werta city |
ለምለሙ የፎገራ ምድር የምርታማነት ቀጠና ነው፡፡ ትርፍ አምራች በሆነው ምድር የተከበበችው ወረታ ከተማ በአማራ
ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ከባህር ዳር ጎንደር በሚወስደው ጎዳና ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
ወረታ ከአዲስ አበባ ኪሎ ሜትር ከክልሉ ርእሰ ከተማ ከባህር ዳር በ55 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር ከተማ 120 ኪሎ
ሜትር፣ ከደብረ ታቦር ከተማ ደግሞ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ 14,097 ወንድ እና 14,379 ሴት በድምሩ
28,475 ህዝብ የሚኖርባት ወረታ በ1942 ዓ.ም ገደማ ነበር የተቆረቆረችው፡፡ ይሁን እንጂ ፈጣን ልማቷን ተከትሎ በሚሊኒየሙ
ማለትም በ2000 ዓ.ም በከተማ አስተዳደርነት ተደራጀች፡፡
ትርፍ አምራቹ የፎገራ ምድር የከበባት ወረታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ መልኩ እያደጉና ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ
ከመጡ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ መስመር ላይ የምትገኝ መሆኗ፤ ዓመቱን ሙሉ ለሚያመርት አካባቢ
ማእከል መሆኗና መንግስት ለከተሞች ልማት የሰጠው ትኩረት ወረታን በተለየ መልኩ የፈጣን እድገቱን ባቡር የተቀላቀለች ከተማ እንድትሆን
አስችሏታል፡፡
ከጣና ሐይቅ ምስራቃዊ አቅጣጫ ከአዲስ ዘመን ከተማ በስተ ደቡብ ከባህር ወለል በላይ በ1828 ሜትር ከፍታ ላይ
ያረፈችው ወረታ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የበቀለች መንደር እንደነበረች ታሪኳ ያስረዳል፡፡ የዛሬዋ ወረታ ለቀጠናዋ የኩራት ተምሳሌት
ለመሆን የበቃች ከተማ ሆናለች፡፡
በዋናው የሀገራችን ታሪካዊ የቱሪዝም መስመር ላይ የምትገኘው ወረታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተገንብተውባታል፡፡
የወረታ ሆቴሎች ለቱሪስት አገልግሎት በመስጠት ረገድ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ቤተሰባዊ መስተንግዶ የሚሰጡ ሆቴሎች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ
የወረታ ሆቴሎች በንጽህና ረገድ የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ ካፍቴሪያዎች፣ ባሮች፣ ባህላዊ ምግብ ቤቶችና ሌሎች የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ
ተቋማቶቿ በቀጠናው ምቹ የማረፊያ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በጣና ሐይቅ አቅራቢያ ከታሪካዊዎቹ ጎንደርና ደብረ ታቦር ከተሞች አማካይ ስፍራ ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በአጼ
ዘርዓያቆብ ዘመን የተመሰረተው የወረታ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያና በ1942 ዓ.ም የተቋቋመው የወረታ ኑር አምባ መስጂድ የከተማዋ
የጎብኚ መዳረሻ የሆኑ ቅርሶች ናቸው፡፡
የወረታን የቱሪዝም አቅም ከሚያሳዩ ገጽታዎች መካከል በዙሪያዋ ያሉ የጎብኚ መዳረሻዎች ለከተማዋ ቱሪዝም ልማት
ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በተለይም በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና በየዓመቱ 55,000 ጎብኚዎች የሚጎበኙት የክርስቶስ
ሳምራ ገዳም፣ የጉራምባ የተፈጥሮ ፍል ውሐ፣ የአሞራ ገደል የተፈጥሮ አምቦ ውሃ፣ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአጼ ሱሲንዮስ
ካብና 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና ከፍተኛ ትኩረትን እየሳበ የመጣው የአውራምባ ማህበረሰብ ወረታን መዳረሻ ካደረጉ የጎብኚ
መዳረሻዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
No comments:
Post a Comment