Tuesday, February 23, 2016


ለ74ኛ ጊዜ የተካሄደው የኦሮሞ ብሔር የጉጂ የገዳ ሥርዓት የስልጣን ሽግግር በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ፡፡
 

በኦሮሞ ብሔር ባህል በየስምንት ዓመቱ የሚከናወነው የገዳ ሥርዓት የስልጣን ሽግግር ለ74ኛ ጊዜ እጅግ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት በጉጂ ዞን ሜኤ ቦኮ የካቲት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያን አልፎም አፍሪካ የዲሞክራሲ እሴት ቀደምት ባለቤት መሆኗን የሚያሳየው ይህ ታላቅ ባህላዊ ክንዋኔ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር የተከበሩ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን ለ74ኛ ጊዜም እነሆ ዛሬ በስልጣን ላይ የቆየው ለአዲሱ አመራር ስልጣኑን አስረክቧል፡፡ ከአዲስ አበባ 425 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሜኤ ቦኮ ኩነቱን በድምቀት አስተናግደዋለች፡፡
 
ከስልጣን ሽግግሩ በፊት ለአምስት ተከታታይ ቀናት የጉሚ የምክክር ጉባኤ ስነ ስርዓት ከተከናወነ በኋል ባለፉት ስምንት ዓመታት ባህላዊ የአስተዳደር ስልጣኑን ይዞ የቆየው ዳለና ለሀርሙፋ ስልጣኑን አስረክቧል፡፡ ገዳ ለሰው ልጆች ሁሉ ትርጉም ያለው ባህል ነው በሚል ዩኔስኮ በወካይ ቅርስነት እንዲመዘግበው የቀረበውን ጥያቄ ለማሳካትም በተለያዩ አካላት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

 

No comments:

Post a Comment