Thursday, August 4, 2016


                       ኦይዳ ወረዳ
 

የኦይዳ ወረዳ በጋሞ ጎፋ ዞን ከሚገኙ አስራ አምስት ወረዳዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የወረዳው ዋና ከተማ ሸፊቴ ይባላል፡፡ ወረዳው የተመሰረተው በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡ ኦይዳ ማለት ለም ማለት ሲሆን የብሔረሰቡና የወረዳው መጠሪያም ነው፡፡ ወረዳው በሃያ ቀበሌያት የተዋቀረ ሆኖ በደቡብ ኡባ ደብረ ፀሀይ፣ በሰሜን ገዜ ጎፋ፣ በምዕራብ ሰሜን አሪ እና በምስራቅ ደግሞ ደንባ ጎፋ ወረዳ ያዋስኑታል፡፡


የኦይዳ ወረዳ ከአዲስ አበባ በ531 ኪ.ሜ.፣ ከክልሉ መቀመጫ ከሀዋሳ በ319 ኪ.ሜ. እንዲሁም ከዞኑ መቀመጫ ከአርባ ምንጭ በ267 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው የቆዳ ስፋት 133.97 ሄክታር ሲሆን የወረዳው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተራራማ 36%፣ ሜዳማ 25% እና ወጣ- ገባ 39% ነው፡፡ አየር ንብረቱም አማካይ የሙቀት መጠን 24ċ፣ አማካይ የዝናብ መጠን ዝቅተኛው 1100 ሚ.ሜ.፣ ከፍተኛው 1500 ሚ.ሜ. ይደርሳል፡፡ የመሬት አቀማመጡ ከባህር ጠለል በላይ ዝቅተኛው 1260 ሜትር ከፍተኛው 3002 ሜትር ነው፡፡ ወረዳው ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱና ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት ትላልቅ ወንዞች ባለቤትም ነው፡፡ በለም አፈር የታደለው የኦይዳ ወረዳ የኢኮኖሚ መሰረቱ በዋናነት እርሻ፣ ከብት እርባታና ንብ ማነብ ሲሆን ንግድና ሌሎች መስኮችም ለወረዳው ኢኮኖሚ የድርሻቸውን ያበረክታሉ፡፡ የኦይዳ ወረዳ ልዩ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣  የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአጋጌጥ፣ የጭፈራ እና ሌሎች ተጓዳኝ እሴቶች አሉት፡፡ በወረዳው በርካታ መስህቦች የሚገኙ ሲሆን ከእነሱም ቦንብ የተፈጥሮ ዋሻና ፏፏቴ፣ የምድር እንብርት ተብሎ የሚታወቀው የዣውሻ ወይም ሳዓ - ጉልዓ ተራራ ተጠቃሽ ሲሆኑ ሌሎች ፏፏቴዎች፣ ደኖች እና ተራራም ይገኙበታል፡፡

ወረዳው የተፈጥሮአዊና ባህላዊ እና ታሪካዊ መስህቦች ባለቤት ሲሆን በተለይም ለዓይን ማራኪና አስደናቂ ዋሻዎች ፏፏቴዎችና ለጤና ተስማሚ የሆነ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ፀባይ እንዲሁም ሰው ሰራሽ የቀርሀ ደኖች መኖሩ ለኢንቨስትመንትም ምቹ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

በወረዳው ከሚገኙት መስህቦች የተወሰኑትን ስንቃኝ፡-

የቦንብ ዋሻ፡-

የቦንብ ዋሻ በኦይዳ ወረዳ በባርንዴ ንዑስ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን ከዋና ከተማው ማለትም ከሸፊቴ ያለው ርቀት በግምት 24 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዋሻው በውስጡ ብዙ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን የአንዱ ክፍል ስፋቱ እና ርዝመቱ 4 በ 4  ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ የሚሸሸጉበት ክፍልም አለ፡፡ የሴቶች ክፍል ከወንዶች 15 ሜትር የሚርቅ ሲሆን የወንዶች ክፍል ወደ 4 የሚጠጉ ሌሎች ክፍሎች አሉት፡፡ በመግቢያው በር ሲታለፍ ከ1000 በላይ ሰው ሊይዝ የሚችል አዳራሽ አለው፡፡ በውስጡ ግድግዳውም ሆነ ጣሪያው በድንጋይ ንጣፍ የተዋበ ነው፡፡ ዋሻው በደንና በቁጥቋጦ የተሸፈነ ሲሆን የዚህ ዋሻ አስገራሚነት በአናቱ ላይ ፏፏቴ ይገኛል፡፡ ፏፏቴውም 60 ሜትር ያህል ይረዝማል፡፡

ሞቶ ዋሻ፡-

ዋሻው የሚገኘው ከሸፊቴ ከተማ በተወሰነ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የቦታው አጠቃላይ ስፋት 2 ኪ.ሜ. ነው፡፡ ሞቶ ዋሻ በውስጡ ሦሥት ትላልቅ ክፍሎች አሉት፡፡

አንደኛው ክፍል 75 ሜትር ርዝመት እንዲሁም 10 ሜ የጎን ስፋት አለው፡፡ አዳራሹ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሺ ህዝብ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ የቀሩት ሁለቱ ክፍሎች እያንዳንዳቸው ደግሞ 15 ሜትር ስፋት አላቸው፡፡ ከሞቶ ተፈጥሮአዊ ዋሻ መግቢያ በር በስተግራ በኩል ከ35 ሜትር ከፍታ የሚወርደው ፏፏቴ ከዋሻው ጋር ሲታይ ግሩም ያስብላል፡፡ አጠቃላይ ዙሪያው በቀርከሀ ደን የተሸፈነ መሆኑም ተጨማሪ ውበትን ሰጥቶታል፡፡ በኢጣሊያን ጦርነት ግዜ የአካባቢው ማህበረሰብ ከነንብረታቸው ይሸሸጉበት የነበረና ጠላታቸውን ይከላከሉበት እንደነበረ የአካባቢው አባቶች ይናገራሉ፡፡ እስከ መስህቡ ድረስ የሚያደርስ መንገድ መኖሩ መስህቡን ለመጎብኘት ምቹ ያደርገዋል፡፡

ሱቦ አምዲላ ዋሻ       

ይህ ዋሻ የሚገኘው በዚሁ በኦይዳ ወረዳ በሱቦ እና በባጋራ ቀበሌ ድንበር ላይ ሲሆን ከወረዳው ዋና ከተማ ሸፊቴ በግምት 12 ኪ.ሜ ያህል ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዋሻው በፊት ግዜ ከጣልያን ወረራ ለመሸሸግያነት የሚጠቀሙት እንደሆነና ከዚያም ለተወሰነ ዓመታት በውስጡ አራዊቶች ይኖሩበት እንደነበር ይነገራል፡፡

ዋሻው በውስጡ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ሁለት በ 3 ሜትር የሆነ ስፋት አለው የመግቢያው በር 4 ሜትር ይሆናል፡፡

ዋሻውን ስንመለከት ከአንድ ድንጋይ የተሰራ ይመስላል ግድግዳውም ሆነ ጣሪያው ከአንድ ንጣፍ የተሰራና አስገራሚ ተፈጥሮ ያለው ሲሆን በግራና በቀኝ በሰብሎች የተከበበ ነው፡፡ በተጨማሪም በዋሻው አናት ላይ ያለው ፏፏቴ ሌላ ውበትን አጎናፅፎታል፡፡ ፏፏቴው 6 ሜትር አካባቢ ሲሆን በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አርሷደሮች ውሃውን ለመጠጥነት ይጠቀሙበታል፡፡

ወርባንድ ዋሻና ፏፏቴ

ከሽፊቴ ከተማ በ6ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ቃምኦ ሾምባ ቀበሌ ከሚገኙ መስህቦች ወርባንድ ሆምኢ /ወርባንድ ዋሻ እና ፏፏቴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እነዚህ ተፈጥሮአዊ መስህቦች ማለትም ፏፏቴ ከዋሻው ጋር በማበር በተፈጥሮአዊ ውበቱ የሰውን መንፈስ ተቆጣጥሮ የመማረክ አቅሙ ያስደምማል፤ ፏፏቴው በግምት ወደታች 30 ሜትር ያህል እየተወረወረ ከመሬት ሲጋጭ የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በፏፏቴው ውበት ተደመው ሳይጨርሱ 5.5 ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ያለው ዋሻ ይገኛል የዋሻው የውስጠኛው ክፍል እንደሰው መኖሪያ ንፁ እና ፅዱህ ነው፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች ሲናገሩ ዋሻው በኢጣልያ ወጊያና ከጋሞና ከጎፋ /ከኢባ/ ጋር  በነበረው ውጊያ ጊዜ ለአካባቢው ህብረተሰብ መሸሸጊያ ሆኖ እንዳገለገለእያስረዱ በአሁኑ ሰዓት በወጣቶች እና ሙሽሮች /ጫጉላ/ መዝናኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሀገሩ ሽማሌዎች አስረድተዋል፡፡

ቶንኖት የተፈጥሮ ደን

በወረዳው ከሚገኙ ተፈጥሮአዊ መስህቦች አንዱ የሆነው የቶንኖት ደን ከወረዳ ዋና ከተማ በሽፊቴ 20 ኪ.ሜ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ የደኑ አጠቃላይ ስፋት በግምት 7 ኪ.ሜት ስኩዌር ሲሆን የደኑ ከፍታ ከ2500-3000 በሚደርስ የከፍታ ጣሪያ በር ትገኛለች፡፡

በደኑ ውስጥ የተለያዩ የዕፅዋት እና የእንሰሳት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በሀገራችን ብቸኛ የሆነውን በአሁኑ ሰዓት እየጠፋ የሚገኘውናለመድሀኒትነት የሚያገለግለው የኮሶ ዛፍ በብዛት ሲገኝ ከዱር እንሰሳትም እንደ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ጉሬዛ፣ ነብር፣ እና የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በፊት በአካባቢው ህብረተሰብ ደኑ በባላዊ መንገድ ተጠብቆ እንደቆየ ይነገራል፡፡

የወረዳው የኢንቨስትመንት አማራጮች

ወረዳው በተፈጥሮ የበለፀገ እና አየሩም ምቹ መሆኑ በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ስራ መስራት ያስችላል፡፡ በወረዳው ከሚመረቱ የግብርና ውጤቶች መካከል በጥራጥሬ ምርት፣ በቅባት እህሎች፣ በዶሮ እርባታ፣ በከብት እርባታ ሰፊ አማራጮች የሚገኙበት ወረዳ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment