Friday, October 2, 2015



የዓለም ቱሪዝም ቀን


ሃና መለሰ



በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የዓለም የቱሪዝም ቀን "ሚሊዮን ቱሪስቶች ሚሊዮን እድሎች " በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተከበረ ይገኛል፡፡
ለዚህ በዓል ከፌደራልና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የቱሪዝም ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን ቅዳሜ መስከረም 15, 2008 ዓ.ም. መነሻውን አዲስ አበባ ያደረገው ቡድን እሁድ መስከረም 16 ቀን በሀረሪ ክልል ሲደርስ የሀረር ከተማ ህዝብ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊዎችና ሰራተኞች በማርሽ ባንድ አጅበው አቀባበል አድርገዋል፡፡ ቀጥሎም በከተማው ውስጥ ካሉት 4 ሙዚየሞች ሁለቱን ሙዚየሞች እንዲሁም በግንባታ ላይ ያለውን የእደ-ጥበብ ውጤቶች ማምረቻና ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና የሀረሪ ክልል የባህል ማዕከል ግንባታን በማስጎብኘት ልዑካን ቡድኑን ወደ ጅግጅጋ ሸኝተዋል፡፡
ጉዞውን ወደ ጅግጅጋ ያደረገው ቡድን ለዓይን የሚማርኩ፣ የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው እና የተደራረቡ ድንጋዮችን እንዲሁም የባቢሌ አርኪዮሎጂ ጥናትና መስህብ ስፍራ ተፈጥሮሯዊ መልካአ ምድርን ተመልክቷል፡፡ በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የክልሉ ባለስልጣናት፣የክልሉ የኪነት ቡድን ድንቅ በሆነው የባቢሌ የተፈጥሮ መስህብ መዳረሻ ስፍራ ላይ በባህላዊ ሙዚቃ ታጅበው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገዋል፡፡
ሰኞ መስከረም 17
በዓሉን አስመልክቶ በጅግጅጋ ከተማ በሱማሌ የባህል አዳራሽ የባህል ቱሪዝም ሚኒስትሮችና በየተዋረዱ ያሉ አመራሮች በተገኙበት ሲምፖዝየም የተካሄደ ሲሆን በሲምፖዚየሙም ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡የመጀመሪያው ፅሁፍ ትኩረት ያደረገው ክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም መስህብ እና መዳረሻዎቹን ያመላከተ ሲሆን ሁለተኛው ጥናታዊ ፅሁፍ ደግሞ ከመሪ ቃሉ ጋር በማስተሳሰር አለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ሁኔታን የዳሰሰ ነበር፡፡ 


ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሀ ግብር ደግሞ የወንበርካ ግድብ፣ የሶማሌ ባህላዊ መንደር (ካሌ)፣ ባህላዊ ቁሳቁሶች እና ባህላዊ የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች ለእይታ ቀርበዋል፤ በወንበርካ ግድብ ዙሪያ የችግኝ ተከላ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡
ማክሰኞ መስከረም 18 ቀን
ከጅግጅጋ ከተማ በ212 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሲቲ ዞን በኤረር ወረዳ የሚገኘው የኤረር ፍል ውሀ እና የአፄ ኃይለ ስላሴ ቤተ መንግስት ጉብኝት ተካሂዷል፡፡በእነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ከሀረሪ ክልል ወጥተን የሶማሌ ክልልን ከረገጥንበት ጊዜ ጀምሮ በሄድንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ህዝቡ በየመንገዱ ግራ ቀኝ ተሰልፎ በአካባቢው ቋንቋ "ሶዶ ዋዳ" በአማርኛ ሲተረጎም እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት እንግዳ ተቀባይነቱን አስመስክሯል፡፡

No comments:

Post a Comment