Monday, May 27, 2013


አፍሪካና ቱሪዝም

የዛሬ 50 ዓመት ከመነጣጠል አንድነትን የመረጡት አፍሪካውያን ግማሽ ምእተ አመት የሚሆን የጋራ ጉዞ አድርገዋል፡፡ ዘንድሮ ይህንን ልደት መዲናችን አዲስ አበባ እያከበረችው ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ዝግጅት ምክንያት አድርገን አፍሪካና ቱሪዝምን ለመቃኘት ወደድን፡፡
African un
 

አህጉራችን አፍሪካ በቀላሉ የሚጋዙ ሀብቶቿን በቀኝ ግዛት ዘመን ቢበዘበዝባትም፡፡ ተፈጥሮ የለገሰቻት ተወስዶ የማያልቀው ጸጋዋ ግን ዛሬም የትናንት ቀኝ ገዢ ሀገራትን በስጎመዠ መልኩ እንደነበር አለ፡፡ አፍሪካ አሁን የዓለም ጎብኚዎች መዳረሻ እየሆነች ነው፡፡ ሀምሳ አራት ገደማ ሀገራት የተጠለሉባት ይህች አህጉር እንደ ኪሊማንጃሮ ካሉ ተራሮች እስከ ዝቅተኛው የምድር አካል ዳሉል ድረስ የተካተተባት ምድር ናት፡፡ ታላቁ የሰሀራ በርሐ መገኛ አፍሪካ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ የተለየ ቦታ ካላቸው የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ የሆነውና ረጅሙ ወንዝ ናይል የአፍሪካውያን ነው፡፡

የግብጽ ቀዳሚ የስልጣኔ አሻራዎች፣ የደኣማት ስርወ መንግስት ቅሪቶች የማሊ እስላማዊ ቅርሶች የሊቢያ ቀደምት ገናና የታሪክ እውነታዎች፣ የሀዳር የአርኪዎሎጂ ውጤቶች የማእከላዊና ደቡባዊ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች የአፍሪካውያን መገለጫዎች ከሚባሉት እጅግ ብዙ ሀብቶች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአፍሪካ ከፍተኛው ስፍራ በታንዛንያ የሚገኘው ኪሊማንጃሮ ተራራ ነው፡፡ ዝቅተኛው ደግሞ 515 ከባህር ወለል በታች በ515 ሜትር የሚገኘው የጅቡቲውና ኢትዮጵያ ድንበሩ አሰል ሀይቅ፡፡ የአህጉሪቱ ረጅሙ ወንዝ ናይል ነው 6650 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ 9ሺ ስኩዬር ኪሎ ሜትር የሚሰፋው የሰሀራ በረሐ ወደር የለውም፡፡ ማዳጋስካር ታላቁ የአፍሪካ ደሴት ሲሆን በዓለምም 4ኛው ነው፡፡ 68 ሺ 800 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቪክቶሪያ ሐይቅ በአፍሪካ አንደኛው ቢሆንም በዓለም 2ኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ቪክቶሪያ ፏፏቴ ደግሞ 108 ሜትር ርዝመት ላይ የሚወረወር ድንቅ መስህብ ነው፡፡

ናይጄሪያ ብዙ ህዝብ የሚኖርባት የአፍሪካ ሀገር ናት፡፡ ካይሮ ደግሞ ከአፍሪካ ከተሞች ብዙ ህዝብ የሚኖርባት መዲና ናት፡፡ ከ2000 በላይ ቋንቋዎች ይገኙባታል፡፡ በየዓመቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚጎበኛት ግብጽ ግንባር ቀደሟ የአፍሪካ የጎብኚ መዳረሻ ናት፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንደ ግብጽ ሁሉ ከ9 ሚሊዮን ያላነሰ ዓመታዊ ጎብኚ አላት፡፡ ኬንያና ታንዛንያ የምስራቃዊ አፍሪካ የጎብኚ መዳረሻ ቀጠናዎች ናቸው፡፡ ጋምቢያና ሴኔጋል ደግሞ የምራብ አፍሪካን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ይመራሉ፡፡

በአፍሪካ ከ83 በላይ ገናና ወንዞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወንዞች በርካታ የአፍሪካ ፓርኮችን ሰንጥቀው ያልፋሉ፡፡ አፍሪካውያን ወንዞች በራሳቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡

ከ366 በላይ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ስፍራዎች ያሉዋት አፍሪካ የእልፍ አእዋፋት፣ እጽዋትና ዱር እንስሳት መኖሪያ ናት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎች አፍሪካ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ 13 ዓለም አቀፍ ሐይቆች ያሉዋት አፍሪካ በከርሰ ምድር ሀብቷም ትታወቃለች፡፡

አፍሪካን ገናና ያደረጉት የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የነበሩ ህዝቦቿ ናቸው፡፡ የብዙ ህዝቦች አህጉር በመሆኗ በባህል ሀብቷም የገነነች ናት፡፡ ይህ ሁሉ ያላት አፍሪካ አሁን ከዓለም የቱሪዝም ድርሻ ውስጥ የእሷ ድርሻ ከ15 በመቶ በታች ነው፡፡ ለዘመናት ቱሪዝም ይፈልጋቸው የነበሩ ግብዓቶችን ማሟላት ተስኗት በረሐብ በእርስ በእርስ ጦርነት በመሰረት ልማት አለመሟላት ሰፊ ስፍራ ይዛ ኖራለች፡፡ በአህጉሪቱ ውስጥ ይህንን ዓይነት ጠባሳ ታሪክ እስከነአካቴው የሚፋቅበት ዘመን ሩቅ አይሆንም፡፡ የአፍሪካ ደሴቶች ግዙፍ የመዝናኛ ማእከላት እየተገነባባቸው ነው፡፡ አፍሪካ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያላት ድርሻ እየጎላ መጥቷል፡፡ ውሎ አድሮ አፍሪካ ግንባር ቀደም የጎብኚ መዳረሻ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አትችለውም የተባለውን የአንድነት ጉዞ 50 ዓመታት ተጉዛዋለችና፡፡

No comments:

Post a Comment