Saturday, November 7, 2015

የሆቴሎች ኮከብ ደረጃ ምደባ ይፋ ሆነ



የኢ.ፌ.ድ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባሩት መንግስታት የዓለም ቱሪስት ድርጅት ጋር በመሆን ከሚያዚያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የሚገኙ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በኮኮብ ደረጃ የመመደብ ስራ የጀመረና በቅድሚያም የአዲስ አበባ ከተማ ሆቴሎች ጊዜያዊ የደረጃ ምደባ አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡

   ከጊዜያዊ የደረጃ ምደባው በኋላ በምደባው ቅሬታ ያላቸው ባለሆቴሎች ቅሬታቸውን ማቅረብና መስተናገድ እንደሚችሉ በተሰጠው እድል መሰረት በተወሰኑ ሆቴሎች የቀረቡ ቅሬታዎችን በመመልከት ለመጨረሻ ጊዜ የትኛው ሆቴል ምን ደረጃ አገኘ የሚለውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሳውቋል፡፡

 
በመጀመሪያው ዙር ለ123  ሆቴሎች በተገቢው መስፈርት ግምገማ የተደረገ ሲሆን ከ123 ሆቴሎች ውስጥ 68 ሆቴሎች በኮኮብ ደረጃ ውስጥ ሲገቡ የተቀሩት ሆቴሎች ኮከብ አልባ ሆነዋል፡፡
 
በተሰጠው የኮኮብ ደረጃ መሰረት ሸራተን አዲስ ሆቴል፣ኢሊሊ ሆቴል፣ ካፒታል ሆቴል እና ራዲሰን ብሉ ሆቴል ባለ 5 ኮኮብ ደረጃ ያገኙ ሲሆን፣ ኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል፣ ሐርሞኒ ሆቴል፣ ድሪምላይነር ሆቴል ፣ ጁፒተር ሆቴል/ ካሳንቺስ/፣ ሳሮማሪያ ሆቴል ፣ደብረዳሞ ሆቴል፣ ናዝራ ሆቴል፣ ፍሬንድሺፕ ሆቴል ፣ኔክሰስ ሆቴል ፣ዋሽንግተን ሆቴል ፣ ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ ጁፒተር ሆቴል / ቦሌ/፣ተገን ገስት አከሞዴሽን ሆቴል ባለ 4ኮኮብ ደረጃን ሲያገኙ 25 ሆቴሎች ባለ ሶስት ኮከብ ፣19 ሆቴሎች ባለ ሁለት ኮከብ ፣7 ሆቴሎች ባለ አንድ ኮከብ በጥቅሉ 68 ሆቴሎች በደረጃ ውስጥ ገብተዋል፡፡
 
ቅሬታ ያቀረቡ ሆቴሎች በሌላ ቡድን ቅሬታቸው የታየ ሲሆን አግባብ ሆኖ የተገኘው የተስተካከለበትና ቅሬታው ተገቢ ያልሆነው በዛው ደረጃ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ከ3 ዓመት በኃላ ዳግም የደረጃ ምደባ ስራ እንደሚሰራ እንዲሁም  አንድ ሆቴል ባገኘው የደረጃ ልክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በየጊዜው የሚጣራ እንደሆነና ማንኛውም በደረጃ ውስጥ ለመካተት የተገመገመ ሆቴል የቀድሞውን በማሻሻል ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችል አቅም አጎልብቻለው የሚል ከሆነ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በ 1 ዓመት ውስጥ በድጋሚ ሊታይለት እንደሚችል ተገልጻል፡፡
 
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ለሆቴሎች ደረጃ መስጠት አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው ሆቴሎች የአገር አምባሳደሮች ናቸው፡፡ የአገር መሪዎች ፣ታላላቅ ሰዎችና ቱሪስቶች ለስብሰባዎች ለኤግዚቢሽኖች እና ለኮንፈረንስ ወደ አገራችን ሲመጡ ሆቴል ውስጥ ነው የሚያርፉት ሆቴሎቹ የሚሰጡት አገልግሎት የአገር አገልግሎት ጭምር ነው፡፡ የሆቴሎችን ደረጃ ማወቅና ለዛ ደረጃ የሚመጥን አገልግሎት መስጠታቸውን ማወቅ የመንግስት ኃላፊነትም ነው፡፡ ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰራን ላለነው አጠቃላይ የአገር ገፅታን የመገንባት ሂደት በማስተዋወቅ ዙሪያ የራሱ በጎ አስተዋፅ አለው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በተመረጡ ክልሎች ባሉ ሆቴሎች ላይ የኮከብ ደረጃ ምደባው ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment