Friday, October 14, 2016


የመስቀል በዓል አከባበር በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ
ጢያ ትክል ድንጋይ-ሶዶ ወረዳ
 

የመስቀል በዓል የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ የተነፋፈቁ ናፍቆታቸውን የሚወጡበት፣ ያለፈው ጊዜ ምን እንደሚመስል መጪው ጊዜ ምን መሆን እንዳለበት የሚወስኑበት ለክብረ በዓሉ በሰላም ላደረሳቸው ፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ለወደፊቱም መልካም ምኞታቸውን የሚገልፁበት አጋጣሚ ነው፡፡ መስቀል የክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ማህበረሰባዊ ልማዱን ከትውልድ ትውልድ ከሚያስተላልፍባቸው ሀገራዊ ልማዶች መካከል አንዱ በዓል ነው፡፡


እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን ከጉያቸው አድርገው ናፍቆታቸውን የሚወጡበት፤ ወንድሞችና እህቶች ታላላቆቻቸውን በፍቅር የሚያዩበት፣ ሚስት ከባሏ ጎን ሆና የምታሳልፍበት፣ ልጆችም በቤተሰቦቻቸው ዙሪያ ተሰብስበው የሚወያዩት በዚህ በዓል አጋጣሚ ነው፡፡

የመስቀል በዓል ዓመቱን በሙሉ መዘጋጀትን የሚጠይቅ ቢሆንም በዋናነት ከነሐሴ 13 ጀምሮ ጭፈራዎች ይጀመራሉ፡፡ ነሐሴ 13 ደመራ የሚቆረጥበት እለት ሲሆን ይዳሬ የሚባል እንደ ሙልሙል ያለ ዳቦ ለቤተሰብ አባላት ተጋግሮ ይሰጣል፡፡ ይህንንም አንዳንድ አባቶች ከሐይማኖታዊ ይዘት ጋር ያገናኙታል፡፡

በበዓሉ ከሚዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች መካከል ቆጮ እንጀራ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ማባያው ደግሞ የጎመን የስጋ ክትፎ የመሳሰሉት ሲሆኑ ለመጠጥነት ከሚቀርቡት መካከል ደግሞ ጠላ፣ ጠጅና አረቄ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለበዓሉ ድምቀትና ስምረት ከእያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት ማለትም ከአባቶች፣ ከእናቶች፣ ከልጃገረዶቸና ከወጣቶች የሚጠበቁ ተግባራት አሉ፡፡

የአባቶች ሚና፡-

በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ዘንድ አባቶች ከነሐሴ ወር ጀምሮ ለእርድ የሚሆን ሰንጋ ማፈላለግ ይጀምራሉ፡፡ የግቢውን አጥር የማደስ ወይም የማስዋብ ስራም ይሰራሉ፡፡

የእናቶች ሚና፡-

ዓመቱን ሙሉ ለበዓሉ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ ቆይተው ከነሐሴ ወር ጀምሮ ልዩ የሆነ ቆጮ አይብ፣ ቅቤ፣ በርበሬና ቅመማ ቅመም በማዘጋጀት በግድግዳ ላይ ያሉትን መሶቦች /ሌማቶች/ በማውረድ መስቀል መድረሱን ያሳውቃሉ፡፡

የወጣቶች ሚና፡-

ከነሐሴ ወር ጀምሮ እንጨት ፈልጦ በመከመር እንዲሁም ለመብራት አገልግሎት የሚውል የደረቀ ስንደዶ /ገረፋ/ ያዘጋጃሉ፡፡ በተጨማሪም ከነሐሴ 13 ጀምሮ ደመራ ይደምራሉ፡፡ ደመራውም የአዛውንቶች የልጆች በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡

የልጃገረዶች ሚና፡-

ከነሐሴ ወር ጀምሮ ግቢን ማስዋብና የቤት ግድግዳዎችን በአፈር መቀባት የቤት እቃዎችን ማፅዳት፣ ለመመገቢያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን መስፋት ዋናዋናዎቹ ተግባሮች ናቸው፡፡ ይህንን ባላደረጉ ልጃገረዶች በሥነ ቃላቸው ‹‹የገረድ ተላላ ምስም ቲመጣላ ቡናም ቲፈላላ›› እያሉ አሉታዊ አባባላቸውን ይገልፃሉ፡፡ እንዲሁም ደመራ በተደመረበት አካባቢ የሰንበት ቀናት አበቤ አበቤ ዬቦ ዬቦ በማለት እስከ መስቀል መዳረሻ ይጨፍራሉ፡፡

የመስቀል በዓል ዋና ምዕራፍ

ለመስቀል ከላይ እንደተገለፀው የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲከናወኑ ይቆያሉ፡፡ በተለይ እናቶች ልዩ የጎመን ዝግጅት በማዘጋጀት የአካባቢው ሴቶች ተጠራርተው በዓሉን በማስመልከት የሚጠግቡበት ይህ ቀን /ዎልቀነ/ በመባል ይታወቃል፡፡

የልጆች ደመራ /ደንጌሳት/

ይህ በዓል የሚከበረው መስከረም 14 ሲሆን ነሐሴ 13 የተተከለው ደመራ የሚቀጣጠለው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዕለቱ የጎመን ክትፎ በቀጮ መብላት የተለመደ ስለሆነ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለየግል በተዘጋጀለት ባህላዊ መመገቢያ /ጣባ/ ይቀርብለታል፡፡ የቀረበው ምግብም በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ሳይሆን ከአንድ እስከ ሁለት ቀን ቆይቶ የሚመገቡትና ጓደኞቻቸውን የሚጋብዙት ነው፡፡

የእርድ ዕለት /ጨርቆሳ/

ለመስቀል በዓል የተዘጋጀው ከብት የሚታረደው በዚሁ ዕለት መስከረም 15 ነው፡፡ በመሆኑም የአካባቢው ሽማግሌዎች የተዘጋጀውን ጠላና አረቄ ጠጥተው በሁሉም ቤት ተራ በተራ በመመራረቅ የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ ይከናወናል፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ባል ለሚስት ያስገባውን ስጋ መጀመሪያ ያቀምሳል፡፡ እንዲሁም ባል የሞተባት ጎረቤት ካለች ስጋ የምትመገበው በዚሁ ዕለት ሲሆን ጎረቤትና ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ስጋ በቅቤ እንድትመገብ ይደረጋል፡፡ በተለይም ከከተማም ሆነ ከገጠር ያሉ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን ለማስደሰት ስጦታ በማምጣት የሚመረቁ ሲሆን ወላጆችም የተደረገላቸውን ወይም የተሰጣቸውን ስጦታ ለጎረቤት ሽማግሌዎች በማሳወቅ ያስመርቃሉ፡፡

የሽማግሌዎች ደመራ /የጉርዝ ኸሳት/

ዕለቱ መስከረም 16 ሲሆን የአዳብና ሥነ-ሥርዓት የሚጀመርበት ዕለት ነው፡፡ ቀኑን ወጣቶች በደመራው ዙሪያ ሲጨፍሩ ውለው ወደ ቤት በመመለስ ለትንንሽም ሆነ ለትልልቅ ወንዶች ችቦ በማዘጋጀት ከቤት ውስጥ እሳት በመለኮስ ምሰሶውን /ችባን/ ሶስት ግዜ በማስነካት ወደ ደመራው በመሄድ በቅድሚያ ሽማግሌዎች እንዲለኩሱ በማድረግ የማቃጠል ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የደመራ ሥነ-ሥርዓቱም ከተካሄደ በኋላ የስጋ ክትፎ ለቤተሰብ አባላት ለየብቻ በጣባ የሚታደል ሲሆን እስከ ፈለጉ ድረስ አቆይተው መመገብ ይችላሉ፡፡

መስከረም 17 የከሰል ቀን የሚባል ሲሆን ከጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ የእድር /ሳቡኘት/ አባላት ተሰብስበው ስለ አካባቢያቸው ውይይት ያደርጋሉ፡፡ የእድር አመራርም የሹም ሽረት የሚያደርገውም በዚሁ ዕለት ሲሆን አጥፊዎችና ሌቦችን በማውገዝ ቃለ መሃላ ፈፅመው የሰላምና የጤና የጥጋብ እንዲሆን በመመኘት ተመራርቀው ይለያያሉ፡፡ መስከረም 18 የስንደዶ /የፊቃቆማይ/ ዕለት ሲባል ልጃገረዶች በጠዋት ተነስተው ምግብ ሳይቀምሱ በየአካባቢው በመዘዋወር ለስፌት የሚሆን ስንደዶ ይለቅማሉ፡፡ ያመጡትን ስንደዶ እንዲደርቅ በየቤቱ ጣሪያ ላይ ይሰቅሉታል፡፡ 

በአጠቃላይ መስቀል በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ በብዙ ባህላዊ እሴቶች የሚደምቅ፣ በዓመት አንዴ የሚመጣ፣ አካባቢው አረንጓዴ ሲለብስና ምርት ምድር ስታጌጥ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ይህንን በዓል በሶዶ ወረዳ ማሳለፍና በዚህ ወቅት አካባቢውን መጎብኘት በህይወት ዘመን የማይረሳ ትዝታን ጥሎ የሚያልፍ ታሪካዊ አጋጣሚም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment