Saturday, March 16, 2013


ምርጥ 10 የስልጤ ዞን የቱሪስት መዳረሻዎች
የስልጤ ዞን በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ የዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት    ሲሆኑ በዞኑ የሚኖረው ህዝብ ብዛት ደግሞ ይደርሳል፡፡ የዞኑ ርእሰ ከተማ ወራቤ ከአዲስ አበባ በ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ እና በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ ናት፡፡ ስልጤ ዞኑ በበርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች ከክልሉ አርአያ ከሚባሉ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ ከእነዚህ መልካም እና ስኬታማ ተግባራት መካከል ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በየዓመቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት ፕሮሞሽናል ቁሳቁሶችን ያዘጋጃል፣ ያትማል፣ ያሰራጫል፤ የተለያዩ የባህል እሴቶቹ እንዲጠኑ፣ ቋንቋውን የተመለከቱ ምርምሮች እንዲደረጉ በፈጠረው ምቹ እድል በክልሉ የዘርፉ የልቀት ቀጠና ከሚባሉ ዞኖች መካከል ሊጠቀስ ችሏል፡፡
በዚህ ረገድ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የዞኑን ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን በመለየት ደረጃ በማውጣት እና በማስተዋወቅ እያከናወነ ያለው ተግባር እንደሀገርም የተለየ ያደርገዋል፡፡ እኛም በዞኑ ምርጥ 10 ተብለው የተለዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን በወፍ በረር እንቃኛቸዋለን፡፡
ሀረ ሸይጣን ሀይቅ
በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ አጎዴ በተባለው ቀበሌ የሚገኘው ይህ ሀይቅ ከአዲስ አበባ ወራቤ አርባምንጭ በተዘረጋው አስፋልት ላይ ቡታጅራ ከተማን አልፈው 9 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኃላ በስተምስራቅ 1.2 ኪሎ ሜትር ገባ ብለው የሚያገኙት ሐይቅ ነው፡፡ ሀራ ሸይጣን ሀይቅ የሚገኝበት ወረዳ ዋና ከተማ ቅበት ሲሆን ሀይቁ ከቅበት 3.4 ኪሎ ሜትር እንዱሁም ከወራቤ 30.4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ሀይቅ የተለየ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ፣ የሀይቁ ገጽታ እና ስለሀይቁ የሚነገሩ ታሪኮች ዋናውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ የገበቴ ቅርጽ ያለው ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ከላይኛው የመሬት ገጽታ በታች ተንጣሎ የተኛ በየወቅቱ የውሃውን ቀለም የሚቀያይር ጎብኚዎች አፋፉ ላይ ሆነው ድንጋይ በመወርወር ሊያስገቡ የማይችሉበት መሆኑ ጎብኚ የበለጠ እንዲማረክና ትእንግርት እንዲሆንበት አድረጓል፡፡ በሀይቁ 1 ኪሎ ሜትር አቅራቢያ ሌላ አስገራሚ አይናጌ የተባለ ድንቅ ዋሻም ይመለከታሉ፡፡ በዞኑ የተዘጋጀው ሀረ ሸይጣን ሀይቅን የተመለከተ መረጃ ሀይቁን ሲገልጸው በሀይቁ ዙሪያ የሚደረግ ጉብኝትና ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራም በማይለቅ ብዕር የሚጻፍ የህሊና ታሪክ እንደሆነ ብዙዎች መስክረዋል፡፡ ሲል አስፍሯል፡፡

አባያ/ጡፋ/ ሐይቅ
በስልጤ ዞን ስልጢና ላንፈሮ ወረዳዎች መካከል የሚገኘውና እና በአብዛኛው አካሉ በስልጢ ወረዳ ላይ ያረፈው አባያ/ጡፋ/ ሀይቅ ከወራቤ በሰሜናዊ አቅጣጫ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ከስልጢ ዋና ከተማ ቅበት ከደረሱ በኃላ በስተምስራቅ 15 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኃላ የሚያገኙት ሐይቅ ነው፡፡
ለዋና የሚመች ነፋሻማ አየር ያለው ለጀልባ መዝናኛና ለአሳ ማስገር ቱሪዝም የተመቸ ስፍራ ሲሆን ሀይቁ ጣፋጭ የቆሮሶ የአሳ ዝርያም በብዛት ስለሚገኝ በሀይቁ አቅራቢያ ለዚህ ስራ በተደራጁ ወጣቶች ተዘጋጅተው ይቀርብልዎታል፡፡ ስፍራው የስምጥ ሸለቆ መለያ የሆኑ አእዋፋት በብዛት የሚገኙበት ነው፡፡ ስፍራው ለኢኮ ቱሪዝምና ለኢኮ ሎጅ ኢንቨስትመንት አመቺ ነው፡፡ አባያ /ጡፋ/ ሐይቅን እየጎበኙ በጀልባ ቀዘፋና በዋና ይዝናኑ፡፡
ሙጎ ተራራ
ሙጎ ተራራ የሚገኘው በምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ከወራቤ 91 ኪ.ሜ ከወልቂጤ ወደ ሆሳዕና በሚወሰደው የመኪና መንገድ አጠገብ ሲሆን በዞኑና በክልሉ ተጠቃሽ መሆን የቻለ የበርካታ ብርቅዬ አእዋፋትና የዱር እንሰሳት መገኛ ነው፡፡ የሙጎ ተራራ በአካባቢው አጠራር ‹‹ሚዳቻ›› የሚባል ሲሆን ትርጉሙም የስልጤ ባህላዊ ምድጃ እንደማለት ነው፡፡ አሰያየሙ በአካባቢው የሚገኙት ሌሎች አነስተኛ ኮረብቶች መካከል ከፍ ብሎ የሚገኝ በመሆኑ እንደሆነ በአካባቢው የሚገኙ ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡ ከስሩ በርካታ ምንጮች የሚፈልቁበት የሙጎ ተራራ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 3277 ሜትር ሲሆን የተራራው ሰንሰለት ወደታች ዝቅ ብሎ ነው የሚገኘው፡፡ አናቱ ላይ ሆነው የጉራጌ፣ የሀድያና የበርካታ ዞኖችና የስልጤ ዞን መንደሮችን እንዲሁም ደግሞ ማታ ማታ የጅማ ከተማን ያለተጨማሪ መርጃ መሳሪያ ማየት ያስችላል፡፡ በዚህም የተነሳ ይመስላል የጣሊያን ጦር የመመሸጊያና ስትራቴጂክ ቦታ አድርጎ የመረጠው፡፡ ተራራው አናት ላይ ቢላል የሚባል ጥንታዊ መሰጂድና አንድ ዋሻ ይገኛል፡፡ ተራራውና አካባቢው በኢትዮጵያ ከሚገኙ 69 አበይት የአዕዋፍ መገኛ ቦታዎች አንዱ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ተፈጥሮ ታሪክ ማህበር ጥናት ያረጋግጣል፡፡ እርስዎም ተራራው አናት ላይ በመውጣት አይንዎ የቻለውን እየተመለከቱ በተራራው ስንሰለት ላይ ደግሞ የአዕዋፋቱንና ዝማሬ እያዳመጡ ሙጎን ይጎብኙ! ለተራራ ጉዞ መዝናናት (መውጣትና መውረድ) የሚመርጡት የአድቬንቸር ቱሪዝም ስፍራ ነው፡፡
 
የጊስት ጣሂራት ጥንታዊ መስጂድ
ከዞኑ ዋና ከተማ ወራቢ በአሊቾ ውሪሮ ወረዳ በኩል ወደ ወልቂጤ በሚወስደው መንገድ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ ሶጃት ተብሎ በሚጠራው መንደር ከቃዋቆቶ ደግሞ በስተ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያገኙታል፡፡ መስጂዱ በጥንት ጊዜ  ከምስራቅ አቅጣጫ በመምጣት አካባቢው ላይ ስፍረው ለዛሬው የስልጤ ብሔረሰብ ጎሳዎች ምንጭ ከሆኑት ታላላቅ ሴት አያቶች መካከል በአንዷ (ጊስት ጣሂራት) አማካይነት እንደተገነባ  የሚነገር ሲሆን ከአገታ ተራራ ስር ከሚገኝ አንድ ቋጥኝ ተቦርቡሮ የተሰራ ነው፡፡ መስጂዱ ከ500 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚገመት እና ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ ነው፡፡ መስጂዱ ጋ ለመድረስ በሀገር በቀል ቁጥቋጦዎች የተሸፈነውን የአገታ ተራራ እየተንፏቀቁ በታላቅ ጅግንነትና የጎብኚነት ስሜት በመውረድን ይጠይቃል፡፡ አድቬንቸር ቱር ይሏል እንዲህ ነው፡፡
የሀጅ አልዬና የገን ስልጤ መስጂዶች
የሀጅ አልዬ መስጂድ የሚገኘው በምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በታች ዑምናን ቀበሌ ከወራቤ በስተ ምዕራብ እቅጣጫ 54 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ሀጅ አልዬ ከስልጤ ቀደምት አባቶች መካከል በመሪነት ከመጡት አንዱ ሲሆኑ የአብዛኛው የስልጤ ብሄረሰብ የዘር ሀረግ የሚመዘዝባቸው አባት እንደሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ሃጂ አልዩ መጀመሪያ ያረፉትም ሆነ መጨረሻ የሞቱት እዚህ አካባቢ መሆኑን አዋቂ ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡ ከመስጂዱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሀጅ አልዬ ጊዜ የሰላት ጥሬ አድሪጊ /ሙአዚን/ የሚቆምበት ታሪካዊ ድንጋይ በመኖሩና በመደዳ የተደረደሩት ከውዱዕ በኋላ ለመረማመጃነት ያገለገሉ የነበሩ ድንጋዮች መገኘታቸው የቀድሞውን የስልጤ ታሪካዊና ጥበባዊ ቅርሶች ለመመልከትና ብዙ ዓመታትን ወደኃላ ለማስታወስ እድል ይሰጣል፡፡ በልዩ ኪነ ህንጻ የተሰራው መካነ መቃብር ሌላው ቅርስ ሆኖ መስጊዱ አጠገብ ይገኛል፡፡ የገን ስልጤ መስጂድም በአልቾ ውሪሮ ወረዳ ከኩተሬ ከተማ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በ7 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚገኝ ሲሆን መታሰቢያነቱ ለበርካታ የስልጤ ብሔረሰብ ጎሳዎች አባት ለሆኑት ገን ስልጤ የተሰራ በመሆኑ ከሐጅ አልዬ መስጊድ ጋር ተያይዞ በቅርስነቱ ይጠቀሳል፡፡
አልከሶ መስጂድ
አልከሶ መስጂድ የሚገኘው በስልጤ  ዞን ወረዳ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ወራቤ በሰተሰሜን አቅጣጫ 8ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ከወረዳው 2 ከተማ አልክሶ ደግሞ 38 ሜትር ርቀት ላይ ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ ከስልጤ ቀደምት ኃይማኖታዊ መሪዎችንዱ ለሆኑት አልክስዬ መታሰቢያነት የተገነባ ጥንታዊና የብሔረሰቡን ስነ-ግንባር፣ ፍልስፍና የሚያንፀባርቅ ይዘት ያለው መሰጂድ ሲሆን በየአመቱ የረመዳን ፆም ከመግባቱ 15 ቀን ቀደም ብሎ የሚዘጋጀውና በርካታ ባህላዊ ሰነ-ስርዓቶችን የሚያካትተው መውሊድ ይስተናገድበታል፡፡ በ2004 የ105ኛው መውሊድ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ የአልከሶ መስጂድ በአሰራሩም ሆነ ባለው ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ገጽታ ታዋቂነትን ያተረፈ ጥንታዊ መስጂድ ነው፡፡ መስጂዱ የተሰራበት 3ሜትር መጠነ ዙሪያ ያለው ምሰሶ ከረጅም ርቀት በሰው ጉልበት ተጎትቶ መምጣቱና ከምሰሶው የሚነሱ ወጋግራዎችን ውስጡን ገብቶ የሚጎበኝ ሰው ሳይደነቅባቸው ከማይወጣባቸው ቅርሶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡  መስጂዱን ለመጎብኘት ሲመጡ በመስጂዱ አስጎብኚዎች የሚነገሩ በርካታ አስገራሚ አፈ-ታሪኮችና ገጠመኞች የኖራሉ፡፡ የስልጤ ብሔረሰብን የሥነ-ጽሑፍና ሥነ- ጥበብ ሂደትንም በውስጡ ይዟቸው በሚገኙ ባህላዊ የመጻፊያ መሳሪያዎችና የሥነ-ጥበብ ዘዬዎች ማገናዘብ ይችላል፡፡
 
አሳኖ ትክል ድንጋይ
የአሳኖ ተክል ድንጋይ በስልጢ ወረዳ ከዋና ከተማው ቅበት ወደ ወራቤ በሚወስደው መንገድ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ትክል ድንጋዮቹ በቁጥር ከ3 የሚበልጡ ሲሆን በጠፍጣፋ ቅርፅ የተሰራው ዋናው ትክል ድንጋይ መጠነ-ዙሪያ 1 ሜትርና ቁመቱ 2 ሜትር ይገመታል፡፡ የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል የሆኑትን ዓይን፣ አፍ፣ እጅ፣ ጡት፣ ደረት፣ ሆድ፣ የሚነበቡ ፅሑፎችና ስንቅ ወይም የጦር መሳሪያ /መያዣ/ ወዘተ …ምስሎች ተቀርጸው  የሚገኙበት ነው፡፡ በሌሎቹ ላይ ደግሞ መገልገያ መሳሪዎች የሚመስሉ ምስሎች ተቀርጾበታል፡፡ ሌላው ከዚሁ አካባቢ ተወስዶ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በክብር በግልጽ ቦታ ተተክሎ የጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ትክል ድንጋይ የዚሁ ትክል ድንጋይ አካል እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ በጥቅሉ የአሳኖ ትክል ድንጋይ በጥንት ጊዜ በአካባቢው ላይ ይኖር የነበረው ማህበረሰብ ስነ-ጥበብን የሚያንጸባርቅ ትክል ድንጋይ ነው፡፡ ጎብኚዎች ብዙ ሳይቸገሩ ከቅበት ወደ ወራቤ ጉዞ ላይ አሳኖ ቀበሌ እንደደረሱ በመንገዱ ከ100ሜ ባልበለጠ ጉዞ እነኚህን ድንጋዮች ማየት የሚችልበት አጋጣሚ ያለ በመሆኑ የሰው ዘርን የስነ-ጥበብ ውጤቶች ቁልጭ ባለ ሁኔታ ተረድቶ ለመመለስ አጋጣሚው መልካም ነው፡፡
 እመዥር ዋሻ
ዋሻው በምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የሚገኝ ሆኖ የጥንት አባቶችን አሻራና ጥበብ ይዞ የሚገኝ ዋሻ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወራቤ ሆሳአና አርባምንጭ በሚወስደው መንገድ ላይ ከወራቤ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የ33 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኃላ ወደ ምእራብ በመታጠፍ የ4.7 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከወረዳው ዋና ከተማ ቂልጦ ደግሞ በ7 ኪሎ ሜትር እመዣር ከተማ አጠገብ ያገኙታል፡፡ ከጉራቾ ወንዝ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ይሄው ዋሻ በውስጡ የተለያዩ ክፍሎች/ መደቦች/ ያሉት ሲሆን ዋናው መግቢያ በር ጋር የዘበኛ ቤት፣ አለፍ ሲልም የህጻናትና የባለቤቶች መቀመጫ የነበሩ መደቦችን ያገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ ዋሻው ከሁለት መግቢያና መውጫ በሮች በላይ ያሉት ሲሆን አንዱ አሁን ባለው ይዘት ባቻ እንኳን 300 ሜትር የሚሆን ውስጥ ለውስጥ ጉዞ በኃላ የሚያስወጣ ሲሆን ሌላው መውጫ ግን ገና በጥናት ያልተደረሰበት ነው፡፡ ዋሻውን በእግር ለማቋረጥ የሚፈልግ ጎብኚ የእጅ ባትሪ እና የለሊት ወፍ መከላለከያ የፊት ሽፋን መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ዋሻውን በዚህ መልኩ አቋርጠው ሲወጡ አንዳች የጀብድ ስሜት ይሰማዎታል፡፡
የኢማም ሱጋቶ ፎቅ
የስልጤ ብሔረሰብ በታሪኩ ካለፋቸው የአስተዳደር እርከኖች ውስጥ ኢማም ሱጋቶ ዘይኔ ስልጤንና አካባቢውን "ጎጎት" በሚባል አንድነት በማሰባሰብ ያስተዳደሩበት ጊዜ ይገኝበታል፡፡ ይህ ጊዜ ከ90 ዓመት በፊት ሲሆን በጊዜው ለመሪው መኖሪያና የአስተዳደሩ ማእከል እንዲሆን ታስቦ የኢማም ሱጋቶ ፎቅ የሀበሻ ጥድ እና ቅርቀሃ ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ ማቴሪያሎች የተሰራ ነው፡፡ ይህ ፎቅ በብዙ መልኩ ከጅማው አባጅፋር ህንጻ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ቤቱም ሲሰራ ከአባጅፋር ጋር እንደተጋገዙ በስፋት ይነገራል፡፡
ኢማም ሱጋቶ ፎቅን ለመመልከት የሚፈልግ ጎብኝ ከስልጤ ዞን ዋና ከተማ ከወራቤ 83 ኪሎ ሜትር ተጉዞ የምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ዋና ከተማ ሌራ ከደረሰ በኃላ 5 ኪሎ ሜትር ያክል በተሸከርካሪ አልያም በእግር ወደ ዱና ቀበሌ መጓዝ ይችላል፡፡ ይህ ፎቅ ባለ አንድ ደረጃ ሲሆን 3 በሮችና 3 መስኮቶች በአሁኑ ሰዓትም በኢማሙ ቤተ ዘመዶች እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል፡፡
ባልጩ ተራራ
ይህ ተራራ የሚገኘው በስልጤ ዞን በዳሎቻና ላንፋሮ ወረዳዎች መካከል አብዛኛው አካሉን ዳሎቻ ወረዳ ላይ ዘርግቶ የሚገኝ ከአራት ቀበሌዎች በላይ የሚያቋርጥ ተራራ ነው፡፡ ባልጩ በዞኑ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ሲሆን 1675 ሄክታር ገደማ የሚሸፍን ነው፡፡ ሰንሰለታማው ተራራ ታሪካዊ ክስተቶችንም ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ የባልጭ ተራራ ለደን ልማትና ለዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ የተመቸ ቦታ ነው፡፡ ተራራው ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ደን ቁጥቋጦ ተሸፍኗል፡፡ በተራራው ላይ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎችና ቁጥቋጦዎች የሚገኙ ሲሆን በእጽዋቱ የተጠለሉ የዱር እንስሳትና ድንበር ዘለል ወቅታዊ ቋሚ የአእዋፍ ዝርያዎችም በብዛት ይገኛሉ፡፡

No comments:

Post a Comment