Tuesday, August 18, 2015

የሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ ምደባ ውጤት ይፋ ሆነ፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጋር በመሆን ከሚያዚያ 1ቀን 2007ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የሚገኙ ሆቴሎችና ሪዞርት ላይ በኮኮብ ደረጃ የመመደብ ስራ የጀመረ ሲሆን በቅድሚያም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች ላይ የደረጃ ምደባ ስራው ተከናውኗል፡፡ በዚህም መሰረት በኮኮብ ደረጃ የመመደቡ ስራ ተጠናቆ ውጤቱ ነሐሴ 2,2007 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ሆኗል፡፡ 

የዓለም ዓቀፍ የምዘና ቡድኖች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ 123 ሆቴሎች ላይ በተዘጋጀው አለም አቀፍ የሆነ የሆቴሎች መገምገሚያና የኮከብ ደረጃ መወሰኛ መስፈርት መሰረት የደረጃ ምደባ አድርገዋል፡፡ከ123 ሆቴሎች ውስጥ 3 ሆቴሎች ባለአምስት ኮከብ፣11ሆቴሎች ባለ አራት ኮከብ፣13 ሆቴሎች ባለ ሶስት ኮከብ፣10 ሆቴሎች ባለሁለት ኮከብ ፣1ሆቴል ባለ አንድ ኮከብ በጥቅሉ 38 ሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ ሲያገኙ የተቀሩት ሆቴሎች ማሟላት የሚገባቸውን ነገሮች ሳያሟሉ በመቅረታቸው ኮከብ አልባ ሊሆኑ ችለዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር የሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ ምደባ መከናወኑ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ፣ጎብኚዎች እንዲሁም ወደሀገራችን የሚመጡ እንግዶች እንደፍላጎታቸው አማራጭ የመስተንግዶ ተቋማት እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል እንዲሁም የውድድር መንፈስ ስለሚፈጥር የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና ገቢያቸውም ከፍ እንዲል ያደርጋል በዋናነትም ለሀገር ገፅታ ግንባታ የሚሰጠው አስተዋፅኦ የላቀ ነው ብለዋል አክለውም ሂደቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊት በራስ ኃይል የሆቴሎችን ደረጃ ምደባ ለማከናወን ልምድ ያገኘበት፣የሆቴሎች ባለንብረቶች ያሉባቸውን ጉድለቶች አይተው ለማሻሻል ዕድል ያገኙበት፣ የሆቴሎች አስተዳዳሪዎች በቂ የዕውቀት ሽግግር የቀሰሙበት በአጠቃላይ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዕድል የተፈጠረበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ከምደባው በዋላ ቅሬታ ያላቸው ባለ ሆቴሎች ቅሬታቸውን አቅርበው እንደአስፈላጊነቱ እንደገና የመመዘን ስራ ይከናወናል፡፡የቅሬታ የማቅረቢያው ቀናት ሲጠናቀቅ የኮኮብ ደረጃቸውና ሰርተፍኬት ለሆቴሎቹ ይሰጣል፡፡ በቀጣይም በተመረጡ ክልሎች ላይ የደረጃ ምደባ ስራ ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment