Monday, December 8, 2014


ያሶ ወረዳ

በካማሺ ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን በ13 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ቆዳ ስፋት 2858 ስኩዬር ካሬ ሜትር ሆኖ ከባህር ወለል በላይ ከ1200-2000 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ መልካ ምድራዊ አቀማመጡም 50 በመቶ ሜዳማ፣ 30 በመቶ ተራራማ እና 20 በመቶ ሸለቆአማ ሲሆን የአየር ንብረቱ 91.8% ቆላማ እና 8.2%  ደግሞ ወይና ደጋ ነው፡፡ አማካይ የወረዳው የዝናብ መጠን ከ1200-1800 ሚሊ ሜትር ይጠጋል፡፡  የሙቀት መጠኑ በአማካይ 35ċ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡ በ2005 ቆጠራ የወረዳው ህዝብ ብዛት ወንዶች 16082 ሴቶች 3581 ሲሆን በድምሩ 19663 ይሆናል፡፡ 
 

በወረዳው ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም አያሙሳ ውሀ፣ ባጨጋንት ተራራ፣ ኮሚጳፍል ውሀ፣ የተፈጥሮ ዋሻ፣ ግሽሚላ ድንጋይ፣ ዳዱ ፏፏቴ፣ ፈወለወ ውሀና ቦንቅሽ ፓርክ ይገኙበታል፡፡


አያሙሳ ፡- ይህ መስህብ የሚገኘው ከወረዳው ከያሶ ከተማ  በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ድብ አረንጋማ ቀበሌ ሲገኝ ትርጓሜውም አያሙሳ ማለት በጉምዝ ቋንቋ አያ ማለት ውሀ ሲሆን ሙሳ ደግሞ አምላክ ማለት ነው፡፡  የውሀ አምላክ እንደ ማለት ሲሆን ይህም የተባለው የአካበቢው ማህበረሰብ የአምልኮ ስርአት ይፈጸምበታል፡፡ ውሀውን ለየት የሚያደርገው ዝቅና ከፍ የማለት እንዲሁም የመጥፋትና በሌላ አቅጣጫ ቦታ ቀይሮ የመውጣት ባህሪ አለው፡፡ እንደ እንፋሎት ጭስ ነገር የሚወጣውሲሆን ሞቃትና ለተለያዩ ደዌ እንደ መድሀኒትነትም ይጠቀሙበታል፡፡

ባጨጋንት ተራራ፡- ከወረዳው 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ድብደ ጉራቻ ቀበሌ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በአካባቢው ማህበረሰብ የአምልኮ ስርዓት የሚፈጸምበት ሲሆን ተራራው ላይ የተለያዩ የቤት እንስሳት እና ማዕድኖች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ሌላው ደግሞ አንዲት መካን ሴት በተራራው ስም ከፀለየች በዓመቱ ልጅ ትወልዳለች ተብሎ ይታመናል፤ በተራራው ስም አባቶች ቢረግሙም ቢመርቁም ተሰሚነት አለው፡፡ በየዓመቱም በአካባቢው ማህበረሰብ መስዋእት ይቀርባል በጣም የሚፈራ እና የሚከበር ተራራ ነው፡፡

ኮምጳፍል  ውሀ፡- ከወረዳው በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቦጅ ጠበላ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ የተቀመጠ እንደ ኩሬ ዓይነት ውሀ ነው፡፡ ውሀው ጨዋማ ከመሆኑ የተነሳ በክረምት ሰዓት ሞልቶ በአካባቢው ሲፈስ (ሲዳረስ) ውሀው የነካው አካባቢ ሁሉ ነጭ እና ጨዋማ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የዱር እንስሳት ውሀውን ለመጠጣት ቦታው ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ጎሽ ፣ ነብር አንበሳ ተጠቃሾች ሲሆኑ በዚህ ሰዓት ባይኖርም እነዚህንም የዱር እንስሳት ተከትለው አደን ላይ የተሰማሩ ሰዎች በቦታው በመሄድ በቀላሉ ያድኗቸው ነበር፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችም ውሀውን እንደጨው ይጠቀሙበት፤ ከዚህ በተጨማሪም የተለያየ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ለመድሀኒትነት ይገለገሉበታል፡፡ ውሀውን ለመነከርም በአቅራቢያው የተሰሩትን ጎጆዎች በመጠለል ለአንድና ለሁለት ሳምንት ቆይተው በመነከር ከደዌያቸው ተፈውሰው ይመለሳሉ፡፡

የተፈጥሮ ዋሻ፡- ከወረዳው ከተማ 46 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በሀሎ መከርባና በቴንጆሜጢ ቀበሌዎች መካከል የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ እጅግ በጣም ስፋት እና ርዝመት አለው፡፡ ጨለማ ከመሆኑ የተነሳ በቀን ለመግባት እንኳን መብራት ያስፈልጋል፡፡ እባብ፣ ዘንዶ እና የተለያዩ የዱር እንሰሳት በዚህ ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ እናም ወደ ዋሻው ለመግባት ያስፈራል፡፡ በዋሻው አካባቢ ጥቅጥቅ ያለ ደን በመኖሩ ዝናብ እና የውሃ ጠብታ ከአካባቢው አይታጣም፡፡

ግሽማለ ድንጋይ፡- በያሶ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን 10 የተወሰነ የእግር መንገድም አለው፡፡ በመጠኑ በጣም ትንሽ ሆኖ በዛ ያለ ሰው ለማንሳት ቢሞክር ለማንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ ከዚህ የተነሳ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ አምልኮ ይጠቀምበታል፡፡

ዳዱ ፏፏቴ፡- በያሱ እና በሎጎጎፕ ወረዳ መካከል ሲገኝ ከያሱ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ስያሜውንም ያገኘው የጉሙዝ ብሄረሰብ ሆኖ በፊት እዛ አካባቢ በሚኖር ዳዱ በተባለ ግለሰብ ስም ነው የተሰየመው፡፡ በዙሪያውም ጥቅጥቅ ያለ ማራኪ ደን ይገኛል፡፡ ውሃው ከላይ ወደ ታች ሲወርድ እንደ ጭስ የመትነንና የሚወርድበት ስፍራ የራሱ የሆነ ጉድጓድ ሰርቶ በመጠራቀም ይፈሳል፡፡ ይህ ሁኔታም መንፈስን ይማርካል፡፡

ፍል ውሃ፡- በያሱ እና በሎጎጎፕ ወረዳ መካከል ሲገኝ ከወረዳው 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ውሃው በክረምት ወቅት ብቻ ሲኖር በበጋ ወቅት የመጥፋት (የመድረቅ) ባህሪ አለው፡፡ ከመሬት ውስጥ ሲሆን የሚወጣው የጨዋማነት ባህሪ አለው፡፡ ለከብቶች እንዲሁም በቆሎ፣ ዘንጋዳ እና ስጋ ለማብሰያነትም ይገለገሉበታል፡፡

ቦንቅሽ የዱር እንሰሳት መጠለያ፡- 813 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ከወረዳው በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ በቁርሳዳሊቲ እና በቺካሻ ቀበሌዎች መካከል ይገኛል፡፡

በጉሙዝ ብሔረሰብ የእንግዳ አቀባበል ስነ-ስርዓት

በጉምዝ ብሄረሰብ የእንግዳ አቀባበል ስርዓት ከሌላው አካባቢ ለየት ያለ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገውም አንድ እንግዳ ወይም ነባሩ ብሄረሰብ ሩቅ ቦታ ቢሆን የመጠያየቅ ባህሉ ጠንካራ ነው፡፡ ወደ ጉምዝ አካባቢ ለመጣ ሰው በመጀመሪያ የሚሰጠው ሰላምታ ሳይሆን መቀመጫ ወንበር ነው፡፡ ከዚያ እጅ እና ፊቱን የሚታጠብበት ውሃ ይሰጠዋል፡፡ ይታጠብና እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡ ቡና ተፈልቶ ምግብ ተዘጋጅቶ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጫወታል፡፡ ከተወሰነ ሰዓታት በኋላ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠራርቶ ይመጣና እንደ እንደየእድሜ ደረጃቸው ተራ በተራ እየተነሱ ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ ሰላምታ በሚለዋወጡበት ጊዜ በእድሜ ከፍ ያሉ (ያገር ሽማግሌዎች) የእንግዳውን የእጅ ጣቶች አንድ በአንድ አምስቱንም በመሳብ ሰላምታቸውን ይገልፃሉ፡፡ እንግዳው ዝቅ ብሎ እጁን የሚሰጥ ሲሆን ሽማግሌዎቹ የእንግዳው ራስ ላይ እንትፍ እንትፍ በማለት እና ራሱን ብብታቸው ስር በማስገባት ይመርቁታል፡፡ በጣም የቆየ እና የቅርብ ዘመድ ከሆነ ፍየል ይታረዳል፣ ይዘፈናል፣ ይጨፈራል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በእድሜ ገፋ ያሉ ሁለቱም ፆታዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ከዚያ በመቀጠል በእድሜ ደረጃቸው ሁሉም በትከሻቸው እና በመሳሳም ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ዘመናዊነት እየተንሰራፋ በመምጣቱ እየተረሳ እና እየቀረ ያለ ባህላዊ ስርዓት ነው፡፡

የጉሙዝ ብሔረሰብ ባህላዊ ምግብ

ገንፎ

የገንፎ አዘገጃጀት

የገንፎው እህል የበቆሎ፣ የማሽላ ወይም የቦቤ ዱቄት ሊሆን ይችላል፡፡

የበቆሎ ወይም የማሽላ ዱቄት ከተፈጨ በኋላ ቁለንጋ (እንሴግዛ) በተባለ ባህላዊ እቃ ከውሀ ጋር በመቀላቀል በደረቁ ይቦካል፤ የተቦካው ሊጥ ከአንድ ወይም ሁለት ቀን በኋላ በድንጋይ ወፍጮ እንደገና ይፈጫል፤ የተፈጨውን ሊጥ(ቡኮ) እንሴንጋ በተባለ ድስት ውስጥ ይደረግና እሳት ላይ ይጣዳል፡፡ ጀንጋ በተባለ ማመሰያ እየተማሰለ ከበሰለ በኋላ ዡምፓ በተባለ ከእንጨት በተሰራ መመገቢያ እቃ ላይ ይደረግና ይቀርባል፡፡

ከቦቤ የሚሰራው ገንፎ ደግሞ የቀርከሀ እንቡጥ በካራ ይላጥና ለመፍጨት እንዲያመች ሆኖ ይቆራረጣል፡፡ ከዚያም በድንጋይ ወፈጮ ይዳጣል፣ ውሀ ይጣድና የተዳጠውን ዱቄት ጨምሮ ሲበስል አውጥቶ በገንፎ ማቅረቢያው ማቅረብ ነው፡፡ ከገንፎው ጋር አብሮ ወጥ ይቀርባል ወጡም ከተለያየ ነገር ሊሰራ ይችላል፡፡

የወጥ አሰራር የወጥ አሰራሩ የተለያየ ቢሆንም ከነዚህ አንደኛው

ቤላ (ክማ) (ቤትታ) የሚባል ለገንፎ ማባያ /ወጥ/ የሚሆን በድንጋይ ወፈጮ በመፍጨት እና የተለያዩ ቅመሞችን (ዠማ፣ በሼላ፣ ቴንጉሳ፣ ፍሪንዣ፣ እና ጨው)  በመጨመር ይሰራል፡፡ የተሰራው ወጥ አንትርሳ በተባለ ከሸክላ በተሰራ እቃ ላይ ይደረጋል፡፡ ከገንፎው ጋር አብሮ በማቅረብ ገንፎው በወጡ በማጥቀስ የሚበላ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡

የወረዳው የኢንቨስትመንት አማራጮች

በእርሻው በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር በወረዳው እየለሙ ያሉ ምርቶች ሲሆኑ በ2005 ዓ.ም. በሄክታር ሲሰላ በቆሎ ከ80-120 ኩንታል፣ ሰሊጥ 6-8 ኩንታል፣ ማሽላ ከ50- 60 ኩንታል፣ በቆሎ እስከ 12 ኩንታል፣ ለውዝ 4-6 ኩንታል፣ በርበሬ 6-7 ኩንታል ማግኘት ተችሏል፣ እጣን ከ30 - 40 ኩንታል በዓመት ሲሰበሰብ፣ በዓመት የመንግስት ግብር በማእድን ውጤቶች፤ በአሸዋና ጠጠር በዓመት ዝቅተኛው 20000 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 100,000፣ በእጣን ምርት 25000-30000፣ በሰሊጥ ከኢንቨስተር 1 ሚሊየን ሁለት መቶ ሺ ብር እንደሆነ ያለን መረጃ ይጠቁማል፡፡

አባይ እና ደዴሳ ወንዝን ተከትሎ በመስኖ ለማልማት ለሚፈልጉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በተለይ በኮረሪማ እና እጣን በወረዳው ያልተሰራባቸው አዋጪ መስኮች ናቸው፡፡ የእጣን ምርት እስካሁን በአንድ ኢንቨስተር ብቻ እየለማ ያለበት ሁኔታ ሲሆን ሌሎች ኢንቨስተሮችም ወደ ወረዳው መጥተው ማልማት ቢችሉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡

እንዲሁም በከብት፣ በፍየል እና በንብ እርባታም ለሚሰማሩ በወረዳው በቂ መኖ ከመኖሩ ጋር ያልተሰራበትና ጥሩ ሊሰራበት የሚችል መስክ መሆኑንም ከግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

No comments:

Post a Comment