Friday, January 25, 2013


የዛይ ማህበረሰብ የትንሣኤ ዘመን

ዝዋይ የሚለው ቃል ትርጉም ዛይ ከሚለው የደሴቶቹ ማህበረሰብ መጣ የሚሉ አፈ-ታሪኮች በርካታ ናቸው፡፡ የዝዋይ ደሴቶች እጅግ በርካታ ምሁራንን አፍርተዋል፤ ከዚህ ዓልፎ እንደ ግርሀም ሀንኮክና ጀምስ ብሩስ ባሉ የጉዞ ጸሐፍት የተተረከላቸው እነኚህ ደሴቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ሚስጥራዊ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ታቦተ ጽዩን በስደቷ ወቅት ያረፈችበት ስፍራ በመሆኑ ብዙዎች ለበረከት ይተማሉ፡፡


የዛይ ቋንቋ ሞቷል ተብለን የተማርንው ቋንቋው ሞቶ ሳይሆን በቁም ገዳይ በዝቶ ይመስላል፤ ምክንያቱም አባት እና ልጅ ስለዚህ ቋንቋ እየሞተ ነው የሚል ትምህርት ተምረዋል፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት እየሞተ ነው የተባለለትን ቋንቋ የለም ህያው ነው ለማለት የዛይ ልጆች ያቋቋሙት የዛይ ልማት ማህበር በርካታ ስራዎች እየሰራ ነው፡፡

ማህበሩ ከማህበራዊ ስራዎቹ ባሻገር የደሴቶቹ ታሪካዊ እሴት እንዲወጣ፣ ቅርሶቹ እንዲጠበቁ፣ የዝዋይ ደሴቶች በመንፈሳዊ ቱሪዝም መዳረሻነት እንዲተዋወቁ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ዓመታዊውን የአስተርዮ በዓል ለመታደም ብዙዎች ወደ ዝዋይ እየተጓዙ ነው፡፡  ዘንድሮ የጠዴቻ አብረሃም ቤተ ክርስቲያን ይመረቃል፡፡ ይህን ለመታደም ጥር 19 የዝዋይን ሐይቅ እየሰነጠቁ ወደ ጠዴቻ አብረሃም ለመጓዝ ብዙዎች ባቱ ከትመዋል፡፡

ጥር 21 በደብረ ጽዩን የሚከበረው የአስተርዮ ማርያም በዓል ብጹአን ጳጳሳት ጭምር ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ዝግጅት ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ እሴቶችን በምስልና በጽሑፍ ለማስቀረት የዛይ ልማት ማህበር የራሱን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በአጭር ግዜ ስለ ዛይ ማህበረሰብና ስለ ዝዋይ ደሴቶች ፋይዳ ብዙ ነገር እናውቃለን፤ ደግሞም ሩቅ አይሆንም፤ ግን ደግሞ እገዛን ይሻል የሚመለከተው ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ የዝዋይ ደሴቶች ገና ምንም ያልተጎበኙ ነገር ግን በብዝሃ ሕይወት ሃብታቸው የካበቱ ናቸው፡፡ አእዋፋት የሚያዜሙበት ድንቅ ስፍራ …. የቃል ኪዳኑ ታቦት ያረፈበት የተቀደሰ ምድር፣፣፣፣፣

No comments:

Post a Comment