Thursday, January 26, 2012


ወገና - የሐድያ የሠርቶ መለወጥ ልዩ እሴት


ወገና ብዙ ነገር ነው የሥራ ፍቅር ሠርቶ ጥሮ ራስን የመለወጥ ባህል ነው፡፡ ከወገና ጀርባ በስኬት መከበርና መሞገስ አለ ወገና ጥበብ ነው፡፡
ብዙ ምስጢር ያለው ጥበብ ወገና በሐድያ ብሔረሰብ ባህል ከብቶችን መቶ ወይም ሺሕ በማለት ማስቆጠር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የጥረትን ውጤት በተዋበ ባህል ማስመረቅ ነው፡፡ ለወገና ሥርዓት የሚመረጠው ወቅት መስቀልን ከሚያስተናግደው ወርሃ መስከረም አንሥቶ እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ይህ ወቅት የጥጋብ ነው፡፡ መስኩ ለምለም የሚሆንበት ወራት በመሆኑ የሐድያ ከብቶች ሰውነት ይደልባል፤ በዚያ ላይ ወንዞች መጠናቸው ቀንሶ የጐርፍ ስጋት የማይኖርበት ነው፡፡ እነኚህ ሁሉ ተደምረው ወገና የሚከናወንበትን ወቅት ልዩ እንዲሆን አድርገጎታል፡፡ በወገና የከብቶች ቆጠራ ሥነ ሥርዓት ሁለት ደረጃዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መቶ ከብቶችን የማስቆጠር ሥርዓቱ ጢቢማ ይባላል፡፡ ኩሚማ ደግሞ ሺሕ ከብቶችን የማስቆጠር ሥርዓት ነው፡፡

ማስቆጠር ማለት ማስመረቅንም የያዘ ነው፡፡ መቶ በማስቆጠሩ የጢቢማ ወግና ሥርዓት አንድ ሰው ከብቶቹ መቶ መሙላታቸውን ለማረጋገጥ አንድ ሁለት አስብሎ በማስቆጠር ማረጋገጥ ሲችል በሌላ መልኩ ደግሞ የቁልቋል ዛፍ ከበረት አዛባ መውጫ ላይ በመትከል ማስፈጸም ይችላል፡፡ ይህ የአቆጣጠር ባህል አንድን ሰው ይህን ያህል ከብት አለህ በሚል ብቻ ከብቶቹን ቆጥሮ ግለሰቡን የሚያሞካሽ ሳይሆን የከብቶቹን ምንጭ ለግለሰቡ ክብር እና ለሥርዓቱ እንደ ዋነኛ መስፈርት የሚቆጥር ነው፡፡ ይህም ከብቱን የሚያስቆጥረው ሰው ጥሮ ግሮ፣ ተፍጨርጭሮና ላቡን አንጠፍጥፎ አርብቶ መቶ ሲያደርስ ብቻ ነው፡፡ የሥራ ፍቅሩና ጥረቱ ከላቡ ውጤት ጋር ካልተደመረ ይሄንን ክብር ማግኘት አይቻልም፡፡ ያለ ስርቆትና ያለ ማጭበርበር በራሱ ጥረት ከብቶችን መቶ ማድረስ የቻለ ሰው ሐሜት ሳያገኘው ልጆቹ ሳያፍሩ እሱ ተከብሮ ይኖራል፡፡

ከዚህ ሥርዓት ጀርባ በሐድያ ባህል የጠበቀ ፉክክር አለ፡፡ አንዱ ከሌላው ላለማነስና ይሀንነ የወገና ክብር ለማግኘት ጠንክሮ ይሠራል፡፡ ወገናን አስመልክቶ በአቶ ኤርሲዶ አንተሴ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ሥርዓቱ ሐድያ ከከብት እርባታ ከእርሻ ሥራ ጋር የጠበቀ ቁርኝት በነበረው የቀድሞ ጊዜ በሁሉም የሐድያ አካባቢዎች የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው አሁን አሁን ግን ሥርዓቱ በስፋት የሚካሔደው አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በሚኖርበት ቆላማ አካባቢዎች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በወገና ሥርዓት ከገበያ የተገዛን ከብት ደምሮ ማስቆጠርን ባህሉ አያበረታታውም፡፡ ከዚህ ባለፈ የከብቶቹ መቶ ሞልቷል ሲባል የጥጆች ቁጥር ሳይጨመር ነው፡፡ ይህም ወግና ሥርዓቱን ለማከናወን የራሱ ሒደቶች አሉት፡፡ የግለሰቡና የሚስቱ ዘመዶች በተጠሩበት ይህንን ቁጥር የሚያፀድቁ ቡድኖች ይጋበዛሉ፡፡ እንደ ቅቤ፣ ማር፣ መጠጥና ምግብ ያሉት የእርድ ሰንጋዎች ይዘጋጃሉ፡፡ አዲስ በረት ለከብቶቹ ያዘጋጃል፡፡ ይህንን ሥርዓት ለመከታተል ለሚመጡ እንግዶች የሚሆን ማደሪያ ይዘጋጃል፡፡ እንደ አቶ ኤርሲዶ አንተሴ ጥናት ወገና ሁለት ምዕራፎች አሉት የመጀመሪያው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዐት እስከ ሌሊቱ 11 ሰዓት ያለው ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ‹‹ቄቃስ›› ይባላል፡፡ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡

ሁለተኛው ቀን ሌሊት ጀምሮ ያለው ሥርዓት ደግሞ በድራንቻ የሐድያ ባህላዊ የሙገሳ ጨዋታ ጭፈራ የሚደምቅ ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት በረቱ ተከፍቶ ከብቶቹ ሲወጡ መጀመሪያ የወጣውን ከብት የበኩር ልጅ፣ በመጨረሻ ላይ የወጣውን ደግሞ የመጨረሻ ልጅ ይወስዳሉ፡፡ በዚህ በወንዝ ማዶ በሚከናወን ሥርዓት በዚህ ሌሊት ማንም ሰው ከከብቶቹ ቀድሞ ወንዙን እንዲሻገር የሐድያ ባህል አይፈቅድም፡፡ ከብቶቹ የሚሻገሩበት ይህ ወንዝ ክረምት ከበጋ የማያቋርጥ መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ሀብቱ የማያቋርጥ ለትውልድ የሚተላለፍ እንዲሆን ያላቸውን ምኞት የሚወክል ነው፡፡ ከብቶቹ ወንዝ ሲሻገሩ ይህንን ሥርዓት የሚያፀድቁት ኮሚቴዎች ትልልቅ ከብቶችን ይቆጥራሉ፡፡ ቁጥሩ ልክ ከሆነ ያ ሥፍራ የኮሚቴውን ማጽደቅ ተከትሎ በእልልታና በሆታ በጭፈራ ይደምቃል፡፡ ባልና ሚስት ቅቤ ይቀባሉ፤ የሹመት ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከሹመቱ ስያሜዎች ብዙ ጊዜ የተለመደው አበጋዝ ነው፡፡ ይህ የጦር አበጋዝን ይወክላል፡፡ ከድህነት ጋር ታግለው ከፀሐይና ከዝናብ ጋር ተዋግተው በጥረት ባህላዊውን ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡

በሐድያ ባህል ሥራና ጥረት ፍጻሜ የለውም፡፡ ለዚህ ነው በወገና ሥርዓት መቶ ያስቆጠረ ትጉህ፣ ሺሕ ሞልቶ ኩሚማ (ከብቶችን ሺሕ የማስቆጠር) ሥርዓትን ለማከናወን ይጥራል፡፡ ከብቶችን ሺሕ በማስቆጠር የወገና ሥርዓት እንደ መቶ ማስቆጠሩ ሁሉ የቆጠራ ሥርዓቱ ተመሳሳይ ሲሆን፣ በሺሕ የማስቆጠሩ ሒደት ከመቶ የሚለየው ሥርዓት ከብቶች ሜዳ ላይ አውጥቶ በእግራቸው ሥር ማዶ አሻግሮ በማየት ሰማይ ከታየ አልሞላም፤ ካልታየ ግን ሺሕ ሞልቷል የሚባልበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህን ሺሕ የመሙላት ሥርዓት በድል ያጠናቀቀ ‹‹አዲላ ገራድ›› የሚል ማዕርግ ይሰጠዋል፡፡
ሐድያ በወገና ሥርዓት ሠርቶ መለወጥን በራስ ጥረት መከበርን በሥራ መግነንን የሚያሳይ ድንቅ እሴት ነው፡፡ (ቱባ፣ ሚያዝያ ፳፻፫)    

No comments:

Post a Comment