Thursday, January 26, 2012


‹‹ዳጉ ባአህ››



‹‹ሰው በዜና ውሃ በደመና›› የሚል የኖረ ብሂል አለ፡፡ ሰው በዜና ይኖራል፡፡ ውሃም በደመና በኩል ይመጣል፡፡ ተረተኛው እንዲህ ያነፃፅረዋል፡፡
የዘመኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ተከትሎ የመረጃ መለዋወጫ ደረጃው ከላቀ ደረጃ ከመድረሱና ዓለምን ወደ አንድ መንደር ከመለወጡ በፊት እንደየኅብረተሰቡ ወግና ልማድ፣ እንደየነገዱ አካሔድ የመረጃ መለዋወጫ ስልት ለዘመናት ኖሯል፡፡ አሁንም አለ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ የአፋር የመረጃ ልውውጥ መንገድ ነው፡፡ በአፋርኛ ‹‹ዳጉ›› ይሰኛል፡፡

ሀገሬ ሚዲያ ባወጣው ‹‹ሀገራችንን እንወቅ - ቱባ›› ሕትመቱ ላይ ስለ ዳጉ ያብራራል፡፡ ዳጉ በበረሃማው ስነ ምህዳር የሚኖሩት አፋሮች አካባቢያቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በዳበረ መረጃ ልውውጥ የታነፀ እንዲሆን ያስቻላቸው የባህል እሴት ነው፡፡ 


በአፋሮች ባህል ማዳመጥ ከመስማት በአለፈ ጠልቆ በመረዳት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይኸ ደግሞ እንደ ዳጉ ባሉ የባህል እሴቶቻቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ ዳጉ ማለት በአፋርኛ ወሬ፣ ነገር እንደማለት ነው፡፡ 

በዚህ ስልት እርስ በእርስ መረጃን ይለዋወጣሉ፡፡ በዚህ ስልት ተደማጭ ካልሆኑ ባለ ረጅም ሞገድ የሬዲዮ ስርጭቶች በፈጠነ ሁኔታ መረጃ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ይደርሳል፡፡ ከመልካ ሰዲ ኤሊ ውሃ፣ ከበርሃሌ ዱብቲ፣ ከገዋኔ ኦፍዴራ በረሃማውን የአፋር ምድር ርቀት ሳይገድበው አብሮነታቸውን እንዲዳብር ያደረገው የአፋሮች እሴት ይህ ዳጉ የተባለ መረጃን የሚለዋወጡበት ስልት ነው፡፡ 

በአፋሮች ባህል ልብን ሰጥቶ ማዳመጥ የግድ ነው፡፡ ጫፍ ይዞ መሮጥም የለም ለዚህ ነው ባህላዊ የፍትህ ሥርዓታቸው ግጭትን በማስወገድ በኩል የተዋጣለት የሆነው፡፡ ነገርን ከመሠረቱ ያደምጣሉ ከመሰረተ ችግርን እንዲፈቱ ያግዛቸዋል፡፡ የዝናብና የግጦሽ ሁኔታ የግጭትን ዜና የአካባቢያቸውን ውሎ እየተቀባበሉ ይሰሙታል እናም እድሜ ለዳጉ አፋሮች አካባቢያቸውን በሚገባ እንዲያውቁ አድርጎአቸዋል፡፡ ያልነበሩበትን አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ በመረጃ ስልታቸው የነበሩ ያክል ያውቁታል፡፡ ዘመን የግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ጥበብን ሳያዳብር ዜናዎች በሳተላይት በረው ከየሰው ጆሮ መድረስ ሳይጀምሩ ኢትዮጵያ ዳጉን የመሰለ የመረጃ መለዋወጫ ስልት እሴት ባለቤት ነበረች፡፡ የዳጉ ስልት ግን በአማርኛ እንዳለው ትርጉም ቀለል ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእርግጥ አፋሮች እርስ በእርስ በሚኖራቸው ግንኙነት ወቅት ‹‹ዳጉ ባአህ›› ይባባላሉ፡፡ ይኸም መረጃ አቀብለኝ እንደማለት ነው፡፡ ጨዋታ አምጣ ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጨዋታው ከፌዝነት ይልቅ መረጃነት ያለው መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ 

በአፋሮች ባህል ሁለት አፋሮች እንደተገናኙ አንዱ ሌላኛው ይጠይቃል፤ ስለ ራሱ፣ ስለ ቤተሰቡ፣ ስለ መንደሩ፣ ስለ ጎሳውና ስሰማው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ሁሉንም ይተርካል፤ ያደመጠው ደግሞ በተራው የራሱን ለሌላኛው ይነግረዋል፡፡ ዳጉ የተባለው ባህል ይህ ነው፡፡  

ቱባ፣ ስለ አፋር ክልል መስህቦቹም ያነሣል አፋሮች ባህልና ተፈጥሮ ህብር ሠርተው በተቀናጁበት ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ባህላቸው የፈጠረው ቀለም ምድራቸውን አስውበውታል፡፡ ምድራቸው በራሱ ተፈጥሮ የቸረችው ገጽታ ደግሞ ምትሃት ቢባል የሚቀል ድንቅ ውበት ነው፡፡ የኤርታ አሌ እሳተ ጎሞራ እስከ 1200 ዲሴ በሚደርስ የእሳት እቶን የሚንቀለቀል ስፍራ ነው፡፡ አፋሮች ኤርታ አሌ ያሉትም ለዚህ ነው፡፡ የሚጨስ ተራራ የሚል ትርጉም አለው፡፡

ከሦስት ሚሊዮን ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረችው ሉሲም መገኛዋ በዚህ በአፋር ክልል ነው፡፡ ከሰመራ 136 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሃዳር የተባለው ስፍራ በአፍሪካ ገናና ከሚባሉ የአርኪዮሎጂ ጥናት ቦታዎች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ ከሉሲ ባሻገር እንደ ራሚደስ፣ ካዳባ፣ ጋርሂ ያሉ ቅሪተ አካሎች የተገኙበት የአፋር ክልል በፓርክ ሃብቱም ይታወቃል፡፡ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ እና ገና ብዙ ያልተወራለት በአዘሎ ተራራ ሥር የተዘረጋው የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክም መገኛ ነው፡፡ አሳአሌ ሐይቅ፣ አፍዴራና አቤ ሃይቆችና የዳሎል ረባዳ ምድር የአፋር ውብት ከሚገለፅባቸው መስህቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ምድራቸው ተፈጥሮ ሁሉ በብዝሃ የባህል እሴቶች የሚታወቁት አፋሮች ዋንኛ የኑሮ መሠረታቸው የእንስሳት እርባታ ግብርና ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment