Wednesday, October 3, 2012


ማጫወት፣ መጋበዝ እና መውደድ የሚችለው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ

120 ሰዓታትን በደስታ

የ2005 ዓ.ም  የዓለም ቱሪዝም ቀን መስከረም 17 ቀን ተከብሯል፡፡ ሃገር አቀፍ ዝግጅት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተከበረ ሲሆን ከተከበረባቸው ስፍራዎች አንዱ ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ምድር ነው፡፡ ቱሪዝም ከዘላቂ የሃይል አቅርቦት ልማት ጋር ተቆራኝቶ እንዲከበር በመሪ ቃልነት የተከበረውን የዘንድሮ የቱሪዝም ቀን ለመታደም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከትመን ነበር፤

ከመተከል ዞን የጀመረው የሞቀ አቀባበል፣ እስከ ኦሮምያ ክልል ድንበር በዘለቀው የሽኝት ሥነ-ሥረዓት የ120 ሰዓታት እድሜ ነበረው፡፡ በዚህ እድሜ ውስጥ በዙምባራ ጥኡም ዜማ ታጅቦ የጉምዝ አያሌ ባህሎች ከልባችን ገብቷል፡፡ የበርታ እንግዳ አቀባበል፣ የኮሞ ጨዋታ የማኦ መስተንግዶ ስለቤኒሻንጉል ጉምዝ የምናወራውን እልፍ አድርጎታል፡፡

የቦሮ ሽናሻ ብሄረሰብ ከድንቅ ውዝዋዜው ጋር ቁርጡን እየመተረ መስቀሉን አብረንው እንድንታደም አድርጎናል፡፡ የማንኩሽ መስተንግዶ፣ የደጃዝማች ባንጃው ድንቅ እልፍኝ፣ የህዳሴው ምድር ውሎ አያሌ ትዝታዎች የታጨቁበት ጉዞ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ሀብታሙ ክልል አረንጓዴ ምድር እና ገና ያልተነገረ ታሪክ ያለው ነው፡፡

ተጫዋቹ፣ ተግባቢውና ለሰው ቅርብ የሆኑት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከተገናኘንበት ቀን ጀምሮ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንግዳ ተቀባይ አመራር እንዳለ አብነት ሆነው አሳይተውናል፡፡ ያዓ መሰራ እኩል ቀን ከገደልንባቸው መዳረሻዎች አንዱ ነበር፡፡ የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት ጉብኝት የማንጎ ሎጅ መስተንግዶ እና መሰል የመዝናኛ ጊዜዎች አይረሴና መልካም ነበሩ ዓመቱን እንደ ወቅቱ እየቆነጠርን ለመተንተን እድሜና ጊዜ ይስጠን፡፡  

No comments:

Post a Comment