Monday, December 24, 2012


አንድ ምሳ በማንኩሽ

Mankush
 ማንኩሽ በጣም ጥንታዊ ቀጠና ናት፤ እንደ አክሱም ሮሐ ጎንደርና ሸዋ አንድ ወቅት የሃገሪቱ የፖለቲካ ቀጠና ሆና አገልግላለች፡፡ ይህ ታሪኳ ከታላቁ የዳኣማት ስርወ መንግስት የሚጀምር ነው፡፡ የ2005 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀንን ያስተናገደው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የበዓሉን ተጓዦች ካስተናገደበት ስፍራ አንዱ ማንኩሽ ነበረች፡፡ ማንኩሽ ከመድረሳችን በፊት አሻግሮ ይመለከተን የነበረው ጉባ ተራራ ነበር፡፡ ማንኩሽ ስንደርስም ከተማዋን ቁልቁል እየተመለከተ ጠበቀን… የማንኩሽ ህዝብ በሆታ ሲቀበለን ጉባ ግን እንደተኮፈሰብን ተያየን፡፡ ከከተማዋ 35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጉባ ተራራ ለጉባ ወረዳ መጠሪያም ሆኗል፡፡

በሰሜን ከሰሜን ጎንደር ዞኗ ቋራ ወረዳ በደቡብ ከወንበራ ወረዳ በምስራቅ ከዳንጉር ወረዳ በምዕራብ ከሱዳን የምትዋሰነው የጉባ ወረዳ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ትገኛለች፡፡ እኛ የዛሬው ምሳችን ጉባ መዲና ማንኩሽ ላይ ነው፡፡ በክልሉ ከሚገኙ 20 ወረዳዎች አንዷ የሆነችው ጉባ በ1902 ዓ.ም በደጅ አዝማች ባንጃው አብሻኮ ነበር የተቆረቆረችው፡፡ የወረዳው ስያሜ ከጉምዝኛ የተወሰደ ሲሆን ጉባ ማለት ብርሃን ማለት ነው፡፡

በማእድን ሃብቱ የበለጸገው ቤኒሻንጉል ጉምዝ እንደ ጉባ ያሉ ድንቅ ተራራዎቹን ብረሃን ብሎ ቢሰይም ብዙ አይደንቅም፡፡ ቀጠናው በጥንታዊያኑ የግሪክ ጸሐፍት የተመሰከረለት የኩሽ ህዝብ የወርቅና የማእድን ሃብት ከታሪክ ባለፈ እውነት እንደ ነበረ ማሳያ ነው፡፡ ዛሬም በክልሉ በባህላዊ መልኩ ወርቅ ማውጣት የተለመደ ነው፡፡ ጉባ ስሟ ሲወጣም መነሾው ከተራራው አናት ያብረቀርቅ የነበረው ማእድን ብረሃን ነበር፡፡

ከጉባ መዲና ማንኩሽ የጉምዝ ባህላዊ እሴት እንግዳን ከናፈቀ መንፈስ ጋር ተዳምሮ ልባችንን ሃሴት እንዲሞላው አደረገው፤ ከጉባ ተራራ ስር የከተመችው ማንኩሽ በሆታ ተናጠች!! የዙምባራ ጨዋታን….. የጉባ ተራራ እስኪመልሰው ድረስ ጥዑም ድምፁን አስተጋባ! ማንኩሽ ትናንት የነበራትን ገናና ታሪክ ዛሬ ላይ በአይኗ እንዳየችው ሁሉ እንግድነታችንን አከበረችው፡፡ ከዙምባራ የሚወጣው ድምፅና የተጨዋቾቹ ባህላዊ ውዝዋዜ ዝምታችንን ሰብሮት አብረን መወዛወዝ ጀመርን፤

ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበረው ገናና የኢትዮጵያውያን ታሪክ ኑበያን ጨምሮ ይገዛ የነበረው ስርወ መንግስት ታሪክ አንድ ወቅት ማንኩሽን ለመዲናነት መርጧት እንደነበር በጽሁፍ ጭምር የቀሩ መረጃዎች ያትታሉ፡፡ ማንኩሽ ለዚህ መሰሉ ክብር እንድትበቃ ያደረጋት ሚስጥር በዙሪያዋ ያለው እምቅ ሃብት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

ከብረሃናማው ተራራ ስር የምትገኘው ይህች ከተማ ማንኩሽ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በአንድ ወቅት በስፍራው የገባውን አሰከፊ ረሃብ ተከትሎ ረሃቡ የአስጨነቃቸው ኮሽታ ሳያሰሙ ጭስ ባዩበት ቤት ሁሉ ዘው ብለው ይገባሉ፤ ይህ ያልተለመደ ክስተት ትንግርት የሆነባት አንዲት ሴት በጉምዝኛ ማንኩይፅ አለች የማንኩሽ ቃል የተወለደውም ይህንን ተከትሎ ነበር፡፡ የሚል አፈ ታሪክ ቢኖርም ስያሜው መቼ እንደወጣ መረጃ የለም፡፡

ዛሬ መላ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ልብና መንፈሳቸውን የቸሩለት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲነሳ ጉባ የምትነጠል አትሆንም፡፡ ይህ ታላቅ ግድብ በዚች ወረዳ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ ጉባና አካባቢውን ከሶስት አስርት አመታት በላይ ለመግዛት የቻሉት ደጃዝማች መሐመድ ባንጃው አብሽኮ እስልምናዊ እውቀቶችን የተማሩ ቆራጥ ታታሪና ሐገር ወዳድ መሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ እውቀታቸው ምንም ዘመናዊ ትምህርት ላልተማሩት መሪ በሳል እና ጥበበኛ እንዲሰኙ አድርጓቾዋል፡፡

ቦርዴና ገንፎ የሚወዱት ደጃዝማች መሐመድ ባንጃው አረንጓዴዋንና ድንግል ምድር የተላበሰችውን ማንኩሽን ለመናገሻነት የመረጧት ለስሟ መነሻ የሆነውን ብርሃናማ አለትና ወርቅን ጨምሮ በማዕድን ሐብቶች ለበለፀገው አካባቢ ማዕከል በመሆኗ ጭምር ነበር፡፡

እናም እኒህ ብልህ መሪ ቤተ-መንግስታቸውን ማንኩሽ ላይ---ከተሙት---28ሺ ገደማ ህዝብ ለሚኖርባት ጉባ ርዕሰ ከተማ የሆነችው ማንኩሽ ንግድና ግብርናን መሰረት ያደረገ ኑሮ የሚኖሩ በቀላሉ ተግባቢ ተጫዋችና እንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎች ይገኙባታል፡፡ እነኚህ የማንኩሽ ነዋሪዎች ማንኩሽን ረግጦ ይህንን የደጃዝማች መሐመድ ባንጃውን ታሪካዊ ቤተ-መንግስት አለማየት…. ያስከፋናል አሉና እየመሩ ወሰዱን፤

ከከተማዋ ጀርባ ከውብና አረንጓዴ ምሽግ ውስጥ የማንኩሽን ትናንትና ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ድንቅ ቅርስ ተሸሽጓል ማራኪውና ዛሬም የትናንትና ውብቱን ማስመስከር የቻለው ቤተ-መንግስት የተፀነሰው ደጅዝማች መሐመድ ባንጃው ወደ ጎንደር ተጉዘው የአፄ ፋሲል ቅጥር ግቢ ኪነ- ህንፃዎችን ሲመለከቱ ነበር፡፡ እነኚህ የጎንደር አብያ መንግስታት ግብረ ህንጻዎች በደጃዝማቹ ልብ ተጨማሪ ሃገራዊ እሴት እንዲያኖሩ ስሜታቸውን አነሳሳው፤

ለህንፃው የሚሆነውን ሸክላ አፈር የማንኩሽና የአካባቢው ህብረተሰብ ያቡሉ ከምትባለዋ ቀበሌ እየጫነ አምጥቶ የሰራው ነው፡፡ የኪነ-ህንፃው ምህንድስና ሱዳናዊ በሆነው የደጃዝማቹ ወዳጅ በሰኢድ አል አሚን የተመራ ነበር፡፡ ሰኢድ አል አሚን ምህንድስናውን ይምራው እንጂ ስራው ግን ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራ ድንቅ ፈጠራ ነው፡፡

በቦታ አቀማመጡ…..በአሰፋፈሩ የተዋጣለት ይህ ቤተ-መንግስት ሰፊ የችሎት አዳራሽ እና የእንግዶች ማረፊያ አለው፡፡ ለዱር እንሰሳት ፍቅር የነበራችው ደጃዝማች መሐመድ ባንጃው በዚሁ ቅጥር  ለአንበሳ የሚሆን ክፍልም አዘጋጅተው አንበሳ አስቀመጠውበት እንደነበር ይናገራል፡፡

ሚስጥራዊ የመሳሪያ ማስቀመጫ የአገልጋዮች ቤትና የመኝታ ክፍሎችን ያካተተው ዋናው ህንፃ በቤተ-መንግስቱ አንድ ቅጥር ተከቧል፡፡ በዚሁ ቅጥር የስጋ ማስቀመጫ ቤትና እስር ቤት ይገኛል፡፡ በሌላኛው ቅጥር የአውራጃ አስተዳዳሪዎች ሸሆች ጭቃ ሹሞችና የሚስቶቻቸው ደንገጡሮች የሚያርፉባቸው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

ጠላትን ለመከላከል ምቹ የሆነው የቤተ-መንግስቱ ቅጥር እንደህንፃው ሁሉ በሽክላ የተገነባ ነው፡፡ ሌላው የግቢው ውበት በእፅዋት ማሸብረቁ ሲሆን ደጃዝማች መሐመድ ባንጃው ከተለያዩ አካባቢዎች ያስመጧቸው የፍራፍሬ ችግኞች ዛሬ ፍሬያቸውን ይቸራሉ፡፡ ይህ ቤተ መንግስት የፈረሰው በኢህአፓ ጦርነት ሲሆን በርካታ ቅርሶች በወቅቱ ተዘርፈዋል፡፡ የተረፍት በቤተሰቦቻቸው እጅ በመቆየት በተለያየ አጋጣሚ ጎብኚ እንዲያቸው እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ከስድስት መቶ ዓመት እድሜ በላይ የኖረው ነጋሪት አንዱ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment