Thursday, December 10, 2015


                            አሹራ-ሀረሪዎች የሚያደምቁት ኩነት
 
 

አሹራ በሀረሪ በድምቀት የሚከበር ዓመታዊ ኩነት ነው፡፡ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር የሆነው ሙሐረም በገባ በ10ኛው ቀን ይከበራል፡፡ አሹራ በሀረሪዎች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚያጅቡት የተለየ በዓል ነው፡፡ የበዓል አከባበሩ የተለየ እንዲሆን ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ በየቤቱ በአዋቾች የሚዘጋጀው ገንፎ በቅቤ አንዱ ነው፡፡



አሹራ የአዲስ ዓመት በዓል ነው፡፡ ኢስላማዊ መሰረት ያለው ቢሆንም በሀገራችን በተለየ መልኩ የሚያከብሩት ሀረሪዎች ናቸው፡፡ ባህላዊ ገንፎ ያዘጋጃሉ፤ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ በጋራ የመመገብና በዓሉን በአብሮነት የማሳለፍ ባህል አላቸው፡፡ ይሄ ደግሞ መገለጫቸው እስከመሆን ደርሷል፡፡

አሹራ ባህላዊም ሃይማኖታዊም ክንዋኔዎች የተካተቱበት በድምቀት የሚከበር በዓል ሲሆን ሀረሪዎች ዕለቱን በየቤታቸው በጸሎትና ቁርዓን በማንበብ ያሳልፉታል፡፡ የገንፎ ስርዓቱ የባህላዊ ዜማ ጨዋታዎችና ለጅቦች ገንፎ የማብላቱ ስርዓትም የአሹራ መገለጫዎች ከሆኑ ክንዋኔዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ለጅቦች ገንፎ የመመገብ ስርዓቱ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ክንዋኔ ጭምር ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአው ንጉስ አብዱልቃድር ጄይላን፣ በአው ሐኪምና በአው አቦከር አዋች ተፈጥሯዊ በሆነ የድንጋይ ገበታ ላይ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀው ገንፎ በቅቤ ተደርጎ ለጅቦች ይቀርባል፡፡ ጅቦችን በአሹራ የሚዘጋጅላቸውን ገንፎ በደስታና በመጠራራት ይመገቡታል፡፡

የዘንድሮው የአሹራ በዓልም እንደከዚህ በፊቶቹ በዓላት ሁሉ በድምቀት የተከበረ ነው፡፡ በዓሉ ሐሙስ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በድምቀት ሲከበር ዋናው ስነ ስርዓት በአዳ ቤት ተካሂዷል፡፡ በአው አድባር፣ አው ንጉስና አው ፈጣን በከር በድምቀት ስነ ስርዓቱ ከተከናወነባቸው ስፍራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በዕለቱ ከቀኑ 10 ጀምሮ የቅል ሰበራ ስርዓቱ ተካሂዷል፡፡ በየአድባራቱ በመዞር የገንፎ መብላቱ ስርዓትና በየቤቱም ያለው ተመሳሳይ የገንፎ በጋራ መመገብ ስነ ስርዓት የተከናወነ ሲሆን በዕለቱ ምሽቱን ለጅቦች ገንፎ የማብላት ስርዓቱ ተካሂዷል፡፡

No comments:

Post a Comment