Tuesday, February 7, 2012

አንፋርጌ እና ደብረ እንቁ


ቅምሻ ከሰማዳ መስኽቦች ሁለቱን
ስማዳ በአማራ/ብ/ክ/መ በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ መዛግብት የቀድሞ የአካባቢው መጠሪያ ሀገር ቢዝን እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ የአሁኑ ስያሜ ፃዲቁ ዮሐንስ የተባሉት ንጉስ ወደ ስፍራው ከሄዱ በኃላ የመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከአዲስ አበባ በ 767 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የወገዳ ከተማ የስማዳ ወረዳ መዲና ናት፡፡ 40 በመቶ የሚሆነው የወረዳው መልከአ ምድር ወጣ ገባማ ሲሆን ለእይታ ማራኪ ነው 25 በመቶው መልከአ ምደር ሜዳማ ሲሆን አመታዊው አማካኝ የዝናብ መጠን 1000 እስከ 1500 ሲሆን  አማካኝ የሙቀት መጠኑ 23 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ይደርሳል፡፡
እንደ 2001 ዓ/ም ስታስቲክሳዊ መረዳ 239.618 የሚደርሰ ህዝብ የሚኖርበት ስማዳ በርካታ ባህላዊ ታሪካዊ የተፈጥሮ ሰው ሰራሽ መስኸቦችን የታደለች ምድር ናት፡፡
አንፋርጌ ጊዮርጊስ
አንፋርጌ ጊዮርጊስ ሙጃ ሮቢት በሚባለው የስማዳ ገጠር ቀበሌ አቅራቢያ የሚገኝ መስኽብ ነው፡፡ አንፋር የሚለው ዛፍ ስም ለአንፋርጌ ስያሜ መነሻ እንደሆነ አበው ይናገራሉ፡፡
ከወረዳው ርዕስ ከተማ ከወገዳ 80 ከ.ሜትር ርቀት ላይ ቀበሌ 26 በሚባለው ስፍራ የሚገኘው ይህ ደብር በ1335 ዓ.ም በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግስት ዘመን ጭምር የቤተ መቅደስነት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ጥንታዊው የቤተ መቅደስ ፍራሽ ከቀይ ሸክላ ድንጋይ ተጠርቦ የተሰራ እንደነበር ዛሬም ድረስ የቆሙት ፍርስራሾች ማስረጃ ናቸው::
አንፋርጌ በየዘመናቱ ከነበሩ ጥቃቶች የተጠበቀ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት ስፍራ ሲሆን ከ 600 ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠሩ ትውፊቶች ማዕከል ነው፡፡ በአንፍርጌ ጊዮርጊስ ዙሪያ የሚደረጉ ጥናቶች መቀጠል ከቻሉ ተጨማሪ ትኩረት የሚሰጡ ክስተቶች ማዕከል ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
                               ///////                                          

ደብረ እንቁ ማርያም
ከወገዳ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገነው ደብረ እንቁ ማርያም ከተማ 5 ኪ.ሜትር ያክል በአርሶ አደር ማሳ ላይ ከተጓዙ በኃላ በውብ መልከአ ምድር ለአይን ትንግርት በሆነ ስፍራ የሚያገኟት ጥንታዊት ደብር ናት፡፡
ደብረ ዕንቁ ማርያም ቀበሌ 35 በሚባለው የስማዳ ወረዳ ስትገኝ የአረፈችበት ስፍራ በራሱ መስኽብ ነው፡፡ ደብረ እንቁ እና ዙሪያ ገባው መልከአ ምድር በተወሰነ መልኩ ከግሸን ማርያም ጋር የሚመሳሰል ገፅታ ሲኖረው ምናልባትም የደብረ ዕንቁ ማርያም ዙርያ ገባ ተፈጥሮአዊ መልክ የበለጠ ሳቢ የፈጣሪን ጥበብ የሚተርክ የጎብኚን ቀልብ የሚገዛ ስፍራ አድርጎታል፡፡
ከ 485 – 515 ባለው ግዜ በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግስት በአቡነ ፊሊጶስ እንደተተከለች አባቶች ይናገራሉ፡፡
 

No comments:

Post a Comment