Friday, August 26, 2016


ሻደይ 2008 ፌስቲቫል በድምቀት ተከበረ፡፡
Photo: shaday festival 2016 wagehimera zone
ሻደይ 2008 የባህል ፌስቲቫል በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን መዲና በሰቆጣ ከተማ ከነሐሴ 14 ቀን እስከ 16 2008 ዓ.ም. በድምቀት ተከብሯል፡፡"የሻደይ ባህላችን ለዘላቂ ልማታችን" በሚል የተከበረው ይህ በዓል የተለያዩ ዝግጅቶችን ያካተተ ሲሆን በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች የታደሙበት ነው፡፡



በአማራ ክልል ከአዲስ አበባ 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ የዋግ ሹሞቹ መናገሻ ታሪካዊቷ የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን መዲና ይህንን ዓመታዊ ኩነት በድምቀት አስተናግደዋለች፡፡ የመሰረተ ልማት ጉብኝቶች፣ አውደ ጥናት፣ ባህላዊ ትዕይንቶችና ሌሎች በርካታ ክዋኔዎችን ያካተተው ሻደይ 2008 ዓመታዊ ፌስቲቫል ላይ የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኢንጅነር አይሻ መሐመድን ጨምሮ በርካታ እንግዶች የታደሙበት ነበር፡፡
ይህ በዓል መንፈሳዊም ባህላዊም ትርጓሜ አለው፡፡ ከፍልሰታ ጾም፣ ከኖኅ ቃል ኪዳንና ከዮፍታሄ ታሪኮች ጋር ቁርኝት ያለው ሲሆን በዋናነት ልጃገረዶች ለቀናት ዝግጅት አድርገው ያከብሩታል፡፡ ሻደይ ማለት በኽምጣጋ ቋንቋ ለምለም ወይም አረንጓዴ ማለት ነው፡፡ ልጃገረዶች ቅጠሉን አገልድመው፣ በባህላዊ አልባሳት ተውበው፣ በማራኪው የዋግ ባህላዊ ጨዋታዎች እየደመቀ ነው፡፡

በዋግኽምራ ብሔረሰብ ባህላዊ ህግ ዙሪያ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ማዕከል ለአንድ አመት ሲደረግ የነበረው ጥናት ተጠናቆ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በአደባባዮች ላይ የተካሄደው ባህላዊ ትዕይንት ማራኪና ደማቅ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በቀጣይ የሻደይ፣ አሸንዳና አሸንድዬ በዓላትን በጥምረትና በአንድ ፓኬጅ በዓለም ወካይ የሰው ልጆች የቅርስ መዝገብ ለማስመዝገብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እሴቶቹን በማጥናት ስራውን መጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment