Monday, May 27, 2013


የሲዳማ ዞን የቱሪስት መዳረሻዎች
BONORA FALL-SIDAMA
 

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ በሲዳማ ዞን የሚገኝ ለዞኑ ብቸኛ ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡ ፓርኩ በሎካ አባያ ወረዳ ከሐዋሳ ከተማ 73 ኪሎ ሜትር  እና ከሎካ አባያ ወረዳ ዋና ከተማ ከሀንጣጤ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ፡፡ ፓርኩ በታላቁ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ /Great east African rifty vally/ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሞቃት አየር ንብረት ማለትም ወደ በረሃማ የተጠጋ የስነ - ምህዳር ባህሪ ይታይበታል፡፡ የታላቁ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ስነ-ምህዳር Great east African rifty vally system አካል የሆነው የአባያ ሐይቅ የዚህ ፓርክ አካል ነው፡፡ የአባያ ሀይቅን ጨምሮ ብላቴ ወንዝ ፣ጊዳዎ ወንዝ እና ኮላ ወንዝ በዚህ ስፍራ መኖራቸው ለፓርኩ የተለያዩ ብዝሃ ህይወት /bio-diversity/ እንዲኖሩት አድርጎታል ፡፡


ስለ ፓርኩ መስህቦች  አጭር ቅኝት

የሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርኩ በታላቁ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ / Great east African rifty vally/ውስጥ መኖሩ የአባያ ሐይቅ ፣ብላቴ ወንዝ ፣ጊዳዎ ወንዝ እና ከአስር በላይ ፍል ውሃዎች መያዙ በውስጡ ብዙ እንስሳትና እጽዋት እንዲኖሩት ምክንያት ሆኗል ፡፡ በሀገራችን ብሎም በዓለም ላይ በመጥፋት ላይ ያለው ተኩላ /African wild dog /በፓርኩ ውስጥ በብዛት መኖሩ  ለሀገራችን ተስፋ ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙት 23 ብርቅዬ አእዋፋት ሁሉም ማለት ይቻላል በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ጋጋኖ /wattled ibas ፣ዎልማ/ turaco፣ ቆቅ /Harwood franclon / የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች አእዋፋት መኖራቸው በተለይ በዓለም ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ላለው አእዋፋትን የማየት ቱሪዝም /bird watching / ቦታውን ምቹ ያደርገዋል ፡፡

ሌላው አስር ፍል ውሃዎች /thermal spring /በቦታው መኖራቸው ነገ ፓርኩ አድጎ ለቱሪስቶች ማረፊያ በሚታሰብበት ጊዜ ለዋና ገንዳና ኢነርጂ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ አጋዘን፣ ድኩላ፣ ተኩላ፣ ጥንቸል፣ ጅብ፣ አንበሳ፣ አነር፣ ከርከሮ፣ የጫካ አሳማ ወ.ዘ.ተ በሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ አጥቢ እንስሳት ናቸው፡፡እነዚህ እንስሳት በቱሪስት መስህብነት ብሎም ለጥናት ያላቸው ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ በአባያ ሐይቅ ላይ የጀልባ አገልግሎት መመቻቸት ቦታውን ለኢንቨስትመንት ያለውን አማራጭ ይጠቁማል፡፡ የውሃ ውስጥ እንስሳትና እጽዋት /equatic life በቦታው በከፍተኛ ቁጥር ይገኛሉ፡፡

     እነዚህ መስህቦችና የተፈጥሮ ጸጋዎች በሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ከሚገኙ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ውስጥ በጥቂቱ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን የፓርኩ ስነ-ምህዳር በሶስት ይከፈላል፡፡ እነዚህም ሪቨሪያን ፎረስት /reverine forest /፣ ቡሽ ላንድ /bush Land/ እና ሳቫና ሳር ከቁጥቋጦ ጋር/grass land with comperteminetia/ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ሶስቱ ስነ-ምህዳሮች ውስጥ የተለያዩ ከላይ የጠቀስናቸው የዱር እንስሳትና አእዋፋት ብሎም የመልክአ ምድር አቀማመጥ ይገኛሉ፡፡ የውሃ አካልም ትልቁ የስነ- ምህዳሩ ግብዓት ነው፡፡

ሀናፋ ባህላዊ የቱሪስት መንደር

ሀናፋ ባህላዊ የቱሪስት መንደር በአረጋሽ ሎጅ አቅራቢያ ከሀዋሳ 52 ኪ/ሜ ርቆ ይገኛል፡፡ ቦታው የሲዳማ ብሄር የወይና ደጋ አኗኗር ዘይቤን የሚያሳይ ሲሆን በሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ከአረጋሽ ሎጅ ጋር በመሆን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ካስተባበረ እና ግንዛቤ ከፈጠረ በኋላ ለቱሪስት የጉብኝት አገልግሎት እየሰጠ ያለ ቦታ ነው፡፡

በሀናፋ ባህላዊ የቱሪስት መንደር ውስጥ በዋናነት የሚጎበኙት ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀትና አመጋገብ፣ ባህላዊ የቡና ስነ ስርዓት፣ የእንሰት አፋፋቅ ሂደት፣ የቡና አዘገጃጀትና አመራረት፣ በመንደር ውስጥ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ባህላዊ ቤት አሰራርና ውስጣዊ ይዘቱን በቱሪስቶች እየተጎበኘ ከፍተኛ ጥቅም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ከማስገኘቱም በላይ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ያደረገ ቦታ ነው፡፡

ጊዳዎ ፍል ውሃ

የጊዳዎ ፍል ውሃ ከይርጋ ዓለም ሆስፒታል 1 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ከሀዋሣ 47 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል :: ቦታው በአሁን ሰዓት በሲዳማ ልማት ማህበር ስር የሚተዳደር ሲሆን ለቱሪስቶችና ለአካባቢው ህብረተሰብ የፍል ውሃ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በእንዲህ አይነት አገልግሎት ረጅም ጊዜያትን የቆየው የይርጋ ዓለም ፍል ውሃ ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን  ለመድሃኒትን ይጠቀሙበታል ፡፡ የተለያየ ደረጃ እንዲኖረው ማለትም በገንዘብና በጾታ ተለይቶ የተደራጀው የጊዳዎ ፍል ውሃ ይርጋዓለም አካባቢን ለሚጎብኙ ቱሪስቶች ሁነኛ መዳረሻ  ሆኗል፡፡   ሌላው ፍል ውሃው  አካባቢ ያለው ተፈጥሮአዊ  አቀማመጥም በጣም ማራኪና በደን የተሸፈነ መሆኑ ከጦጣና ጉሬዛዎች እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ  አይምሮን ያድሳል፡፡ ስያሜውን ያገኘበት የጌዲዎ ወንዝ በዚህ አጥር ግቢ በዝግታ ሲያልፍ በሰመመን ያስጉዛል ፡፡ የአእዋፋት  ጩኸት ጋጋኖ ፣ ነጩ አሞራ፣ ጩሉሌ፣ ጋራ ላይ ያሉ ሽኮኮች ቱሪስቶችን በቀላሉ መማረክ ችለዋል፡፡ ፍል ውሃው በተጨማሪ የዋና ገንዳ የሙሽሮች መዝናኛ ቢገነባበት አሁን እየሰጠ ካለው አገልግሎት የበለጠ በርካታ ቱሪስቶችን የሚስብ አቅም አለው፡፡

No comments:

Post a Comment