Monday, August 20, 2012


ብጹእ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማይ፤ ፓትረያሪክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ሊቀ-ጳጳስ ዘ አክሱም፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት፤ የዓለም ሐይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፤ የሰላም አምባሳደር በተወለዱ በ76 ዓመታቸው አረፍ፤



ለሃገሪቱ ቱሪዝም ልማት እና ለሙዚየሞች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጾ ማበርከት የቻሉ አባት ነበሩ፤



የዛሬ 76 ዓመት በአድዋ ከተማ አቅራቢያ በአባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ..  ከካህን ቤተሰብ፣ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ አራደች ተድላ ተወለዱ፤ የያኔው ገብረ መድኅን የአሁኑ  አቡነ ጳውሎስ፣ከዚያም  በጥንታዊው አባ ገሪማ ገዳምና በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በማቅናትም ከሩሲያው የቅዱስ ቭላድሚር ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ በኦርየንታልና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የነገረ መለኮት ይትበሐል (ትምህርት) 1954 . ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በየል ዩኒቨርሲቲ በኦሪየንታል፣ በምሥራቅና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከትና ልዩነት ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪን 1958 . ሲያገኙ፣ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማስተርስ ኦፍ ቴኦሎጂ ዲግሪን 1964 .. ተቀብለዋል፡፡ በዚያው ዩኒቨርሲቲ 1980 .. የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪያቸውን ያገኙት ስለእግዚአብሔር ህልውና እና ስለፍልሰታ ማርያም በጻፏቸው የጥናት ድርሳኖች ነው፡፡

ቅዱስነታቸው የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የጥበበ ዕድ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም በመምራት፣የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር፣የታሪክ፣ የድርሰትና የስብከተ ወንጌል፣ የጋዜጦች፣ የመጽሔቶችና የሬዲዮ መምርያ የበላይ ኃላፊ፣ ቃለ አዋዲ የተሰኘውን የመመርያ ደንብ በማውጣት ምእመናን በሰበካ ጉባዔ፣ ካህናትን በካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች በሚያደራጁበት ወቅት ግንባር ቀደም በመሆን ተሳትፈዋል፡፡ በመሆን ሲሠሩ፣ ከአገር ውጭም 1950 .. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመወከል በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ቋሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡

መስከረም 16 ቀን 1968 .. ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ተብለው ከተሾሙ በኃላ ወታደራዊው መንግስት ደርግ እርሳቸውንና አብረዋቸው የተሾሙትን አቡነ ባስልዮስና አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ ለእስር ዳረጋቸው፡፡ ሰባት ዓመትም አሰራቸው፡፡ 1974 .. ከእስር ቢለቀቁም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከቤተ ክህነት በጡረታ እንዲገለሉ በመደረጋቸው ባሕር ማዶ ሔደው በእስር ምክንያት ያቋረጡትን የዶክትሬት ትምህርታቸውን ለመቀጠልና ለማጠናቀቅ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችም ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ምዕመናን አገልግሎት የሚሰጡ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን አቋቁመዋል፡፡ የደርግ መንግሥት 1983 .. መውደቁን ተከትሎ ከስደት የተመለሱት አቡነ ጳውሎስ በዓመቱ በተደረገው ምርጫ አምስተኛው ፓትርያርክ ሆነው በመመረጥ ሕይወታቸው እስካለፈበት እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2004 .. ድረስ 20 ዓመት 36 ቀን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መርተዋታል፡፡ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ የመጀመሪያው አባትም ሆነዋል፡፡

በተለይ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የመንበረ ፓትርያርክ ሕንፃ ማስገንባታቸው፣ ያለፉት የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች የተገለገሉባቸውን ንዋያተ ቅድሳትና ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትንና ታሪካዊ ቅርስ ቅርሶችን አካቶ የያዘ ዘመናዊ ሙዚየም ማስገንባታቸው ልዩ ሥፍራ አግኝቷል፡፡ ለዘመናት በደሳሳ ቢሮ ይኖር የነበረው ጠቅላይ ቤተክህነት ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ፎቆች ባለቤትም ሆኗል፡፡ ሌላው ስኬታቸው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በእንግሊዝ ተዘርፈው ከተወሰዱ ቅርሶች መካከል ታቦትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት እንዲመለሱ ማስደረጋቸው ነው፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ሕትመትም፣ በዘመናቸው በርካታ የአንድምታ ትርጓሜ መጻሕፍት ታትመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚገልጽ በቅዱስ ሲኖዶስና ሊቃውንት ጉባዔ ተዘጅቶ በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ታትሞ የተሰራጨው ለመጀመርያ ጊዜ በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና መሠረት የግእዙን መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ያደረገ መጽሐፍ ቅዱስ በሊቃውንቱ አማካይነት ተዘጋጅቶ 2000 .. ታትሞ እንዲወጣ ማድረጋቸው፣ በተከታታይ ታትሞ ቢሰራጭም አንዳንድ ግድፈት ስለተገኘበት እንደገና ከበፊቱ በበለጠ በጥራት ታርሞና እንከን የለሽ ሆኖ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲታተም በሰጡት መመርያ መሠረት፣ ኮሚቴው ብዙ ጊዜ ወስዶ በጥንቃቄ ካረመ በኋላ በአሁን ወቅት ለሕትመት ዝግጁ መሆኑ ይነገራል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አማርኛው በአንድ ጥራዝ ተጠቃልሎ እንዲዘጋጅ በሰጡት መመሪያ መሠረት ተጠናቅቆ ለኅትመት መቅረቡ ከትሩፋታዎቻቸው መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

እኒህ የሃገራችን መልካም ገጽታ በመላው ዓለም እንዲተዋወቅ የጣሩት፣ደግሞም በእጅጉ የተሳካላቸው ዓለም አቀፋዊው አባት ለኢትዮጵያ የቅርስ ሃብት መጠበቅ እና ለሙዚየሞች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጾ እያበረከቱ በአለበት የአገልግሎት ዘመናቸው በዕለተ ሐሙስ፣ ነሐሴ 10 ቀን 2004 .. ንጋት ላይ አርፈዋል፡፡

ምንጭ፡-
የዲ/ን መላኩ እዘዘው ስንክሳር
የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዓለም አቀፋዊ ሰውነት 2000 ዓ.ም


No comments:

Post a Comment