግዜር አዳራሽ ሰፊ ነው፡፡ የ2002 ዓ.ም የአለም ቱሪዝም ቀን በሃገራችን ሲከበር በሃገር አቀፍ ደረጃ የተከበረውን በዓል ያስተናገደ ድንቅ ስፍራ ነው፤ ብዙ እንግዶችን በሚያምረው ጥላው ከልሎ የአእዋፋትን ዜማ እየጋበዘ ንፁህ አየር እየሳበ እንግዶችን የተቀበለ አዳራሽ ነው፡፡ የእግዜር አዳራሽ በአማረ ተፈጥሮ ውስጥ መሞሸር ለሚፈልጉ ድል ያለ ሰርግ ማስደገስ የሚችል ከተዘጋጀው ድግስ መሃል የራሱን ንፁህ አየር የሚጋብዝ አስደናቂ ስፍራ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ከደረሱ የእግዜር አዳራሽ የት ነው? ብለው ይጠይቁ፡፡

No comments:

Post a Comment