Thursday, December 10, 2015


                     ገዜ ጎፋ ወረዳ
 

ገዜ ጎፋ ወረዳ በጋሞ ጎፋ ዞን ከሚገኙ 2 ከተማ አስተዳደሮችና 15 ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቡልቂ ስትሆን የተመሰረተችውም በ1918 ዓ.ም. ነው፡፡ የቡልቂ ከተማ ከተማው ወደ ሳውላ እስከ ተዛወረበት ማለትም እስከ 1955 ዓ.ም.  የድሮው የጎፋ አውራጃ ከተማም ነበረች፡፡
የገዜ ጎፋ ወረዳ በስተሰሜን ደምባ ጎፋና መሎ ኮዛ ወረዳዎች፣ በስተምስራቅ ደምባ ጎፋና ኦይዳ ወረዳዎች፣ በስተደቡብ ደቡብ ኦሞ ዞንና ኦይዳ ወረዳ፣ በስተምዕራብ ባስኬቶ ልዩ ወረዳና መሎ ኮዛ ወረዳ ያዋስኑታል፡፡ ወረዳው ከአዲስ አበባ በ531 ኪሎ ሜትር፣ ከሀዋሳ 319 ኪሎ ሜትር፣ ከአርባ ምንጭ 267 ኪሎ ሜትር፣ ከወላይታ 148 ኪሎ ሜትር ከሳውላ በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው አየር ንብረት በሶስት አግሮ ኢኮሎጂካል ዞኖች የሚከፈል ሲሆን ደጋ 21.5 በመቶ፣ ወይና ደጋ 70 በመቶ፣ ቆላ 8.5 በመቶ ነው፡፡ አማካይ የሙቀት መጠኑ ደግሞ 23 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲሆን የዓመቱ አማካይ የዝናብ መጠን 1300 ሚሊ ሊትር ይደርሳል፡፡


የወረዳው መልካአ ምድራዊ አቀማመጥ በአብዛኛው ወጣ ገባ ነው፤ አልፎ አልፎ ሜዳማ አቀማመጥ አለው፡፡ ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ ከ2300-2400 ሜትር ሲሆን ዝቅተኛ ቦታ የሚባለው ከባህር ጠለል በላይ 1000 ሜትር ነው፡፡
የወረዳው ህዝብ ብዛት በገጠር 78,460 በከተማ 8,355 በድምሩ 86,815 ነው፡፡ በወረዳው የተለያዩ እምነት ተከታዮች ያሉ ሲሆን እነሱም ኦርቶዶክስ 39.29 በመቶ፣ ፕሮቴስታንት 55.22 በመቶ፣ ሙስሊም 2.39 በመቶ ሌሎች 3.10 በመቶ ናቸው፡፡ ወይና ደጋማ የአየር ንብረትና ለም አፈርን የታደለው የገዜ ጎፋ ወረዳ የኢኮኖሚ መሰረቱ በዋናነት እርሻና ከብት እርባታ ሲሆን ንግድና ሌሎች መስኮችም ለወረዳው ኢኮኖሚ የድርሻቸውን ያበረክታሉ፡፡ ወረዳው የተለያዩ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና መንፈሳዊ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡ በዚህ ዕትም ጥቂቶቹን እንመለከታቸዋለን፡፡
 
ጣቴወራ (ጫት ደን)፡- ከዋና ከተማው 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ የተፈጥሮ መስህብ በተፈጥሮ የተገኘ የጫት ደን የበቀለበት ነው፡፡ የደኑ ሽፋን 4 ሄክታር አካባቢ ሲሆን በድሮ ገርማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ይገኛል፡፡
ኬንቾገራራ፡- ይህ መስህብ ከከተማው በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት በኬንቾ ወይዛ ቀበሌ ሲገኝ ጥንታዊ የጎፋ የንግስና ስፍራ ነው፡፡
ካቲሁምኦ ዋሻ፡- ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የሆነው ይህ ዋሻ 20 ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር ስፋት አለው፡፡ ዋሻው በጣሊያን ጦርነት ግዜ ለምሽግነት ያገለግል ነበር፡፡
ሴሊሁምኦ (ዋሻ)፡- ከከተማው 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በድሮ ሴሎ ቀበሌ የሚገኝ መስህብ ሲሆን ጥናት ባይደረግበትም በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ውስጡ እስከ ሰሜን አሪ ድረስ ውስጥ ውስጡን እንደሚያስኬድ ይነገራል፡፡ ዋሻው ውስጥ በአካባቢው መጠሪያ “ አዶ ” የሚባል ለከብቶች መኖ ማጣፈጫነት የሚያገለግል ጨዋማ አፈር አለው፡፡
ወይራሁምኦ (ዋሻ) ፡- ከከተማው በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዳዳጊያ ቀበሌ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ዋሻ ነው፡፡
ካማሞ ተራራ፡- ከከተማው 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሰንሰለታማ ተራራ ሲሆን ለተራራ ቱሪዝም የተመቸና  ለዓይን የሚማርክ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ያለው ነው፡፡ በተራራው አናት የሰንበሌጥ ሳር ይበቅልበታል፡፡
ባይፃ ተራራ፡- በወረዳው ውስጥ ከሚገኙት ተራራዎች ከፍተኛው ሲሆን ርዝመቱም 2500 ሜትር ይሆናል፡፡ ልዩ የሚያደርገው ተራራው ላይ የተፈጥሮ ጫት ደን እና የተለያዩ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ጎሽና ነብር በተራራው አናት ከሚገኙ የዱር እንስሳት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ተራራው የባህላዊ አምልኮ ስርዓትም ይፈፀምበታል፡፡
ጉያ ተራራ፡- ከከተማው 500 ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ተራራው በባህር ዛፍና በኮሶ የዛፍ ዝርያ የተሸፈነ ነው፡፡ በፊት ዘመን የሰው ልጅ ለመኖሪያነት ይጠቀምበት እንደ ነበርና የአሪ ብሔረሰብ መኖሪያ እንደሆነም ይነገራል፤ በቦታው ቁፋሮ ሲካሄድ የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሶች ተገኝተዋል፡፡ ከነዚህም፡- የድንጋይ ወፍጮ፣ ቅል፣ የትንባሆ ማጨሻ፣ ጨሌ …. ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ሻቺደን (ዞናዊ ፓርክ)፡- ይህ ፓርክ የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎች፣ ተሳቢ እንስሳት እና አጥቢ የዱር እንስሳት መገኛ ነው፡፡ ከእነዚህ እንስሳት ውስጥ ጎሽ፣ ነብር፣ አሳማ፣ ከርከሮ፣ ደፈርሳና አጋዘን በዋናነት ሲጠቀሱ የተለያዩ የአእዋፍና የእባብ ዝርያዎችም ይገኙበታል፡፡
ጉድባ (ምሽግ)፡- በጣሊያን ጦርነት ግዜ በግማሽ ጨረቃ ቅርፅ የተሰራና ለምሽግነት የተጠቀሙበት ነው፡፡ ስፍራው በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ገበያ ተሰርቶ ለመገበያያነት ያገለግላል፡፡
ኮይታ ሊቤጫቆበሳ (የመሀላ ቦታ)፡- በጎፋና በኦይዳ ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን የጎፋና የአሪ ባላባቶች ከረዥም ዓመት በፊት በጦርነት ላለመገናኘት የተማማሉበት ቦታ ነው፡፡ ቦታው እስከአሁንም ድረስ ይህንን ታሪካዊ ክንዋኔ በማስተናገዱ በታሪካዊነት ይጠቀሳል፡፡
የገዜ ጎፋ ወረዳ ረዥም ዘመናት የኖሩና በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ መንፈሳዊ መስህቦች የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የጃውላበሻ ማርያም፣ የቡልቂ መስጂድ፣ የጊዮርጊስ እና የመድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን ይገኙበታል፡፡
የጃውላ በሻ ማርያም፡- በደጃዝማች በሻህ በ1903 የተተከለ ሲሆን ወረዳው ላይ የመጀመሪያውም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በውስጡ የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት ሲገኙ ከእነዚህ ውስጥ የብራና መጽሐፍትና የብር መስቀሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የቡልቂ መድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን፡- በወቅቱ የአካባቢው ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ተስፋዬ መርዕድ በ1918 ፅላቱን አስመጥተው እንዳስተከሉት ይነገራል፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በርካታ ጥንታዊ ንዋየ ቅድሳት (የቤተክርስቲያን መገልገያዎች) ያሉ ሲሆን በተለይም የተለያዩ የብራና መጽሐፍት ማለትም ግንዘት አንድ፣ ዳዊት አምስት፣ መጽሐፈ ቄደር አንድ፣ መጽሐፈ ቅዳሴ አንድ፣ መጽሐፈ መቅድመ ማርያም አንድ፣ መጽሐፈ ስላሴ አንድ፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ ድርሳነ ማህያዊ አንድ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የነሐስ ጽዋ 2፣ የነሐስ መስቀል 2፣ የብር መስቀል 2፣ የነሐስ መቋሚያ 35፣ የነሐስ ፅናፅል  40፣ የነሐስ ፅናህ 4፣ የብር ፅናህ 1፣ 7 የሰጎን እንቁላል የሚገኙበት ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በወቅቱ የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከአቡነ ሰላማ የተበረከተ አንድ ትልቅ ካባ፣ ከነገስታት የተበረከተ አንድ ጥቁር ካባ እና ለምድ ካባ በቅርስነት ይገኛሉ፡፡
የቡልቂ መስጂድ፡- አባቶች እንደሚናገሩት የቡልቂ መስጂድ በ1929 ዓ.ም. በሼህ ሙዘይን ሱሌማን የተቋቋመ ሲሆን በሰዓቱ የተለያዩ የብራና መጽሐፍት የነበሩት ታሪካዊ መስጂድ ነው፡፡ መስጂዱ ውስጥ የነበሩት የብራና መጽሐፍት በአሁን ሰዓት ግን የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡
የወረዳው ኢንቨስትመንት አማራጮች
በግብርና ዘርፍ፡- ጠንካራ አርሶ አደሮች የሚኖሩበትና ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው የገዜ ጎፋ ወረዳ የአገዳ ሰብሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ስራ-ስር አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና ይመረትበታል፡፡
በተለያየ የንግድ ሥራ መስክም የወረዳዋ ከተማ ቡልቂ ምቹ ቀጠና ናት፡፡ ከተማዋ የንግድ ማዕከል ስትሆን በየዓመቱ በአማካይ 695.6 ቶን ቅሽር ቡና፣ 300 ቶን ኮሮሪማ፣ ሰሊጥ 240-9 ቶን እንዲሁም 33,148 ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርብባታል፡፡ ከምግብ እህሎች 2104 የአገዳ ሰብል፣ 3807 ቶን የጥራጥሬ ሰብል፣ 3414 ቶን የብርዕ ሰብል፣ 700 ቶን የስራ-ስር አትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች 37.411 የቁም እንስሳት 2152 ኪሎ ግራም አይብና ቅቤ ለአካባቢውና ለውጭ ገበያ ይቀርባል፡፡
ቡና በስፋት የሚመረት ምርት ሲሆን ኮረሪማም በተመሳሳይ በአብዛኛው የወረዳው ቀበሌዎች ይመረታል፡፡ አብዛኛው ቀበሌ ላይ ስራ-ስር ምግቦች ጎደሬ፣ ቦዬ፣ አንኮሶሌ( ሀገሬድንች)፣ ቦይና፣ ስኳር ድንች በስፋት ይመረታል፡፡ ጫትም በዋናነት 17 ቀበሌዎች ላይ የሚመረት ሲሆን የጥራጥሬ ሠብሎች ደግሞ እንደ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጠመጅ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ቦሎቄና ሌሎችም በበልግና መኸር ወቅት በሁሉም ቀበሌዎች በስፋት ይመረታሉ፡፡
ገዜ ጎፋ በቅባት እህሎች ምርትም ትታወቃለች፡፡ ኦላገልማ፣ ኦላዲያበላ፣ ኦላሸራሼምፓ፣ በድሮኤላ፣ በድሮጨበሮ፣ ኢማሮጎማ፣ ኢማሮሸጌ፣ አሊዛሀይጌሴ፣ ከንቾጎቢ በሚባሉ ቆላማ ቦታዎች ሰሊጥ በስፋት ይመረታል፡፡
ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቡካዶ፣ ፓፓያን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች በ8 ቀበሌዎች ሲመረቱ እንደ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ አበሻ ጎመን፣ ነጭና ቀይ ሽንኩርት ያሉ አታክልቶች በአብዛኛው የወረዳው ቀበሌያት ይመረታል፡፡
በእንስሳት ሀብቱ የሚታወቀው ገዜ ጎፋ ምርት ብቻ ሳይሆን ተወዳጅ የሆነ የእንስሳት ምርት የሚያመርት ወረዳ ነው፡፡  በወረዳው የሚመረተው የቀንድ ከብት በዓመት በአማካኝ 161,817 ይደርሳል፡፡ ተወዳጅ የሆኑ የደጋ በጎች ምድርም ነው፡፡ 57,530 የሚሆኑ በጎች በዓመት ይመረታሉ፡፡ የፍየል ምርቱ ደግሞ 18,837 ሲደርስ 60,274 የሚሆኑ ዶሮዎች ይመረታሉ፡፡ ጋማ ከብቶች ምርት ደግሞ 74,078 ያህል ይደርሳል፡፡ በሌላ በኩል የንብ እርባታ (የንብ ማነብ) በባህላዊና በዘመናዊ የንብ እርባታ ዘዴ በመጠቀም በወረዳው የማርና የሰፈፍ ምርት ይቀርባል፡፡
ወረዳው ለምና ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ወደ ወረዳው መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በገጠር ለግብርና 120 ሄክታር ቦታ የተዘጋጀ ሲሆን በከተማ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሪስቶራንቶች መገንባት ለሚፈልጉ 3000 ካሬ ሜትር ቦታ የተዘጋጀ መሆኑን ወረዳው ያበስራል፡፡

No comments:

Post a Comment