Friday, October 6, 2017



የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል /ሄቦ/


በየም ብሔረሰብ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ባህላዊ በዓላት አንዱ ሄቦ ነው፡፡ በጉጉት የሚጠበቅና ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎበት የሚከበረው የሄቦ በዓል የተጀመረበት ትክክለኛ ጊዜ ባይታወቅም ከጥንት ጀምሮ የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ  ሲከበር የመጣ በዓል ነው፡፡


በሀገራችን በስፋት የሚታወቀው የመስቀል በዓል በየም ብሔረሰብ ከሄቦ በዓል ጋር አብሮ የሚከበር ቢሆንም የሄቦ በዓል ሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ከሚያከብሩት የመስቀል በዓል የተለየ ባህላዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ ይህ በዓል መሠረቱ ከብሉይ ኪዳን የአይሁድ እስራኤላውያን ጋር የሚገናኝበት አጋጣሚዎችም ይታዩበታል፡፡ የሄቦ በዓል የሚከበረው ለበዓሉ ጌታ ለ"ጎር" /"ሳማጎር" የሚል መጠሪያ በመስጠት ነው፡፡
የሄቦ በዓል አመት ሲቀረው በዓሉ ተከብሮ እንዳለፈ ለቀጣዩ በዓል ዝግጅት ለማድረግ ገንዘብ ከመቆጠብ ይጀመራል፡፡ ለምሳሌ አባወራው ከመስከረም 30 ጀምሮ ከመንደሩ አባወራዎች ጋር በመሆን ለእርድ ሰንጋ መግዣ ማጠራቀም የሚጀምረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ እማወራዎችም ሆኑ ወጣቶች ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን ለመግዛት አስቀድመው ይቆጥባሉ፡፡ በዓሉ ሦስትና ሁለት ወራት ሲቀሩት የቤተሰቡ አባላት የሚጠበቅባቸውን የስራ ድርሻ ማከናወን ይጀምራሉ፡፡
ወንዶች "ጎቶ" /የማገዶ እንጨት/ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ወቅት በየም ብሔረሰብ ባህል ለእንጨት ሰበራ ወደ ጫካ አይኬድም፡፡ የማገዶ እንጨቱ ለበዓሉ ሁለር ወር ሲቀረው ይፈለጥና በጎዶ ቅርጽ ተከምሮ እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ይህን "ጎቶ " የሚያዘጋጁት ወንዶች ማለትም አባወራውና ወጣቶች ሲሆኑ በዚህ ወቅት እረኞች በሄቦ በዓል የሚዜሙ ዜማዎችን እየመረጡ በማዜም የበዓሉን መቅረብ ያበስራሉ፡፡
ይህ በዓል የጥጋብ በዓል ነው፡፡ በበዓሉ ሰሞን ሰውም እንስሳም አይራብም፡፡ ከበዓሉ መድረስ ሦስትና ሁለት ወራት በፊት ለእንስሳት መኖ ይዘጋጃል፡፡ ይህ ከለመለመ የመኖ ሳር ታጭዶ በበረታቸው ውስጥ ተቀምጦ ቢያንስ ከሳምንት በላይ እንዲመገቡት ይደረጋል፡፡ ሄቦ እስኪያልቅ እንሰሳት በለመለመ ሳር ይታገዳሉ፡፡ ለሄቦ በዓል ለከብቶች የተለየው ሳር በሚለመልምበት ቦታ የባለቤቱም ሆነ የሌላ ሰው ከብት እንዳይገባ የክልከላ ምልክት ይሆን ዘንድ ረዘም ያሉ እንጨቶች በግጦሽ ሳሩ መካከል ይተከላሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች "ዛዞ" ይባላሉ፡፡ በዓሉ ሁሉም ነገር ጽዱና አዲስ ሆኖ የሚታይበት እንዲሆን የብሔረሰቡ አባላት ግቢያቸውን በአዲስ አጥር ያረጥራሉ፡፡ ይህንን አጥር የማጠሩ ኃላፊነትም የወንዶች ነው፡፡
"የዱዋ ዝግጅት"
በሄቦ በዓል ሰሞን እሳት ከቤት ስለማይጠፋ በዓሉ እስኪጠናቀቅ የሚቆይ ሲያልቅ ሲያልቅ በሌላ የሚተካ "ዱዋ" ወፍራም የማገዶ ግንድ ጉማጅ ተዘጋጅቶ ምድጃ ውስጥ ከምሰሶ አጠገብ በጓዳ በኩል ይቀመጣል፡፡ ዘመድ አዝማድ ከያለበት አካባቢ በዓሉ አስራ አምስት ቀን እና ሳምንት ሲቀረው ከቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር በጋራ ለማክበር ይሰበሰባሉ፡፡ በሄቦ በዓል የሚጠጣው ባህላዊ የየም ብሔረሰብ መጠጥ "የማ ኡሻ" /ችፋ/ ቦርዴ ይባላል፡፡
የሄቦ በዓል መከበር የሚጀምረው መስከረም 14 ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን "ካማ ኬሳ" ይባላል፡፡ "ካማ" ማለት ማር ሲሆን "ኬሳ" ማለት ደግሞ መውጣት ማለት ነው፡፡ ወደ አዲስ አመት ለመግባት ቂምና ቅሬታን በማስወገድ መቀደስን የሚያመላክት ሲሆን ቅራኔና የሰነበተ ቂም በሽማግሌዎች አማካይነት እርቀ ሰላም ወርዶ የሚወገድበት ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው፡፡
ኢፍቲ /የንፃት ቀን
በየም ብሔረሰብ የግልም ሆኖ የአካባቢው ንጽህና መስከረም 15 ቀን ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ቀን "ኢፍቱ" ይባላል፡፡ በክረምት ለግጦሽ ወደ ቆላ የሄዱ ከብቶች ወደ ሰፈር የሚመለሱበት ነው፡፡ ለሄቦ በዓል የተዘጋጀው ምግብ ሲበላ ምንም ዓይነት የሆድ ህመም እንዳይከሰት እና የምግብ ፍላጎት እንዳይጠፋ ጎመንና "ኖዕሜያ" የተባለ የተክል ቅጠል ተከትፎ ከቆጮና ቡላ ፍርፍር ጋር ተቀላቅሎ የተሰራ ገንፎ "ዳኣ" በበርበሬ /ዶቆ/ የሚበላበትም ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቀደም ሲል ተፈልጦ የተከመረውን ጎቶ ወንዶች ሄደው ከተከመረበት ያመጣሉ፡፡ ኮበና /የቆጮ ድፎ/ ይጋገራል፡፡
አሜቱ /የሄቦ ዋዜማ/
መስከረም 16 ቀን "አሜቱ" የተባለው የሄቦ በዓል የዋዜማ ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን የበዓሉ ጌታ "ሳማ ጎር" አቀባበል ይደረጋል፡፡ በዕለቱ በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የቤት አባወራና እማወራዋ የተቀቀለ የአምቾ መሥዕዋት ያቀርባሉ፡፡ እንሰት ከተቀቀለ በኋላ በእንሰት ቅጠል በመያዝ እማወራዋ በጓሮ በኩል አባወራው ደግሞ በፊት ለፊት በኩል በመውጣት በየግላቸው ጓሮአቸው ላይ በመበተን የበዓሉ ጌታ በሰላም እንደመጡ በሰላም እንዲሰናበቱ፣ በዓሉ የሰላምና የጤና እንዲሆን ሰውና እንስሳት ምንም ሳይጎዱ ለመጪው በዓል በሰላም እንዲደርሱ ምስጋናና ጸሎት በማቅረብ አቀባበል ያደርጋሉ፡፡  ዕለቱ የጾም ቀን ካልሆነ በስተቀር አባወራው የቅርጫ ስጋ ያመጣል፡፡ በዕለቱ ለእርድ የሚውለው ከብት ለሄቦ በዓል ተብሎ በመቆጠብ ከተገዙት ሁለትና ሦስት ከብቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ቀን ያለው ለሌለው በመስጠት ሁሉም በመተሳሰብና በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚደረግበት ቀን ነው፡፡
የሄቦ በዓልና የደመራ ሥነ-ሥርዓት
ለደመራ ሥርዓቱ አንድ ሳምንት ሲቀረው ወንዶች ወደ ጫካ በመሄድ ለደመራ የሚሆን እንጨት ሰብረው ይመጣሉ፡፡ ወደ እንጨት ሰበራው ሲሄዱም ከቀንድ በተሰራው ቱቱሩ /መለከት/ ድምጽ እየጨፈሩ ነው፡፡ ደመራው ሁለት ቦታ ይደመራል፡፡ አንዱ በጋራ በሚጨፈርበት ቦታ /ካኛ/ ላይ ተዘርግቶ እንዲደርቅ ከተደረገ በኋላ መስከረም 16 ቀን አሜቱ በሚባለው ዕለት ትንሽና ትልቅ ሆኖ ይደመራል፡፡ ሌላኛው በየደጃፍ በወጣቶች ቡድን የሚደመር ሲሆን በዕለቱ ከ12፡30 እስከ 1፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ ከየቤቱ ችቦ ይለኮሳል፡፡ በዚህ ጊዜ "ዳሲን ማካ ኬስ፣ ማካ ኬስፋን ጋዋ ጊሩን" ትርጉሙም ከጓዳ ረሃብ ውጣና ጥጋብ ይግባ ማለት ነው፡፡ እንደገናም "ሚዳሲን ማካ ኬስፋን ጋዋ ጊሩን" ይላሉ ከበረት ውስጥ ረሃብ ውጣና ጥጋብ ይግባ ማለት ነው፡፡ የችቦውን እሳት በጓዳ፣ በከብቶች በረትና በመኝታ አካባቢ በማዟዟር ረሃብ ውጣና ጥጋብ ግባ እያሉ በማውጣት የመንደር ደመራው ወደ ተደመረበት ቦታ ያሆያ-ያሆያ የሚለውን የቡሄ ጭፈራ እየጨፈሩ ይሄዳሉ፡፡ ደመራው ይለኮሳል፡፡ በመጨረሻም ሽማግሌዎች ከመረቁ በኋላ ለእራት ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡   
ወደየቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ሁሉ ተሰብስበው ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብ ይመገባሉ፡፡ ከዚያም በኋላ የመኝታ ሰዓት ሲደርስ ቅቤ ይታደላል፡፡ ሁሉም ሰው እግሩንና ገላውን የታደለውን ቅቤ ተቀባብቶ ይተኛል፡፡ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ቀድሞ የተነሳ የቱሩሩ /መለከት/ ድምጽ በማሰማት ወደ ካንቻ ይሄድና ትንሹን ደመራ ለኩሶ እየጨፈረ ሌሎች የቱሩሩውን ድምጽ እንደሰሙ ከየቤታቸው ችቦ እየለኮሱ ለሁለተኛ ጊዜ ካንቻ በጋራ በተደመረው ደመራ ቦታ ተስባስበው "ያሆያ፣ ያሆያ" በማለት እየጨፈሩ ቆይተው ሊነጋ ሲል የአካባቢው ሽማግሌዎች መጥተው ከመረቁ በኋላ ሁለተኛው ትልቁ ደመራ ተለኩሶ ጭፈራው እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ ይቀጥላል፡፡
ኢሶንሲ ፊና /የሄቦ በዓል/ የመጀመሪያ ዕለት
መስከረም 17 የሄቦ በዓል የመጀመሪያው ዕለት ነው፡፡ በየም ብሔረሰብ ባህል ከዚህ ቀን ጀምሮ ኢሶንሲ ፊና ወይም የመጀመሪያው ፊና እየተባለ መቆጠር ይጀምራል፡፡ እንዲህ እየተባለ የሚቆጠረው እስከ መስከረም ሰላሳ ነው፡፡ ፊና ማለት ከቅርቀሃ የሚዘጋጅ የብሔረሰቡ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ሲሆን የተለያየ መጠን አለው፡፡ ቅኝቱም የተለያየ ነው፡፡ በሄቦ በዓል ወቅት ብቻ ባማረ ሁኔታ ይቀኝበታል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያው ሁሉንም አሳታፊ ከልጅ እስከ አዋቂ ሴቶችም ጭምር የሚጫወቱበት ሀገረሰባዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡
ፋርዕኒ ኦቱ /መልካም ምኞት መግለጫ/
በየም ብሔረሰብ የሄቦ በዓል ወዳጅ ዘመድ እርስ በእርስ እንኳን አደረሳችሁ የሚባባልበት፣ መልካም ምኞቱን በመግለጽ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብ አብሮ የሚቋደስበት ነው፡፡ በየዓመቱም ወዳጅ ዘመዶች የሚጠያየቁበትና የሚገባበዙበት ቋሚ ቀን አላቸው፡፡ ይህንን ቀን መቅረት አይቻልም፡፡ ችግር ቢገጥም እንኳን አንድ አካል ሄዶ ሁኔታውን ማስረዳት አለበት፡፡ ይህ የእንኳን አደረሳችሁ መባባል የ"ኢሶንሲ ፊና" የሄቦ በዓል ዕለት ይጀምራል፡፡
በዚህ ዕለት ልጆች ለበዓሉ አስቀድመው ካዘጋጁት ጎቶ አንዳንድ ፍልጥ በመያዝ ወደ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በመሄድ ይዘው የሄዱትን የጎቶ ፍልጥ ወደ ቤት ይዘው እየገቡ "ችፋሶ ማአርክ ኬፕሳኒያ" /መጠጡን በሰላም ጠጣችሁ ወይ በማለት መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ የወሰዱትን ፍልጥ ወደ ምድጃውና ምሰሶ አጠገብ ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የቤቱ አባወራውና እማወራዋ "ኡሻኒስ ጎር ዎታውቶ" /ጠጥተናል ጎር ይባርካችሁ፡፡ በማለት ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይሄ በቦሄ በዓል ከወዳጅ ዘመድ ጋር የሚደረገው መገባበዝና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ልውውጥ "ፍርኒ ኦቱ" የአበባ መለዋወጥ ይባላል፡፡
የቦጋ ጨዋታ ሥርዓት



የቦጋ ጨዋታ የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ ማንም በዘፈቀደ አይንቀሳቀስም፡፡ ጨዋታውን በሥርዓቱ የሚመራ የቦጋ ጨዋታ መሪ ይመረጣል፡፡ ይህ መሪ በብሔረሰቡ ቋንቋ "አባሚላ" ይባላል፡፡ አባ ሚላ በጨዋታው መካከል ግጭት እንዳይፈጠር፣ ባለማወቅ ልጆች የጨዋታውን ሥርዓት እንዳያበላሹ፣ ጨዋታው ማን ቤት እንደሚጀመር፣ ስንት ሰዓት ተጀምሮ በስንት ሰዓት መጠናቀቅ እንዳለበት በየቤቱ የሚደረገው መስተንግዶ በሥርዓት እንዲካሄድ መመሪያ በመስጠት ይመራሉ፡፡
የሄቦ በዓል እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የአካባቢው ማህበረሰብ ተሰብስቦ በየዓመቱ በሚጫወትበት ቦታ ወይም በብሔረሰቡ ቋንቋ ካኛ /ካንቻ/ በሚባልበት ቦታ ቦጊኛዎች /የቦጋ ተጫዋቾች/ አስፈላጊውን ቁሳቸውን ይዘው ይሰበሰባሉ፡፡ የሚሰበሰቡት እስኪበዙ ድረስ የቱቱሩ /የቀንድ መለከት/ ድምጽ ያማረ ዜማ ያሰማሉ፡፡ በየቤቱ ያለውም ይህን ድምጽ በመስማት ከየቤቱ ወጥቶ ይሰበሰብና በጋሻ በነብርና በጉሬዛ ቆዳ ያጌጡ አባቶችና ታላላቆች ጨዋታውን በሰልፍ በዚግዛግ እያሰሞሰሙ በመምራት በየዓመቱ የሚባለውን የሄቦ በዓል ጨዋታ "ያሆ ያሆ ኤ ያሆ" እያሉ የጨዋታውን ዜማ በመቀያየር ከቱቱሩው /ከቀንደ መለከቱ/ ድምጽ ጋር በማዋዛት እየጨፈሩ ወደ ቀዳሚው ቤት ያመራሉ፡፡ በቤቱ በራፍ እየተጫወቱ ልጆች ከኋላ ታላላቆች ከፊት በመሆን በአንድነት ውው፣ ውው በማለት ለአጭር ጊዜ የጩኽትና የቱቱሩ /የመለከት/ ድምጽ ያሰማሉ፡፡ በሶማቸው /የቀርቀሃ ዘንግ/ መታመታ በማድረግ ቁርጥ ቁርጥ ባለ ድምጽ ውው፣ ውው እየተባባሉ የተለየ እንቅስቃሴና ትርኢት ካሳዩ በኋላ በአንድነት ቦጊኛዎች በራፍ ደጅ እየዞሩ ይጨፍራሉ፡፡
በዚህ መልኩ ከተጫወቱ በኋላ ባህላዊ መጠጡ /ቦርዴ/ የማኡሻ/ እና ምግር ኮበና ይቀርባል፡፡ ከበሉ ከጠጡ በኋላ አናታቸውን እንዲቀቡ ቅቤ ይሰጣቸዋል፡፡ አናታቸው የተቀቡትን ቅቤ ጋሻቸውን ጭምር በመቀባት "ጎር ዎታውቶ፣ ዎኔትስ ይኔትስ ካታውቶ፣ ሚያስ ፉፍና ፉቱ ኮንተፋው" "ጎር የሄቦ ጌታ ይባርክዎ፣ ዓመት ዓመት ያድርስዎ፣ ከብቶችዎ ተወልደው እንደ አሸዋ አፈር ይብዛልዎት" ብለው ይመርቃሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሚከናወነው ጨዋታ እስከ 9 ሰዓት ይቆይና ከዚያ የጋራ ጨዋታ ወደሚደረግበት ካንቻ ይመለሳሉ፡፡
በመጀመሪያው የቦጋ ጨዋታ ቀን የሀገር ሽማግሌዎች ባህላዊ ቡልኮ ወይም ጋቢ ለብሰው ጦር ይዘው የጋራ ጨዋታ በሚደረግበት ቦታ /ካንቻ/ ቦጊኛዎች /የቦጋ ተጫዋቾች/ ከቤት ለቤት ጨዋታ እስኪመለሱ ይጠባበቃሉ፡፡ ከደረሱም በኋላ በጋራ ይጮሁና የተወሰነ "የያሆ" ጨዋታ ከተጫወቱ በኋላ "የኮምሱ" ሥርዓት በሚደረግበት ቦታ ፊኖአቸውን /የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ/ ይዘው ከሀገር ሽምግሌዎች ጋር እያዜሙ ይሄዳሉ፡፡
በሄቦ በዓል የሚነፋው "ፊኖ" በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ካንቻ/የጭፈራው ቦታ/ ይቀመጣል፡፡ ጨዋታውን አቋርጦ ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ቢኖር እንኳን ፊኖውን በሚቀመጥበት የዛፍ ስር አስቀምጦ ይሄዳል፡፡ የሄቦ በዓል ጨዋታ የተጠናቀቀ ዕለት የፊኖውን ደህንነት ጠብቆ በማስቀመጥ በዓመቱ እንደገና የሚያመጣ ሰው ይመረጣል፡፡
ቻሎ ባህላዊ  ዳኝነት ጭፈራ 


የየም ብሔረሰብ ለዘመናት ለትውልድ እያስተላለፈ ጠብቆት ያቆየው የራሱ የሆነ የዳኝነትና የዕርቅ ሥርዓት አለው፡፡ ከእነዚህ ውስጥምሚላ፣ ሸኒ፣ ረጂ፣ ለጋ፣ ቶጎ፣ ጂጋ እያለ እስከ ቻሎ ባህላዊ ዳኝነት የሚባሉ የባህላዊ ዳኝነትና የዕርቅ ሥርዓቶች አሉት፡፡ አንድ ሰው "ተበድያለው ፍትህ ይገባኛል" ካለ በመጀመሪያ ለሚላ ጉዳዩን ያቀርባል፡፡ ጉዳዩ እልባት ካላገኘ ለሸኒ፣ለረጂ፣ ለለጋ፣ ለቶጎ፣ ለጂጋ እያለ እስከ መጨረሻው የቻሎ ባህላዊ ዳኝነት ድረስ ይሄዳል፡፡ የቻሎ ባህላዊ ዳኝነት የሚካሄደው ከመስቀል በዓል ጋር ተያዞ ከመስከረም 17-23 ለሰባት ተከታታይ ቀናትሲሆንበእነዚህ ቀናት እልባት ያላገኙ ጉዳዮች የሚታዩት ሚያዚያ 27 እና 28 ብቻ ነው፡፡  ይህን የባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት የሚያስፈጽሙ ከጋዘው ጎሳ የሚወከሉ “ሜን ጋኛ”፣ “አውላን ጋኛ” እና“ ኮን ጋኛ“ የሚባሉ ሦስት ዋና ዳኞች ሲሆኑ በተጨማሪም የእነዚህን ዳኞች የፍርድ አፈፃፀም የሚከታተሉ ከተለያዩ ጎሳዎች የተወከሉ 12 ሸማግሌዎች አብረው ይሰየማሉ፡፡ በዚህ ባህላዊ ዳኝነት የተለያዩ ጉዳዩች ቢታዩም በዋናነት ማስረጃየሌላቸውከፍተኛ ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ የሚያገኙበት ነው፡፡ ዳኝነቱና የሄቦ (የመስቀል) ጭፈራ ጎን ለጎን ይካሄዳል፡፡ በዚህ የባህላዊ ዳኝነት እና ሄቦ ጭፈራ ላይበሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደማሉ፡፡ዳኝነቱም የሚካሄድበት ስፍራ ከሳጃ ከተማ 38.8 ኪሎ ሜትር በሾሸር አልማማና በሰሙአዋሾ ቀበሌዎች በሚገኝ ቻሎ ቱና በሚባል ስፍራ ላይ ይካሄዳል፡፡
ይህ ሁሉ ተጠብቆ የሄቦ በዓል ልዩ ግምት ተሰጥቶት በመስከረም 17 ከሚከበረው የመስቀል በዓል ጋር በመደቀ ሁኔታ ተከብሮ እስከ ጥቅምት መግቢያ ይዘልቃል፡፡

2 comments: