Tuesday, December 11, 2012


ያንጉ ዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ

የአዘሎ ስር ውበት

አዘሎ ውብና ግዙፍ ተራራ ነው፤ እንደ ሌላው ተራራ አዘሎን ከባህር ጠለል በላይ ይሔን ያክል ብሎ በሜትር በመለካት ርዝመቱን መተረክ አይቻል ይሆናል… ምክንያቱም የአዘሎ ውበቱ ከስሩ ሆኖ መታየቱ ነውና፤ ከመልካ ወረር ሜዳማ ምድር አልያም ከገዳማይቱ የተንጣለለ መስክ ሲታይ አዘሎ ርቆ የቆመ ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ አካባቢው ዝናብ ሲያገኝ አዘሎ አረንጓዴ ካባ ይለብሳል፡፡ ዝናብ ከራቀው ግን ከል ይለብሳል፡፡ አዘሎ ክረምትና በጋ ልቡስን የሚቀይር ተራራ፤

በአፋር ብሄራዊ ክልል ከአዲስ አበባ በ376 ኪሎ ሜትር ርቀትላይ ከምትገኘው ከገዋኔ ከተማ ራስጌ ተኮፍሶ እስከ አዘቦት ተራራ ዙሪያውን የሚቃኘው አዘሎ አናቱ እድሜ ጠገብ እጽዋት የሞሉበት ዙሪያውን በተቦረቦሩ ሸለቆዎች የተሞላ ነው፡፡ ከገዋኔ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለአዲስ አበባ በሚቀርበው ስፍራ የምትገኘው መተካ በፍል ውሃ ሃብት የታደለች በፊላ የተሞላ ረግረግ ያለባት ስፍራ ናት፡፡ ብዙ ጊዜ እዚህ ጎራ የሚሉ አናብስት መነሻቸው የአዘሎ ሸለቆአማ ምሽግ ነው፡፡

ከአዘሎ አናት ቁልቁል ፍንትው ብሎ የሚታየው የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ ብዙ ያልተነገረለት ድንቅ መስህብ ነው፡፡ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በሰሜናዊ የስምጥ ሸለቆ ክፍል የሚገኘው የያንጉዲራሳ ብሄራዊ ፓርክ በገዋኔና ሚሌ ከተሞች መካከል ይገኛል፡፡ ያንጉዲራሳ ብዙ ያልተወራለት ብሄራዊ ፓርክ በ1977 ዓ.ም ቢከለልም ለዘመናት ተሸሽጎ የኖረ ስፍራ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

4731 ስ.ኪ.ሜትር ስፋት ያለው ያንጉዲራሳ አማካኝ ማእከሉ ከአዲስ አበባ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በአሸዋማ ምድር ያረፈው ይህ ፓርክ ከፊል በርሐማ የአየር ንብረት አለው፡፡ ከ230 በላይ የአእዋፍ ዝርያ የሚገኙበት ያንጉዲራሳ እንደ አቦሸማኔ፣ አንበሳ እና ዜብራ ያሉ የዱር እንስሳት ያለ አሰሳ የሚታዩበት ስፍራ ነው፡፡ በድምሩ 36 የሚሆኑ አጥቢ እንስሳት የሚኖሩበት መዳረሻ ነው፡፡ ያንጉዲ ተራራ ለፓርኩ ውበት ሲሰጠው የአዋሽ ተፋሰስ ዳርቻዎች በእድሜ ጠገብ ዛፎች የተሞላ ነው፤ ያልተነገረለት ያንጉዲራሳ!!    

No comments:

Post a Comment