አንጎለላን በወፍ በረር
ሰሜን ሸዋ ብዙ ያልተነገረለት ምድር
ነው፡፡ በሁሉም ወረዳዎች ከሶስት መቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠሩ ቅርሶች በርካታ ናቸው፡፡ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች
የሚበዙበት ሰሜን ሸዋ ከስምጥ ሸለቆ ምድር እስከ ከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎችን ያካተተ መሆኑ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ ቀጠና ያደርገዋል፡፡
እንደ መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ የቱሪዝም ስፍራ ያሉ ቦታዎች ቱሪዝሙ ላይ ከተሰራ ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማከናወን እንደሚቻል
ማሳያ ነው፡፡
ከእነዚህ ድንቅ የዞኑ መስህብ ስፍራዎች
አንዱ አንጎለላ ነው፡፡ የሸዋው ንጉስ ሳህለ ስላሴ በ1885 ገደማ እንደቆረቆሯት የሚነገርላት አንጎለላ ከአንኮበር በመቀጠል ሁለተኛዋ
የሸዋ ነገስታት ከተማ ናት፡፡ አንጎለላ በወቅቱ ስትራቴጂያዊ ማእከልና የስልጣኔ ቀጠና እንደነበረች የሚያሳዩት ዛሬ ህያው ሆነው
የሚመሰክሩት ቅርሶች ናቸው፡፡ አጼ ሚኒሊክ የተወለዱባት አንጎለላ በአያሌ የታሪክ ጸሐፍት ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡
አንጎለላ የሚነገርላትን ያክል የስልጣኔ
መዲና እንደነበረች የሚያሳዩ የህንጻ ፍርስራሽ ቅሪተ አካላት ዛሬም ታሪኳን በገሃድ ይመሰክራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመስራቿ የንጉስ
ሣህለ ስላሴ ቤተ መንግስት አንዱ ሲሆን ቤተ መንግስቱ ዛሬ ላይ በቀረው ቅሪተ አካል በተለይም በቤተ መንግስቱ የምድር ቤት አሰራር
ላይ የሚታየው ጥበብ አስደናቂ ነው፡፡
በአንጎለላ የሚገኘውን ቤተ መንግስት
ግንባታ በመምራቱ ሂደት እንደ ግሪካዊው ድሜጥሮስ ዓይነት የውጪ ዜጎች የነበሩበት ሲሆን ይህ ቤተ መንግስት ውብና በድንቅ የአገነባብ ጥበብ የተሰራ ነው፡፡ ከቤተ መንግስቱ ግንባታ ጎን
አንጎለላን ተወዳጅ አድርጓት የነበረው የጥበበኞች ቀጠና መሆኗ ነበር፡፡ ከተማዋ በጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስደናቂ የእደ ጥበባት
ማምረቻ ማእከል ነበረች፡፡
በሌላ በኩል ከሸዋ ነገስታት የዲፕሎማሲያዊ
ግንኙነት ጋር ስሟ የሚነሳው አንጎለላ ንጉስ ሣህለ ስላሴ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ መንግስታት ጋር የንግድና የወዳጅነት ውል የተፈራረሙባት
ከተማ ናት፡፡ ይህም አንጎለላ በፓሪስ እና በሎንደን ከተሞች ቤተ መንግስታት ስሟ እንዲታወቅ የሸዋ አሳሾች ደጋግመው እንዲያነሷት
በር ከፍቷል፡፡
ከአንጎለላ ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ
አጼ ሚኒሊክ የተወለዱባት እንቁላል ኮሶ ተብላ የምትጠራው ስፍራ ናት፡፡ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙባት አንጎለላ ኪዳነ ምህረት
በንጉስ ሣህለ ስላሴ የታነጸች ሲሆን አጼ ሚኒሊክም ክርስትና የተነሱባት ደብር ናት፡፡ ይህችው ደብር በአድዋው ጦርነት የጦር ሚኒስትሩን
ስፍራ ይዘው ውጊያውን ሲመሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ የተቀበሩባት ናት፡፡ ዛሬም የጀግናው ኢትዮጵያዊ የፊትአውራሪ
ገበየሁ አጽም በመስታወት ውስጥ ሆኖ ለጎብኚ የሚታይባት ስፍራ ናት፡፡ አንጎለላ በርካታ ታሪካዊና መንፈሳዊ እሴቶችን ከመልካአ ምድራዊ
አቀማመጥ ጋር የያዘች ለጎብኚ ምቹ የሆነ ስፍራ የምትገኝ መዳረሻ
ናት፡፡
No comments:
Post a Comment