Monday, March 18, 2013


ማዜ ብሔራዊ ፓርክ

የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጋሞ ጎፋ ዞን ይገኛል፡፡ በዞኑ አምስት ወረዳዎች ማለትም ቁጫ፣ ደራማሎ፣ ዛላ፣ ከምባና ደምባ ጎፋ ወረዳዎች ናቸው፡፡  በመከላከለኛው ኦሞ ሸለቆ ውስጥ የተኛው ማዜ ፓርክ 220 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በ1997 ዓ.ም ደበብሄራዊ ፓርክነት የተከለለው ማዜ ተፈጥሮአዊ ሃብቱ ከመልካአ ምድራዊ አቀማመጡ ጋር ተዳምሮ በአጭር ጊዜ ቀልብ ሳቢ መዳረሻ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡

የማዜ አየር ንብረት ሶስት ዓይነት መልኮች አሉት ቀዝቃዛ የሚሆንበት ወቅት ከሰኔ እስከ ነሐሴ ያለው ሲሆን ከመጋቢት እስከ መስከረም ዝናብ የሚያገኝበት ወቅት ነው፡፡ ከህዳር እስከ የካቲት ያለው ወቅት ግን የሙቀት ሰዓት ነው፡፡ ትልቁ የማዜ ወንዝ ፓርኩን አቋርጦ ከመፍሰስ ባለፈ ለማዜ መጠሪያ ለመሆን በቅቷል፡፡ ማዜን ውበት ያጎናጸፉት እነዚህ ወንዞች ዳርቻቸው በደን የተሸፈነ ነው፡፡ የማዜ ወንዝን ጨምሮ በፓርኩ የሚያልፉ በርካታ ወንዞች መድረሻቸው ኦሞ ወንዝ ነው፡፡

በሳቫና ሳር የተሸፈነው ማዜ በተለይም ዝናብ በሚያገኝበት ወቅት ለምለምና አረንጓዴ መልክ ሲኖረው ለእይታም በእጅጉ የሚስብ ነው፡፡ ማዜን የተለየ ከሚያደርጉት መገለጫዎች አንዱ በውስጡ የሚኖሩ የዱር እንስሳትን በቀላሉ የሚመለከቱበት ፓርክ መሆኑ ነው፡፡ ማዜ ላይ በተደረገው ጥናት እስከአሁን 39 መካከለኛና አጥቢ እንስሳት ዝርያዎች እና 196 የአእዋፍ ዝርያዎች ተመዝግበዋል፡፡ በዋናነት የስዋይንስ ቆርኪ፣ ፌቆ፣ ቦሆር፣ ጎሽ፣ ከርከሮ፣ ድፈርሳ፣ ድኩላ፣ የዱር አሳማ፣ ትልቁ አጋዘን ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ አንበሳ፣ የዱር ድመት ወዘተ ይገኙበታል፡፡

በሰንሰለታማ እና በድንቅ አፈጣጠር የተዘረጉ ተራራዎች የከበቡት ማዜ በርካታ አስደናቂ መስህቦችን አቅፎ የያዘ መዳረሻ ነው፡፡ ቢልቦ ወይም ሀቦ ፍል ውሃ በሚል የሚጠራው የተፈጥሮ ፍል ውሃ በማዜ የላይኛው ተፋሰስ የሚገኝ ሲሆን በፋዋሽነቱ ይታወቃል፡፡

ወንጂያ ትክል ድንጋይ ዋሻ ከ300 ያላነሰ ህዝብ መያዝ የሚችል ዋሻ ሲሆን ማዜ ከያዛቸው መዳረሻዎች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ መጎብኘት የሚፈልጉ ጎብኚዎች በቀላሉ ከአዲስ አበባ 468 ኪ.ሜትር ከሐዋሳ ደግሞ 248 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ማዜ ለመጎብኘት ሁለት ዓይነት መንገዶችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ አንደኛው ከወላይታ በአርባ ምንጭ ደቡብ ኦሞ ዞንን ጎብኝተው በቶሜላ በኩል ወደ ማዜ ማቅናት ሲችሉ፤ በሌላ መንገድ ደግሞ ከወላይታ ሶዶ 83 ኪሎ ሜትር ርቀት ማዜን ጎብኝተው በቶሜላን በማድረግ ደቡብ ኦሞ አርባ ምንጭ የሚጓዙበት ነው፡፡ በጋሞ ጎፋ ዞን የሚገኘውን የማዜ ብሔራዊ ፓርክ ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ካቀኑ ከማዜ ባሻገር የጋሞ ጎፋ አስደናቂ አያሌ መስህቦችን ለመጎብኘት አጋጣሚውን ያገኛሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ አባያና ጫሞ ሐይቆችን፣ የእግዜር አዳራሽና የእግዜር ድልድይን፣ አንጁሌ ደሴትንና እንደ ዶርዜ መንደርና ብርብራ ማርያምን የመጎብኘት እድል ይፈጥርልዎታል፡፡

No comments:

Post a Comment