Friday, September 14, 2012

tuba

መስቀል በአዲግራት

መስቀል በአዲግራት
 
መስቀል በሃገራችን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በተለይም የደመራ በዓል ከፌስቲቫል ቱሪዝም ሀብታችን ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህንን በዓል የሰው ልጆች ሁሉ እሴት ለማድረግም ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ መስቀልን በዩኔስኮ ለመመዝገብ በቅቷል፡፡

መስቀል እንደ የኢትዮጵያውያን እሴትና ባህል ከዳር ዳር የሚከበር ከአደይ ጋር አብሮ የሚፈካ፣ ከዘመን ጋር የሚጠባ በዓል በመሆኑ ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን አድርገዋለል፡፡

በድንቅ እሴት የተሞላውና ብዙ ሳይነገርለት የኖረው የምስራቃዊ ትግራይ ዞን የመስቀል በዓል አንዴ ሌላ የባህል ሃብት መስህባችን ነው፡፡

Tuesday, August 21, 2012


ኢትዮጵያ በብሄራዊ ሀዘን ላይ ትገኛለች፤

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስክሬን ትናንት ምሽት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፤

መንግስት መደበኛ የመንግስት ስራ ሳይዘጋ የሃዘን አዋጁ እንዲቀጥል አውጇል፤

ላለፍት 21 ዓመታት ሃገሪቱን በግንባር ቀደምነት ሲመሩ የነበሩት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአህጉሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን የሚታደሙት፤የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር፤ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የሃገራችን መንግስት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም ለህዝቡ አስታውቋል፡፡

ሰኞ ለማክሰኞ ዋዜማ ከእኩለ ለሊቱ በፊት መሞታቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው 21 ዓመታት የሚመሩት መንግስት ሀገራችን የቱሪዝምና የባህል ፖሊሲዎች እንዲኖሯት በማድረግ፣በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ፣ አዳዲስ ፓርኮች እንዲለሙ፣ ቅርሶች የቅርሱ ባለቤት የሆነው ህዝብ እንዲያስተዳድራቸው በማድረግ እና የቱሪዝም ልማቱን የሚያግዝ የብድር ስምምነት በማድረግ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ላይ በማተኮር፣ በርካታ የባህል ልውውጥ መድረኮችን ሀገራችን እንድትሳተፍ በማስቻል ያበረከቷቸው ተግባራት የሚወደሱ ናቸው፡፡

የሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን እና የቱባ መጽሔት ባልደረቦች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማንን ሀዘን እየገለጽን ለባለቤታቸው፣ለትግል ጓዶቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

Monday, August 20, 2012


ብጹእ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማይ፤ ፓትረያሪክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ሊቀ-ጳጳስ ዘ አክሱም፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት፤ የዓለም ሐይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፤ የሰላም አምባሳደር በተወለዱ በ76 ዓመታቸው አረፍ፤



ለሃገሪቱ ቱሪዝም ልማት እና ለሙዚየሞች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጾ ማበርከት የቻሉ አባት ነበሩ፤



የዛሬ 76 ዓመት በአድዋ ከተማ አቅራቢያ በአባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም.  ከካህን ቤተሰብ፣ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ሮ አራደች ተድላ ተወለዱ፤ የያኔው ገብረ መድኅን የአሁኑ  አቡነ ጳውሎስ፣ከዚያም  በጥንታዊው አባ ገሪማ ገዳምና በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በማቅናትም ከሩሲያው የቅዱስ ቭላድሚር ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ በኦርየንታልና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የነገረ መለኮት ይትበሐል (ትምህርት) በ1954 ዓ.ም ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በየል ዩኒቨርሲቲ በኦሪየንታል፣ በምሥራቅና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከትና ልዩነት ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪን በ1958 ዓ.ም ሲያገኙ፣ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማስተርስ ኦፍ ቴኦሎጂ ዲግሪን በ1964 ዓ.ም. ተቀብለዋል፡፡ በዚያው ዩኒቨርሲቲ በ1980 ዓ.ም. የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪያቸውን ያገኙት ስለእግዚአብሔር ህልውና እና ስለፍልሰታ ማርያም በጻፏቸው የጥናት ድርሳኖች ነው፡፡

Thursday, August 9, 2012


የሲዳማ ዘመን መለወጫ /ፍቼ/ በአል አከባበር

ከይረጋዓለም ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር


ፍቼ በዓል በሲዳማ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

“ፍቼ” በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዘመን መለወጫ በአል ነው፡፡ በአሉ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሂደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አድምታ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ፍቼ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን ከዚህም በሰፋ መልኩ በባህላዊ አደባባይ /ጉዱማሌ/ በጋራ በድምቀት የማክበር ሂደትን ያካትታል፡፡ ለአከባበሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቅድሚያ እንደ አቅሙ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ አንጻር የቤቱ እመቤት ለበአሉ ቅቤ ታጠራቅማለች ወተት በታጠነ ማለፊያ “ቁሹና” /የወተት እቃ/ ታከማቻለች የእንሰት ውጤት የሆነውን ቆጮ ለበአሉ በሚሆን መጠንና ጥራት ከወዲሁ ታሰናዳለች፡፡

Friday, July 20, 2012


ቱሪዝም በዳዉሮ
ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ


የዳዉሮ ዞን  ከኢትዮጵያ ዉብ ገፅታ ማሳያዎች አንዱ ነዉ፡፡ ዞኑ በደቡብ ክልል የሚገኝ ሲሆን የዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ ትባላለች፡፡ ታርጫ ገስጋሽ ነገር ግን በሚሌኒየሙ ከተወለዱ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ከሐዋሳ በ282 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በሻሸመኔ አድርገዉ በወላይታ ሶዶ የሚጓዙ ከሆነ 455 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ በሌላኛዉ መንገድ በጅማ አርገዉ የሚጓዙ ከሆነ ደግሞ በ479 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚያገኟት ከተማ ስትሆን ከተማዋ በየግዜዉ እያስመዘገበች ባለዉ እድገት ሳቢያም የብዙዎችን ትኩረት ስባለች፡፡

      በደቡብ ከጋሞ ጎፋ በምዕራብ ከኮንታ ልዩ ወረዳ በሰሜን ምዕራብ ከኦሮምያ ክልል በሰሜን እስከ ሰሜን ምስራቅ ከከንባታ ጠንባሮ ዞን በምስራቅ ከወላይታ ዞን ይዋሰናል፡፡ ከሰሜን ምዕራብ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በጎጀብና በኦሞ ወንዞች ተፋሰስ የተከበበዉ የዳውሮ ዞን የብዙ እሴቶች ማዕከል እና እንብርት ነዉ፡፡ ከአምስት በላይ በሆኑ ብሄረሰቦች መከበቡ ዳውሮን ልዩ የባህል አምባ ያደርገዋል፡፡

Wednesday, July 4, 2012


ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ገመገመ

ብዙዎቹ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡

ፓርኮችን በመጎብኘት ረገድ የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የባህል ልውውጥና ግንኙነት አፈጻጸሙ 108 በመቶ ሆኗል….

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በመገምገም የአፈጻጸም ልኬቱን በቁጥርና በመቶኛ አስቀምጧል፡፡ በዘጠኝ ወሩ አስራ ሶስት የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ሲሆን አስራ አራት ለማከናወን በመቻሉ ከእቅዱ ያለፈና 108 በመቶ የሆነ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ብቻ 9 የባህል ልውውጥና ግንኙነት ለማከናወን ታስቦ 11 ለማከናወን ሲቻል አንድ ባህላዊ የሙዚቃ ኪነት ቡድን በውጪ ሃገር ትርኢት ለማቅረብ በታሰበው መሰረት በህንድ ሶስት ከተሞች ትርኢቱን በማሳየት ሃገሪቱንና የህዝቦቿን እሴት በሚገባ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡

በዘጠኝ ወራቱ አፈጻጸም የቱሪስቶች ቁጥር 474,249 ደርሷል፤ ይህም ከእቅዱ አንጻር 88 በመቶ ሲሆን በቋሚ ኤግዚቢሽን ጎብኚዎች ረገድ 106,084 የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች በብሄራዊ ሙዚየም የቋሚ ኤግዚቢሽን የማስጎብኘት እድል ተፈጥሯል፡፡ በሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ገረድም በተለይም ፓርኮችን በመጎብኘቱ አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን 30,110 የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች የሃገሪቱን ፓርኮች ጎብኝተዋል፡፡ የሴቶቹ ቁጥር ደግሞ 12,405 ነው፡፡ ይህ ቁጥር 42,246 የውጪ ጎብኚዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ፓርኮችን የመጎብኘት ባህል እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ በአለፍት ዘጠኝ  ወራት ከቱሪስቶች 371,811,216 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ የአንድ ቱሪስት አማካኝ የቆይታ ግዜ 6.5 ሲሆን የቀን ወጪው ደግሞ 120.6 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ያገኘንው መረጃ ያመላክታል፡፡