Monday, December 8, 2014


መተከል ዞን

የመተከል ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ከሚገኙት ሶስት ዞኖች አንዱ ሲሆን በሰሜንና በምስራቅ ከአማራ ክልል፣ በደቡብ፣ በካማሽ /አባይ ወንዝ/ በምዕራብ ከሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ በዞኑ በዋናነት የጉሙዝና የሽናሻ ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአገውና ሌሎች ብሄረሰቦች ማህበራዊ ትስስር በመፈጠር አብሯቸው ይኖራሉ፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ በቅርብ ጊዜ በ1993 ዓ.ም. የተቆረቆረች ከተማ ብትሆንም አካባቢዋ ለልማት ምቹ ከመሆኑ አኳያ የተፈጠረው ዕድገትና ለውጥ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
 

የዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 22.028 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን በውስጧ 7 ወረዳና 167 ቀበሌዎችን ይዛለች፡፡ በቅርቡ በተደረገው የመረጃ ጥናት ወንድ 191,934 ሴት 191,647 በድምሩ 383,581 ህዝብ እንደሚኖርባት ጥናቱ ያሳያል፡፡ ዞኑ በ3 የአየር ንብረት የተከፈለና ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዘው ሞቃታማ የአየር ሁኔታ የሚበዛበት 75 በመቶ የሆነው ቆላማ የአየር ንብረቱ ነው፡፡ 24 በመቶ ወይናደጋ 1 በመቶ ደግሞ ደጋማ የአየር ንብረት አለው፡፡ የመሬቱ አቀማመጡም በአብዛኛው ሜዳማና ወጣ ገባ የበዛበት ሲሆን ከ6,00-2,731 ሜትር የሚደርስ ከባህር ወለላ ላይ ከፍታ ያለውና ከግንቦት መጀመሪያ እስከ ጥቅምት መጨረሻ የሚቆይ ሲሆን ከ1000-1450 ሚሊ ሜትር የሚደርስ የዝናብ መጠን ያገኛል፡፡

የዞኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች

የመተከል ዞን የተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ መስህቦች ባለቤት ነው ከነዚህም ውስጥ ባቢን ዋሻ፣ ኤደን ዋሻ፣ አክን ዋሻ፣ ኤግንቦ ዋሻ፣ ዝግህ ዋሻ፣ ጂሮ ዋሻ፣ መነሲቡ ዋሻ፣ ሳንቂ ዋሻ፣ መሶቤ ዋሻ፣ ደቅ ዋሻ፣ አንግቶንግ ፍል ውሀ፣ ዝግህ ፍል ውሀ፣ አንግቶንግ አምቡ ውሀ፣ ጎደሬ ፍል ውሀ፣ ዶቡ ጊዮርጊስ ፍል ውሀ፣ ሚንጆ ትክል ድንጋይ፣ ኦርካንግባ ጫካ፣ ትርሚ ጥብቅ ደን፣ መሀመድ /ሳኒ ሰው ሰራሽ ደን፣ ጎርሽ ፏፏቴ፣ ሳንቂ/ ሊላ ፏፏቴ፣ አባት በለስ ፏፏቴ፣ ሚንጆ፣ መነሲቡ፣ በጀምስ በረሀ፣ ጀን ወንበር፣ አሊ ስፕሪንግ፣ ዲጋ ግድብ፣ ከረንቻች /መንትዮች/ ተራራ፣ ከረኔማጂ ተራራ፣ የባሩዳኩሬ /ጥቁር ምንጭ/፣ ፎቶ ማናጀር ባህላዊ አምልኮ ቦታ፣ ደጅ አዝማች ቤተ መንግስት፣ ቀሀስ በር/ኦሜድላ/ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ባቢን ዋሻ፡- በቡለን ወረዳ በኤማንጂና ጎጃ ቀበሌ ከዋናው መንገድ  በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዋሻው ተፈጥሮአዊ ሲሆን ከተራራው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባቢ (ቡለን) ከተማ እስክትመሰረት የዛሬ 40 እና 50 ዓመት አካባቢ የሺናሻ ብሔረሰበ ተወላጆች እንደመኖሪያም እንደምሽግም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ መግቢያው አንድ ሆኖ ወደ ውስጥ እየተገባ በተሄደ ቁጠር ግን እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ሰፊ መንገድ ኖሮት ከስሩ ሸለቆና ተከትሎም ወንዝ ይገኛል፡፡ አካባቢው ጥቅጥቅ ባለ ደን መሸፈኑ፣ በደኑ ውስጥም የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎች መኖራቸው እና የተለያዩ የዱር እንስሳት መገኘታቸው የአእዋፋትን ዝማሬ፣ የውሀውን ድምፅ፣ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ቀለሞችን በማየት ለአእምሮ እርካታን ያጎናፅፋል፡፡

ኤጃሽ ዋሻ፡- ይህ ዋሻ በቡለን ወረዳ በዶቢ ቀበሌ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ዋሻ ሲሆን ጥናት ባይደረግበትም ለምሽግና ለመኖሪያነት ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከወንበራ አካባቢ የሲንቄ ዋሻዎች በመባል በሚጠሩት መነሲቡ፣ ሳንቂ፣ አካንጉቦ ጫካ እና በሚንጆ ትክል ድንጋይ ታጅቦ የተፈጥሮን ስብጥር ያሳብቃል፡፡

ሚንጆ ትክል ድንጋይ ፡- በወንበራ ወረዳ በቦላሌ ቀበሌ ከመንገዱ በ15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ትከል ድንጋይ በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው አንዲት የአካባቢው ነዋሪ ቦርዴ በማዘጋጀት ላይ እያለች አንድ መንገደኛ ውሀ ይጠይቃታል፤ ፈቃደኛ ባለመሆን ውሀም ቦርዴም እያላት ትታው ልጇን ይዛ ወደ ውጭ በመውጣት ባሏን በመጥራት ላይ እያለች በአካባቢው ውሀ መከልከል በጣም እንደ አስነዋሪ ተግባር በመቆጠሩ ይረግማታል፡፡ በዚህ ግዜ ከነልጇ በቆመችበት ደርቃ እንደቀረችና የእሷ አስክሬን በቀበሌው መጠሪያ ሚንጆ ትክል ድንጋይ እየተባለ እንደሚጠራ ይነገራል፡፡ ወደ አካባቢው ቀርቦ ለማየት ግን አምልኮ የሚፈጸምበት ቦታ ከመሆኑና ተሳቢ እንስሳት እንደ እባብና ዘንዶ በአካባቢው ስለሚገኙ ቀርቦ ለማየት ያስቸግራል፡፡

ደጃዝማች መሀመድ ባንጃው ቤተመንግስት፡- በጉባ ወረዳ  2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ቤተ መንግስት በአራት ዓመት ተሰርቶ እንዳለቀ ይነገራል፡፡ ቤተ መንግስቱ የደጃዝማች መሀመድ ባንጃው መኖሪያ ቤት፣ የችሎት አዳራሽ፣ እንደ እስር ቤት የሚጠቀሙበት ቤት፣ በተጨማሪም ለወጥ እና ለምግብ ማብሰያነት የሚያገለግሉ 5 ቤቶች የነበሩት ሲሆን ባለቤቶቻቸውና ልጆቻቸው ይገለገሉበት እንደነበር ይነገራል፡፡ በቤተ መንግስቱ ውስጥ ያሉ ቢሮዎች በረቀቀ ጥበብ የተሰሩ እና በርካታ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን ቤተመንግስቱ ዙሪያው በተጠበሰ ሸክላ በድንጋይ የተሰራ ሲሆን በግምተ 150 ሜትር በ150 ሜትር ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ የጡብ ግንብ በተለያዩ በሮች ጎን ላይ ክፍት እንደመስኮት መሰል ነገር አላቸው ይህም የሆነበት ከውጪ የሚመጣ ጠላትን ለመከላከል እንደሆነ አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡

ቀሀስበር (ኦሜድላ)፡- በጉባ ወረዳ በኦሜድላ ቀበሌ በ80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲገኝ ሀይለ ስላሴ ከእንግሊዝ ሀገር በሱዳን አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በዚያን ሰዓት በአካባቢው ቤት ባለመኖሩ ዛፉ ውስጡ ተቦርቡሮ በዛ ውስጥ በማደራቸው በራሳቸው እጅ ቀሀስ ብለው ፅፈውበት እስካሁን ድረስ ፅሁፉ በዛፉ ላይ ይገኛል፡፡ ዛፉ በውስጡ 40 ሰው ይይዛል፡፡

የሳሊኒ ትሩፋቶች

የዲጋ ግድብ ፡- በፓዊ ወረዳ በመንደር 17 ውስጥ የሚገኘው ይህ ግድብ  በ1982 ዓ.ም የተገነባ ሲሆን የተገነባውም በ1977 በኢትዮጵያ የነበረውን ክስተት ተከትሎ ፓዊ ላይ በተደረገው የሰፈራ ፕሮግራም ለመስኖ እና ለኤሌክትሪክ ሀይል ተብሎ የተገነባ ነው፡፡ ዲዛይኑ የሲሊንደር ቅርፅ ሲኖረው በውስጡ መንገድ ተዘርግቶለት ከወንዙ ማዶና ወደዚህ ያሉትን ቀበሌዎች ያገናኛል፡፡ መንገዱ የፓውዛ መብራቶች የነበረው ቢሆንም ባሁን ሰዓት ግን ተሰባብረው አልቀዋል፤ ያም ሆኖ ግን መንገዱ እስካሁን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፤ ግድቡን ተከትሎ መስኖ በመጠቀም የተለያዩ የልማት ስራዎች ይሰራበታል፤ በተለይ በፍራፍሬ ምርት አካባቢው እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡

አሊ ስፕሪንግ ፡- ከግድቡ ጋር በአንድ ፕሮጀክት የተሰራ ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በአካባቢው በሚኖሩ አሊ በሚባሉ ነዋሪ ስም ነው፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሀ እስካሁንም ለሁሉም የወረዳው ቀበሌዎች ከወረዳውም አልፎ ለአቅራቢያው ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ውሃው እስከ 2005 ድረስ ቆጣሪ አልነበረውም፡፡

አንግቶንግ ፍል ውሀ፡- በድባጤ ወረዳ አንግቶንግ ቀበሌ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፍል ውሀ ለተለያየ ደዌ መፈወሻነት ሲያገለግል በክረምትም ሆነ በበጋ አይደርቅም፡፡

ቢጀሚስ እጩ ፓርክ ፡- በበፊት ስሙ አቢጀሚስ በመባል የሚታወቀው ይህ ፓርክ በኢትዮጵያ ዱር ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን አስራ አምስተኛ ፓርክ ለመሆን በእጩነት ይገኛል፡፡ ጉባን እና ዳንጉርን የሚያዋስነው ይህ ፓርክ ሰፊው ግዛት በዳንጉር ወረዳ ላይ ያርፋል፡፡ ዋናው ዓላማ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ደኑ አፈሩ እንዳይሸረሸር ለመከላከል ውሀውንና ተፈጥሮ ሀብትን አምቆ እንዲይዝ የተዘጋጀ ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ቀጭኔ፣ ከርከሮ፣ ሚዳቆ፣ ጥንቸል፣ እና የተለያዩ የአእዋፋት እና የእባብ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ ያለውን ከፍተኛውን የደን ቁጥር ይይዛል፡፡ ዞኑ የእነዚህና የሌሎችም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያለበት ቢሆንም የታላቁ የህዳሴ ግድብ መኖሪያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

የዞኑ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለበት ሁኔታ

ዞኑ ለምና ለእርሻ ስራ እና ለእንስሳት እርባታ ምቹና ሰፊ መሬት ያለው፤ በማዕድን የበለጸገና በተለይም በክሰል ድንጋይ፣ በወርቅና አምነ በረድ በስፋት የሚገኝበት፤ ለመስኖ ልማትና ለኃይል ማመንጫ ሊውሉ የሚችሉ ታላላቅ ወንዞች ያሉባት ማለትም አባይ፣ በለስ፣ አይማ፣ ዱራ ነገሪ፣ ሻርና ሌሎችም ከፍተኛና መለስተኛ ወንዞች በብዛት የሚገኝበት ዞን ናት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጣና በለስ ፕሮጀክት አካል የሆነው የታችኛው የበለስ ተፋሰስ ልማት በበለስ ወንዝ ላይ በመከተል እየተካሄደ መሆኑና በአካባቢው ላይም ምቹ ሁኔታ ከመፈጠር አኳያ የስኳር ፕሮጀክት ስራ የተጀመረበት ዞን ነው፡፡ በዞኑ በዋናነት የሚመረቱ ዋና ዋና ሰብሎች የቅባትና የምግብ እህሎች ቡና፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ዳጉሣ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ኑግ፣ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ ኦቾሎኒ፣ ባቄላ፣አተር፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ፣ አተርና ጥጥ በስፋት በዞኑ ይመረታሉ፡፡ በዞኑ ስር ባሉት ወረዳዎች የከበሩ ማዕድናት ወርቅ፣ እምነ በረድ፣ የእጣን ዛፍ፣ ኩል ማዕዳት በስፋት ይገኛሉ፡፡

የዞኑ የኢንቨስት  አማራጮች

በግብርና ልማት ዘርፍ በዝናብና በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ ሰፊና ለም የገጠር መሬት በጋና ክረምት የሚፈሱና የማይደርቁ ከአምስት ትልልቅ ወንዞች በላይ ሲገኙ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ23135 ሄ/ር በላይ መሬት በዞኑ ስር ባሉት ሰባቱ ወረዳዎች ተለይቶ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ እስካሁኑ በመስኖ የለማ መሬት በሄክታር 8126 ሄክታር ሊደርስ ችሏል፡፡ በዞኑ ስር ባሉ ወረዳዎች የቅባት እህሎች ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ የደን ልማት፣ ቅመማ ቅመም የቡና ተክል በተለይም ወምበራ ወረዳ ባሉት ሽንኮራ አገዳ የመሳሰሉት በስፋት በዞኑ የሚመረቱ ናቸው፡፡

የከተማ ቦታ አሰጣጥ ሁኔታ ስንመለከት ከዚህ በፊት ከሊዝ አዋጅ ውጪ ለሚያለሙ ባለሀብቶች ሲሰጥ የቆዩ ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን የፌደራል መንግስት ያወጣውን የሊዝ አዋጅ መነሻ በማድረግ የክልሉ መንግስት በሚያወጣው ደንብ መሰረት ለመተግበር በዞኑ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የዞኑን ማህበረሰብ የንፁህ ውሃ መጠጥ ተጠቃሚ ከማድረግ ረገድ በ2005/2006 ዓ/ም 873 የእጅ ጉድጓድ 266 መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓድ 15 ጥልቅ ጉድጓድና 109 የጉልበት ምንጮች ሲኖሩ 79.89% የገጠር የመጠጥ የውሃ ሽፋን 65.79% የከተማ የመጠጥ የውሃ ሽፋን ሲሆን በአጠቃላይ የዞኑ ንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 74.78% ሊደርስ ችሏል፡፡

ዞኑ ሰባቱን ወረዳዎችን የሚያገኙ የበጋና የክረምት መንገድ ያለው ሲሆን ዞኑን በቀጥታ የሚያገናኝ ጉባና ሸርቆሌ መንገድ በፌደራል መንግስት እገዛ ለውጭ ኮንትራክተሮች ተሰጥቶ የተጠናቀቀና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዞኑን ከክልሉ ርዕሰ ከተማ አሶሳ ጋር በአጭር ርቀት የሚያገናኝ በመሆኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ድርሻ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

ዞኑ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ ረገድ የአምስት ወረዳ ከተሞችና ከ10 በላይ በወረዳዎች ስር ባሉት ንዑሳን ከተሞች የ24 ሰዓት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር ዝርጋታ እየተጠናቀቀ ሲሆን የ2 ከተሞች ማለትም የወምበራ ወረዳና ጉባ ወረዳ በ24 ሰዓት ውስጥ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም አልፎ አልፎ የቴክኒክ ብልሽት እየተከሰተ ለጊዜው የ6 ሰዓት የዲዝል መብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የዞኑ የስልክ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ከመደበኛና የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በዞኑ ስር ያሉ የወረዳ ከተሞችን ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲፋጠን ከማድረግ ረገድ የሰባቱ ወረዳ ከተሞች የዕድገት ፕላን ተሰርቶላቸው ተግባራዊ ሲሆን ተጠናቆ ለተግባራዊ እንቅስቃሴ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የመተከል ዞን ገጽታ ስንመለከት ለእርሻና ለከብት /ለእንስሳት/ እርባታ ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት በመስኖ ኃይል ምንጭ የሆኑ ትልልቅ ወንዞች ጥቅጥቅ ያለ ደንና ብርቅዬ የዱር አራዊት ውብና ድንቅ ለኑሮ ምቹና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲሁም የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላዊ እሴቶች ባለቤት የሆነች ዞን ሲሆን ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ወደ ዞኑለሚመጡ ቀልጣፋ አገልግሎትና ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment