Thursday, May 17, 2012


የሥነ-ጽሁፍ ሃብቶቻችን የቅርስነት ዋጋቸው….. በዜጎች ተመዝኖ ይሆን

ብራና
ቅርስ የአንድ ህዝብ ማንነት ነው፤ ከቅርሱ ጀርባ የቅርሱ ባለቤት የሆነው ህዝብ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣እሴቶችና መገለጫዎቹ አሉ፡፡ ለዚህም ነው ቅርሶች ባለቤታቸው ከሆኑ ህዝቦች ህልውና ተለይተው የማይታዩት፡፡ ከቅርስ ጋር ተያይዞ በሃገራችን ያለው አስተሳሰብ ቅርስን ከሥነ-ህንጻ ጥበብ ጋር ብቻ በማቆራኘት የመፈረጁ ባህል ከዘርፍ ጋር በቂ ግንዛቤ በሌላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ባለሙያም በሆኑ አካላት ጭምር እየተስተዋለ ነው፤ ለዚህም ነው የጽሁፍ ቅርሶቻችን ስንል ስለ ጽሁፍ ሃብቶቻችንና ስለ ቅርስነት ይዘታቸው ማንሳት የፈለግንው፤


የጽሁፍ ቅርሶችን በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ሰጥቶ የሚመዘግበው ሚሞሪ ኦፍ ዘ ወርልድ/memory of the world/ ነው:: ሚሞሪ ኦፍ ዘ ወርልድ ቅርሶች ለሰው ልጅ በሚኖራቸው ፋይዳ፣ በታሪካዊነታቸው፣ በኖሩበት ዘመን፣በያዙት እውቀት/ይዘት/፣ በመነሳት መዝኖ እውቅና ይሰጣቸዋል፤ በቅርስነትም ይመዘገባቸዋል፡፡ ይህ ተቋም የላቀ ፋይዳ ያላቸው የጽሁፍ ቅርሶች በመላው ዓላም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ካለው ዓላማ የተነሳ የጽሁፍ ሃብቶቹን ቅጂና ካታሎጋቸውን ወደ ዲጅታል እንዲቀየሩ በማድረግ በድህረ-ገጽ ጭምር እንዲለቀቁ ያደርጋል፡፡

በ1982 እ.ኤ.አ የተቋቋመው ሚሞሪ ኦፍ ዘ ወርልድ ዩኔስኮ በዓለም ላይ ያለው የጽሁፍ ሃብት ተገቢ ባልሆነ አቀማመጥ መቀመጡና ቅርሶቹ በተለያየ አደጋ መጥፋታቸው ሲያሳስበው ይህን ችግር ለመቅረፍና የጽሁፍ ቅርሶችን ለመጠበቅ በማሰብ ነበር ያቋቋመው፡፡

ዩኔስኮ በዚህ መሰረት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቀዳሚ በማድረግ ያስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች ውስጥ የስነ-ጽሁፍ ቅርሶችን የመለየትና በዓለም የሥነ-ጽሁፍ ቅርስነት የመመዝገብ፣ ምዝገባውን በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ማድረግ፣የአህጉርዊ ምዝገባን ስልት ማስቀመጥ፣በሃገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ በብሄራዊ ኮሚቴ አማካኝነት ብሄራዊ ምዝገባ ማካሄድ፣ የጽሁፍ ቅርሶች እንዲጠበቁ ግንዛቤ የሚሰጡ ስልቶችን በመንደፍ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የጽሁፍ ቅርሶች እንደሌላው ቅርሶች ሁሉ የአንድ ሃገር ሃብት በመሆናቸው ከስርቆት፣ከተለያዩ አደጋዎች ተጠብቀው እንዲኖሩ ማድረግና ማስጠበቅ፣የተጠበቁት የጽሁፍ ቅርሶች ለተጠቃሚዎች ምቹ በሆኑ መንገዶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይገኙበታል፡፡

የጽሁፍ ቅርሶች ለምዝገባ እንዲበቁ ከሚያደርጉ መመዘኛዎች ውስጥ እውነተኛነታቸው፣ሊተኩ የማይችሉ መሆናቸው፣ የተጻፍበት ግዜና ቦታ፣ርእሰ ጉዳያቸውና የአጻጻፍ አይነታቸው ከብዙ መመዘኛዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከላይ በገለጽናቸው መመዘኛዎች ፋይዳቸው ልቆ በመገኘቱ በሃገራችን ካሉ የጽሁፍ ቅርሶች ውስጥ አስራ ሁለት የሚደርሱት በዓለም የጽሁፍ ቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዝገበቻቸው የጽሁፍ ቅርሶች የአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን አርባዕቱ ወንጌል፣የአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን የጳውሎስ መልእክት፣የአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ግብረ-ህማማት፣በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የህትመት መጽሐፍ የሆነው መዝሙረ ዳዊት፣ የአጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግሰት ለቪክቶሪያ የጻፉት ደብዳቤ፣ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ለሞስኮው ቄሳር ዳግማዊ ኒኮላስ የላኩት ደብዳቤ፣ ከሸዋው ንጉስ ሳህለስላሴ ለእንግሊዝ ንግስት የተላከ ደብዳቤ፣ታሪክ ዘ-ምኒልክ፣መጽሐፈ ሄኖክ፣ታሪክ ነገስት፣ቅዳሴ፣ፍትሃ ነገስት ናቸው፡፡

በሃገራችን ያሉት የጽሁፍ ቅርሶች በዓይነትም ሆነ በይዘት በርካታ ናቸው፡፡ ገና በርካታ የጽሁፍ ቅርሶችን የማስመዝገብ እድል አለን፡፡ እስላማዊ የጽሁፍ ቅርሶቻችን ተለይተው እንኳን አልታወቁም፣አሁን አሁን የካበተ እስላማዊ የጽሁፍ ቅርስ እንዳለን ለመረዳት ችለናል፡፡ በሌላ በኩል ታሪካዊ ፋይዳቸው የጎላ ሃገር በቀል ድንቅ ጥበቦችን የታጨቁ አያሌ የብራና መጻህፍት አሉን፣ እነዚህ ሁሉ መጠበቅ ከቻሉ ትውልድ ለዓለም ሊያበረክታቸው የሚችሉ የቅርስ ሃብቶች ናቸው፡፡ የጽሁፍ ቅርሶች እንደ ሥነ- ህንጻ ካሉ የቅርስ ሃብቶች የሚለዩት ሥነ-ህንጻ ጥበብ እውቀትን ጭምር መያዝ የቻሉ ሁለገብ የማንነት አሻራዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ትኩረት ለጽሁፍ ቅርስ ሃብቶቻችን!!!

No comments:

Post a Comment