Wednesday, October 2, 2013

የሀላባ ልዩ ወረዳ የቱሪስት መዳረሻዎች


የሀላባ ልዩ ወረዳ በክልላችን  ካሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ከሚገኙባቸው ልዩ ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ በሀላባ ልዩ ወረዳ የተለያዩ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ተከማችተው ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የአርቶ ፍል ውሃ፣ የስፋሜ ዋሻ፣ የኑርአህመድ መካነ-መቃብር፣ የብላቴ ፏፏቴ/ፋማ/ ፓርክ፣ የአሶሬ ደን እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች የውጭ ምንዛሬ ከማምጣታቸውም በላይ ለተለያዩ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የቻሉ በመሆናቸው አሁንም በእነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ቦታው ክፍት መሆኑን በመጠቆም ነው፡፡

የአርቶ ፍል ውሃ

አርቶ ፍል ውሃ የሚገኘው በአርሾ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲሆን ከልዩ ወረዳዋ ዋና ከተማ ቁሊቶ በ10 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የአርቶ ፍል ውሃ ምንም ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የመታጠቢያ ገንዳ ባይኖረውም በአካበቢው የሚኖሩ ሰዎች በዘልማድ የወንድና የሴት መታጠቢያ ተብሎ ከፋፍለው ይጠቀሙበታል፡፡ የአርቶ ፍል ውሃ ከ15-20 ደቂቃ ውስጥ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን  እንደ ቦሎቄ፣ እሸት በቆሎ፣ድንች፣ ጥቅል ቡና… በፍጥነት ያበስላል፡፡ ይህ ፍል ውሃ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ብንለው አያሳፍረንም፡፡ የአርቶ ፍል ውሀ ለተለያዩ በሽታዎች እንደ ብረድ፣ ቁርጥማት፣ ለጡንቻ መሸማቀቅና ለቆዳ በሽታ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ ከላይ እንደገፅነው በዚህ ፍል ውሃ ዙሪያ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ አሰርቶ የውሃውንና የአካባቢው ስነ-ምህዳር ጠብቆ ለሚያለማ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ኢንቨስተር ምቹ ሁኔታዎች የተቀመጡ መሆናቸውን ጭምር እንጠቁማለን፡፡

የስፋሜ ዋሻ

ይህ ዋሻ ከሀላባ ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ ቁሊቶ ከተማ በ12 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአይማሌና በሀቢቦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ድንበር ላይ ይገኛል፡፡ የስፋሜ ዋሻ ስያሜውን ያገኘው ከተከለለበት የቀበሌ፤ መንደር ስም ነው፡፡ ዋሻው ታሪካዊ ገፅታ ሲኖረው ከአካባቢው የሀገር ሸማግሌዎች ከተገኘ የታሪክ ምስክርነት ውጭ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር አልተደረገበትም፡፡ ይህ ዋሻ በአሰራር ይዘቱ ልዩ የሚያደርገው የጣሪያውና ግድግዳው ግንባታ ከመሬት ወለል ውስጥ ሜትር ከፍታ ላይ መገኘቱን በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ይጠቀሟቸው የነበረች የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያዎች በዋሻ ስር መኖሩ ነው፡፡

የብላቴ ፏፏቴ/ማ/

ይህ ፏፏቴ ከወረዳዋ ዋና ከተማ ቁሊቶ ከተማ ቁሊቶ በ1.5 ኪ.ሜ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ፏፏቴው የሚወስደው መንገድ በበጋም ሆነ በክረምት እጅግ አመቺ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በብሎኬት የተሰሩ ዘመናዊ መናፈሻ ያለው ሲሆን በተጨማሪም በባህላዊ ይዘት የተሰሩ ትናንሽ ሎጆች/መናፈሻዎች/ ያሉ ሲሆን ፏፏቴው ልዩ ውበት እንዲጎናፀፍ አስችሎታል፡፡

የኑረላአህመድ መካነ-መቃብር

ይህ መካነ-መቃብር የሚገኘው በዋንጃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን ሲሆን ወደ ወላይታ በሚወስደው መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ ኑርአህመድ የባሌው ኑር ሁሴን ልጅ ናቸው፡፡ ከአባታቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ጂንካ ሄዱ፡፡ ከዚያም ወደ ቁሊቶ ከተማ በመምጣት ቁሊቶ ከምትባል ሴት ጋር ከተቀመጡ በኋላ ወደ ኑርአህመድ መጡ፡፡ ሰውዬውን በወቅቱ የነበሩ የአካበቢው ህብረተሰብ በሙሉ ልቦናቸው የተቀበሏቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ተከታዮችን ያፈሩ ሲሆን አሁንም በዚያው ዓይነት ስሜት የሚከተሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ህዝቡ እየዘየራቸው /እየጎበኛቸው/ ከልጃቸው ጋር የተቀመጡት ኑርአህመድ መስጂድ ካሰሩ በኋላ ለህልፈት በቁ፡፡ የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም እዚያው ተፈፀመ፡፡ ይህ የቀብር ቦታ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለያየ ጊዚያት ሰዎች እየመጡ የሚጎበኙ ሲሆን በተለይ የአረፋ በዓል ጊዜ ከሁሉም ጊዜ በተሻለ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ይጎበኘዋል፡፡

No comments:

Post a Comment