Tuesday, May 29, 2012



የአቡኑ ከተማ

በሰሜን ሸዋ ዞን .. ከደጋማው የመንዝ ምድር .. ተፈጥሮው በብዙ ከሚተርክበት .. መልከአ-ምድር መሃል በዚያ ንጹህ አየር በሚሳብበት ውብ ምድር የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡

ሰላድንጋይ የዚህ ድንቅ ስፍራ መጠሪያ ነው፡፡ ከሰሜን ሸዋ ዞን መዲና ከደብረ ብርሃን ከተማ በ75 ከ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሰላ ድንጋይ ኢትዮጵያን ለ38 ዓመታት በፓትሪያሪክነት ያገለገሉት አባት የአቡነ ማቴዎስ የመንበር ጵጵስናቸው መቀመጫ ነበረች፡፡

 ግብጻዊው ፓትሪያሪክ አቡነ ማቴዎስ በዚሁ ስፍራ በ1875 ዓ.ም የማርቆስ ቤተ-ክርስቲያንን አሰርተዋል፡፡


በአቡነ ማቴዎስ የተሰራው የማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ህንፃ በተሰራ በ25 ዓመቱ በመብረቅ አደጋ ፈርሷል፡፡ እንደ ብዙ የቅርስ አጥኚ ባለሙያዎች አስተያየት ቀድሞ የተሰራ የማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ህንፃ አሰራር ጥበቡ ድንቅ ነበር የሚል ሲሆን በመብረቅ ከመውደሙ ጋር ተያዞ በ1900 ዓ.ም ነበር በድጋሚ በንጉስ ምኒሊክ ትዕዛዝ በድጋሜ የታነፃው፡፡

ለሁለተኛ ግዜ በንጉስ ምንሊክ አማካኝነት የታነፀው የማርቆስ ቤተ ክርስቲያስ ህንጻ በንጉስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስለ ነበር በድንቅ ሁኔታ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ ግማሽ መንፈቅ ብቻ ፈጅቶበታል፡፡ ይኸው ደብር የሚያዝያ ማርቆስ ዕለት (ሚያዚያ 30) ንጉሱና አቡኑ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተባርኳል፡፡

የሰላ ድንጋይ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ከህንፃው የአስተናነፅ ጥበብ ህንፃውን ለመስራት ከተጠቀሙበት ቁሳቁስና በየዘመናቱ በነበሩት ታሪኮች ስፍራው የተለየ ቦታ እንዲሰጠው አድርገውታል፡፡

ለመንበረ ጵጵስናቸው መቀመጫ አድርገው የመረጡት አቡነ ማቴዎስ ለመቀመጫነት ከግብፅ አስመጥተውት የነበረው ወንበራቸው ዛሬም ድረስ አለ፡፡ በቀደመው የሸዋ ነገስታት ዘመን የወይዘሮዎች መዲና በመባል የምትታወቀው እና በታሪክ ጉልህ ስም ያላት የሰላ ድንጋይ የሸዋው ንጉስ የንጉስ ሣህለ ስላሴ እናት ስም የምትጠራው ሰገነት በራሳቸው በወይዘሮ ዘነበወርቅ እንደተሰራች ይነገርል፡፡አቡነ ማቴዎስ በዚህች ሰገነት ላይ ይቀመጡባት ነበር፡፡

አብዛኛዎቹ የሸዋ ነገስታት ቆነጃጅት ሚስቶቻቸውን ያስቀምጡባት የነበረች ስፍራ በመሆኗ የወይዘሮዎች ከተማ የሚል ስያሜ ቢሰጣትም ሰላ ድንጋይ የእምነትና የፖለቲካ ማዕከል ነበረች፡፡ በዚሁ ስፍራ የምትገኘውና የደብረ ምጥማቅ ጽላት ተሰውሮባታል የሚባለው ፃድቃኔ ማርያም የስፍራውን የቅርስ ማዕከልነት ከሚያሳዩ ማስረጃዎች አንዱ ነው፡፡ አፄ ዘርዓያቆብ ወደ ሸዋ በወረዱ ግዜ ለማረፊያነት የሚጠቀሙበት ቤተ መንግስታቸውም በዚሁ በሰላ ድንጋይ ይገኛል፡፡

አፄ ዘርዓያቆብ ቤተ መንግስታቸውን ቀልሰው በነበረበት ስፍራ አቅራቢያ የምትገኘው ጥንታዊቷ ደብረ ምጥማቅ በ1426 እስከ 1460 ባለው ግዜ የተመሰረተች ታሪካዊ ስፍራ ናት፡፡

ሰላ ድንጋይ የኃይማኖታዊ ጉባኤዎች ማዕከልም ሆና አገልግላለች፡፡ በ1442 ዓ.ም የተደረገውና ከመቶ ዓመት በላይ በቅዳሜ ሰንበትነት ዙሪያ ይደረግ የነበረው ክርክር በአፄ ዘርዓያቆብ አማካኝነት የሃገሪቱ ሊቃውንት በተገኙበት በደብረ ምጥማቅ የተካሄደ ጉባኤ ነበር፡፡

ከ 1276 ዓ.ም ጀምሮ ይነሳ የነበረውን ይከን የቅዳሜ ሰንበትነት ጉዳይ ለመጨረሻ ግዜ እልባት እንዲያገኝ ያስቻለው ጉባኤ የተካሄደበት ደብረ ምጥማቅ የያኔው ህንፃዋ ፈራርሶ ፍርስራሹ ዛሬም ይታያል፡፡

No comments:

Post a Comment