Saturday, April 25, 2015



ባሌ ዞን
የባሌ ዞን በኦሮምያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን በቆዳ ስፋቱም ሁለተኛው  ነው፤ በስተምስራቅ የሶማሊያ ክልል፣ በሰሜናዊ ምስራቅ ምስራቅ ሐረርጌ፣ በሰሜን ምዕራብ ሐረርጌና አርሲ ዞን፣ በምዕራብ ምዕራብ አርሲ እና በደቡብ ጉጂ ዞን ያዋስኑታል፡፡ ዞኑ 14.93 በመቶ በደጋ፣ 21.54 በመቶ በወይናደጋ እና 63.53 በመቶ በቆላ የአየር ንብረት የተከፋፈለ ነው፡፡ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡም 55.89 በመቶ ሜዳማ፣ 30.7 በመቶ ወጣ ገባማ፣ 12.14 በመቶ ተራራማ እና ቀሪው 0.4 በመቶ ሸለቆማ ነው፡፡ በሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች አንጋፋውን ስፍራ ከሚይዙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የባሌ ዞን እጅግ በርካታ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የታደለ ምድር ነው፡፡ ጥቂቶችን በዚህ ዕትም እንዳስሳለን፡፡



ተፈጥሮአዊ መስህቦች
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተመሰረተው በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ የሚገኘውና ከ40 ዓመት በፊት የተቋቋመው የዲንሾ ሎጂ በወቅቱ አንድ የውጭ ሀገር ባለ ሀብት በጎች ለማርባት ተፈቅዶለት በጎች እያረባ እንደ ቢሮና ማደሪያ ይገለገልበት ነበር፡፡ በአጋጣሚ በግ አርቢው የደጋ አጋዘን፣ የሚኒሊክ ድኩላንና ሌሎችም ብርቅዬ እንስሳቶችን በማየቱ ይሄ ነገር ፓርክ ሊሆን ይችላል በሚል ለመንግስት ሪፖርት በማድረግና መንግስትም ያለውን ነገር በማጣራት በ1962 .ም. እንደ ፓርክ ሊከለል ችሏል፡፡ በ1960ዎቹ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን ከተቋቋሙት ሶስት ፓርኮች አንዱ ለመሆን በቃ፡፡
ፓርኩ ከአዲስ በባ 4ዐዐ ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲገኝ ስፋቱ  2165 ስኩየር ኪሜትር ነው፡፡ ከሰሜን ወደ ደቡብ 74 .ሜ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ደግሞ 53 ሜትር ይሰፋል፡፡ ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ145ዐ እስከ 4377 ጫማ ባለ ልዩነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካትታል፡፡ 4377 ጫማ የሚረዝመውና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራን ጨምሮ የአፍሮ አልፓይን ከፍተኛ ቦታዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የባሌ ተራሮች ከፍተኛ አካባቢ በተለያዩ መንገድ የተፈጠሩ ሀይቆች፤ እርጥበት አዘል መሬቶች፣ የእሳተ ጎሞራ ቅሪቶችን አቅፎ ይዟል፡፡
ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

ፓርኩን ልዩ የሚያደርጉት የተፈጥሮ አቀማመጡ አፍሮ አልፓይታን (ቀዘወቃዛና ውርጫማው) አካባቢ 1000 ኪ.ሜ ስኩየር በአፍሪካ የመጀመሪያው ፕላቶ መኖሩ፣ በኢትዮጵያ በከፍታው በ2ኛ ደረጃ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራ በመገኘቱ እና ስደተኛና በአካባቢው የሚቆዩ በርካታ አእዋፍ መኖራቸው፤ በኢትዮጵያ ትልቁና ወደ ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዬር የሚሸፍ ነው ‹‹የሐረና ደን›› በውስጡ በመገኘቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ተካቷል፡፡
ከዚህም ሌላ ከ1600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳት፤ 280 የአእዋፍ ዝርያዎች በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 31 የሚጠጉ ብርቅዬና ድንቅዬ የዱር እንስሳትና ወደ ስድስት የሚጠጉ ዕፅዋት በብሔራዊ ፓርኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ዓለም ፈጽሞ አይገኙም፡፡ በባሌ ተራሮች ፓርክ ከሚገኙት 78 አጥቢ የዱር እንሰሳት  17 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሶስቱ ደግሞ በዚህ ፓርክ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንሰሳት ናቸው፡፡

ብርቅዬው ቀይ ቀበሮ-ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
 ከዚህ ባሻገር ለሳይንስና ኢኮሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በደረታቸው የሚሳቡ ልዩ ልዩ እንስሳትና መንቆረርቶችን ፓርኩ አቅፎ ይዟል፡፡ ቡናና በኢትዮጵያ ውስጥ ለባህል መድኃኒትነት የሚውሉ 40 ከመቶ ዕፅዋቶችም ይገኙበታል፡፡ በእፅዋት እና በእንሰሳት ብዝሃ ህይወት መበልፀግ ደረጃ ፓርኩ ከአለም 34ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የባሌ ብሄራዊ ፓርክ በ “Bird lite International” በዓለም ከሚገኙ አስፈላጊ የአዕዋፍ መኖሪያ ቦታዎች ጎራ ተመድቧል፡፡ በፓርኩ ከ28ዐ በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች ሲኖሩ ሰባቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ የወፎች ድርጅት ሪፖርት ከሆነ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የአፍሪካ አራተኛው ‹‹በርዲንግ ሳይት›› ተብሎ ተመዝግቧል፡፡
በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ዋቢ ሸበሌ፣ ዌብ፣ ዱማል፣ ያዶትና ወልመል የተሰኙ ወንዞች ይፈሳሉ፡፡ በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት መካከል ቀይ ቀበሮ፣ ኒያላ፣ አጋዘንና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ፓርኩ አስደናቂ የተራራ እይታዎች፣ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩ ደኖችና የውሃ አካላትን ይዟል፡፡  ወደ ፓርኩ የሚጓዙ ቱሪስቶች የፓርኩን ተራራዎች በእግር በመውጣት /Trekking/ የማይረሳ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ በፓርኩ የሚገኙ የዳንካ፣ ዌብና ሻንያ ወንዞች እና ልዩ ልዩ የውሀ አካላት አሳ በማጥመድ ለሚዝናኑ  ጎብኝዎች የተለየ የእርካታ ምንጮች ናቸው፡፡ አሳ ለማጥመድ ግን ከፓርኩ አስተዳደር ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
ሶፍ ኡመር ዋሻ
ባሌ ዞን የሚያስገርም የተፈጥሮ ስጦታ የሆነውና በአፍሪካ ካሉ ትላልቅ ዋሻዎች አንዱ የሆነው የሶፍ ኡመር ተፈጥሮአዊ ዋሻ መገኛ ነው፡፡ 15.1 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ዋሻ በኢትዮጵያም ረጅሙ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ዋሻው በጊዜያዊ የዓለም ቅርስነትም ተመዝግቧል፡፡
ዋሻው በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ስፍራ ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ሶፍ ኡመር በሚባሉ የሀይማኖት ሰው ነው፤ ዋሻውን በመጠለያነት በመጠቀም ለብዙ ዓመት ኖረዋል፡፡ ወደ ዋሻው መግቢያ በድንጋይ የታጠረ ቦታ ክር ቅዱስ ኡመር ይባላል፡፡ ይኸውም ከበሮ በመምታት የሚያመሰግኑበትና የስለት ከብት በማረድ የሚበላበት ቦታ ነው፡፡ የሚሳሉ ሰዎች ከታረደው በግ (ፍየል) ላይ ትንሽ ቆዳ ተቆርጦ ዋሻ ውስጥ ለፀሎት ይንጠለጠልላቸዋል፡፡ በስተቀኝ በኩል ከዋሻው ፊት ለፊት ወንዙ ውስጥ በጣም ትልቅ የሆነ የተከፈተ መሶብ ቅርፅ ያለው ተፈጥሮ የተራቀቀበት ወጥ ድንጋይ የሆነ የሶፍ ኡመር መቀመጫ አለ፡፡ የሶፍ ኡመር ዋሻ መግቢያ ጉለንተና የውመኩ ሲባል መውጫው ደግሞ ሁልቃ ይባላል፡፡
ጉለንተና የውመኩ የሶፍ ኡመር ልጅ ከራዮሞኩ የምትቀመጥበት ቦታ ነው፡፡ የባትሪውን መብራት በሚሰብረው ጭለማ ወደ ዋሻ ውስጥ ሲገባ ጀባ ቢቂላ የሚባል ትልቅ ክብ ድንጋይ አለ፡፡ በዚህ ቦታ ከድንጋዩ በላይ ግንድ የነበረ ሲሆን ግንዱ ላይ እናትና አባት የረገሟቸው በጣም የሚያስቸግሩ ወጣቶች የሚታሰሩበት (የሚቀጡበት) ቦታ ነው፡፡ ጀባ ቢቂላ የተባለው በሰዓቱ ከታሰሩት ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ጥፋተኞቹ የሚወጡበት ትልቁና ክቡ ድንጋይ በጀርባው በኩል የኢትዮጵያ ካርታን ቅርፅ ይዟል፡፡
ዋሻው የተለያዩና በርካታ ክፍሎች ሲኖሩት ወደ መሀል ሰፊ የሆነ ክፍል አለይህም ፊጢሱማ አብዲ ይባላል፤ በሶፍ ኡመር ልጅ ስም የተሰየመ ቦታ ነው፡፡ ክፍሉ (አዳረሹ) መካከል ላይ በክብ ቅርፅ ጎርጎድ ብሎ ወደ ላይ ከፍ ያለ ሲሆን ተፈጥሮአዊ መሆኑ ያስገርማል፡፡ የተለያየ ገፅታዎችን በማሳየት አንዱን አድንቀን ሳንነሳ ሌላ የተፈጥሮ ገፅታን የሚያሳየን የማያልቅበት ይህ ዋሻ የሶፍ ኡመር አዳራሽ ተብሎ ወደ ተሰየመው ዋሻ ክፍል ያሸጋግረናል፤ በዚህ ክፍል ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሶፍ ኡመር ጋር ተገናኝተው ችግራቸውን የሚያስረዱበት ቦታ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚው የዋሻ ክፍል ደግሞ ስጋጃ የተባለው ነው፡፡ ይህ ክፍል መስገጃ ሲሆን በዚህ ክፍል አራት ትልልቅ ጠፍጣፋና ሰፋፊ ድንጋዮች አሉ፤ እነዚህም የሶፍ ኡመር፣ የሼህ ሁሴን፣ የከራዮ መኮ እና የሼህ አበል ቃሲም መስገጃ ስጋጃዎች ናቸው፡፡
ይሄ ግዙፍ ዋሻ ከአዕምሮ የማይጠፋና እጅግ አስገራሚ የሆነ ተፈጥሮ የተለያየ ኪናዊ ጥበብን ያሳየችበት ስራ ነው፡፡ ጣራው የፋብሪካ ምርት የሆነ ልምድ ባለው ባለሙያ ተስተካክሎ የተገጠመ ወጥ ኮርኒስ ይመስላል፡፡ በዋሻው መሀል የሚጓዘው ዌብ የተሰኘው ወንዝ በውስጡ ሲጓዝ ሰባት ጊዜ የሚታጠፍባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ሁለቱም ተጣምረው መኖራቸው በራሱ ሌላ አስገራሚ ትዕይንት ነው፡፡

 ድሬህ ሼህ ሁሴን በመጀመሪያ ስሙ አንጅና (ያልተቀደሰ መሬት)
ድሬህ ሼህ ሁሴን ኡለማ ሲሆኑ አርሲና ባሌ አካባቢ የእስልምና አስተምህሮ ያስፋፉ ነበር፡፡ አርሲዎችም ባሌዎችም ሼህ ሁሴን የኛ ነው እያሉ ይጣሉ ነበርና ሜዳው (አካባቢው) ለሼህ ሁሴን ተሰጥቶ በሳቸው ስም በጋራ ሼህ ሁሴን ሜዳ በመባል ተሰየመ፡፡ በባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ላይ ሲገኝ ከአዲስ አበባ በ610 ከዞኑ ዋና ከተማ ከሮቤ ደግሞ በ180 .ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ቦታው የቁራአን ትምህርት የሚሰጥበት ሲሆን በየ6 ወሩ ተማሪዎቹን ያስመርቁም ነበር፡፡ ለተመራቂዎች ወላጆቻቸው ስንቅና ስጦታ ይዘው ይመጣሉ፡፡ በዛው ዝየራ (ጉብኝት) ተለመደ፡፡ ሼህ ሁሴን ከሞቱ በኋላም የሳቸው ደቀ መዝሙር ቤተሰቦቻቸውና ተከታዮቻቸው ያንኑ ስርዓት ይዘው ቀጠሉ፡፡ በየ6 ወሩ የእምነቱ ተከታዮች ከ500,000 ህዝብ በላይ በቦታው ይገኛል፡፡ ልዩ የሚያደርገው የማንኛውም እምነት ተከታይ የሆነ በዚህ በዓል ላይ በመገኘት የዝግጅቱ ታዳሚ መሆኑ ነው፡፡
ወደ ድሬህ ሼህ ሁሴን የሚሄዱ ሰዎች ስለት (ናዝሪ) ይሳላሉ፣ ስለታቸው የደረሰላቸው የተሳሉትን ይሰጣሉ፣ ስጦታውን የሚሰጡት ለአካባቢው ማህበረሰብ ሲሆን የገንዘብ፣ የአልባሳትና የቀለብ ስጦታ ያደርጋሉ፡፡ ኬናወሬጋ (የስለት ስጦታ)፣ የእርድ ከብት (ደርጋ) በድሬህ ሼህ ሁሴን ብቻ ተወስነው ለሚኖሩ ሠዎች የሚሰጥ ነው፡፡
በቦታው የሚሄዱ ሰዎች የሚያገኗቸው ነገሮች፡- ምርቃት፣ ጀዋራ (የአካባቢውን አፈር) እንደ መድሀኒትነት ይጠቀሙበታል፣ ዘምዘም (በአካባቢው የሚገኝ ውሀ) ይሄም ሀሮ ልኩ የሚባል ቦታ ብቻ ነው የሚገኘው፤ ሀሮ ኩሬ ሲሆን ልኩ ደግሞ ዶሮ ነው፤ ዶሮ የሚጠጣው ውሀ ስለሆነ ሀሮ ልኩ ተባለ ይባላል፡፡ ውሀው ቁራአን የሚማሩበት ቦርድ (ሎሂ) የተፃፈበትን ቀለም እያጠቡ መልሰው የሚፅፉበት ውሀ ስለሆነ በቁራአን ተጠምቋል ተብሎ በመታመኑ ለፈውስነት ይጠቀሙበታል፡፡
ሼህ ሁሴን በህይወት እያሉ የሰሯቸው በርካታ ስራዎች ሲኖሩ በዋናነትም ዙቅጡም መድረሳ (በህይወት እያሉ የከፈቱት የቁራአን ት/ቤት ይገኝበታል፡፡ የተሰራውም ከድንጋይና ከአፈር ነው፡፡ ዙቅጡም መስጊድ /የፀሎት ቤት/፣ ሶፍ ኡመር ባላ መስጊድ ባለ 40 ምስሶ ሲሆን በአሁን ሰዓት ፈርሷል፡፡ የሼህ ኢብራሂም መስጊድ፣ ሶስት ሠው ሰራሽ ኩሬዎች ማለትም ሀሮ ልኩሀሮ ኡመሮና ሀሮ ድንኩሬ እስካሁን ድረስ ይገኛሉ፡፡
ሼህ ሁሴንን እውቅና ካሰጧቸው ነገሮች መካከል እሳቸው ያስተማሯቸው ተማሪዎች ቁጥር 6666 መድረሱ ነው፡፡ ከተማሪዎቻቸው ያገዟቸውና ለስኬት ያበቋቸው ግን ሶፍ ኡመርና ሼህ ቡልጃጅ፣ ሼህ አሊ ባር፣ አዮመኮ፣ ሼህ ሱልጣን….. ታዋቂ ተማሪዎቻቸው ሲሆኑ ከሀረር ባሌ ቦረና አርሲ ድረስ በመሄድ አስተምህሮታቸውን አሰፉ፡፡ ሲመረቁ የተሻሉ የሚባሉትን ተማሪዎች የተለያዩ አካባቢዎችን ተከፋፍለው እንዲያስተምሩና በየ6 ወሩ ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ የሀረር ኡለማዎች (ሼሆች) የተለያዩ መፅሀፍትን ከውጭ በማስመጣት ይዘው ይመጣሉ፤ ት/ት በመስጠት ልምዳቸውን ይለዋወጣሉ፡፡ ሼህ ሁሴን ድምፃዊና የግጥም ተሠጥኦ ያላቸው በመሆኑ ትምህርቱን በባህላዊ ዘፈን ውስጥ ኢስላማዊ አስተምህሮ ያላቸውን መልዕክቶች በማስገባት በድምፅና በዜማ በማቀንቀን በቀላሉ ሴቶችና ህፃናትን ሌሎቹንም በመሳብ ብዙ ሰዎች የእምነቱ ተከታይ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
ሼህ ሁሴን ሲሞቱ ባሮ እሳቸውን ለማወደስ ባህር (ሆደ ሰፊ) ነህ ባህረ ኪያ ተብሎ ተጀምሮ ባሮ ተብሎ እስካሁን ድረስ ይታወቃል፡፡ ባሮ የሚያወጡ ሠዎች ኡሌ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ኡሌ የተባሉት ሰዎች ባላ ያለው ዱላ ይዘው የሚያዜሙት ኡሌ ሼህ ሁሴን በህይወት እያሉ ይጠቀሙበት ስለነበረ ነው፡፡
ዋሬ ማለት ኡሌ የተባሉት ሰዎች ተሰብስበው ሚያዜሙበት ስፍራ ነው፡፡ እነዚህ ስፍራዎች ደግሞ ድሬ የታወቁ 3 ቦታዎች አሉ፡፡ እነሱም ቶቆካራ፣ ዲንኩሬ፣ ባሮ ጃርሶ በመባል ይታወቃሉ፡፡
ደገሌ፡- እያንዳንዱ ነዋሪ ያለው የድንጋይ (የአፈር) ቤት ደገሌ ይበላል፡፡ ደገሌ ማለት (ማረፊያ) ነው፤ ለነሱ መኖሪያ ቢሆንም ለበዓሉ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ (ለእንግዶች እንደ ማረፊያነት) ስለሚያገለግል ደገሌ ይባላል፡፡
ሀድራ፡- ወንድና ሴቱ አንድ ላይ ተሰብስበው የሚጨፍሩበት ቦታ ሲሆን ከዋሬ የሚለየው ዋሬ ላይ ስለ ድሬህ ሼህ ሁሴን ብቻ እየተነገረ የሚዜምበት ነው፤ በዚህኛው ግን ከበሮና ጭፈራ አለ፤ ሀድራ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሲሆን እሱም ሀጂ አዱም ዝክሪ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህን ቦታ ልዩ የሚያደርገው ምንም ሰው ቢበዛ ያለ ምንም ጥበቃ ሀይል በሠላም ተስተናግደው ይገባሉ፡፡
ገሞ፡- ሼህ ሁሴን ከሞቱ በኋላ ለሳቸው መታሰቢያ የተሰራ ትልቅ ገሞ (ሀውልት) ነው፡፡ ገሞ ሰፊ አጥር ናት፤ ልቅ በድንጋይ ብቻ በጥንታዊ የእጅ አሻራ የተሰራ ነው፡፡ እድሜው 360 ዓመት ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ የሚጎበኙት ገሞ ሼህ ኢብራሂም፣ አዮመኮ፣ ገሞ ሼህ መሀመድ መስኪ (ሽቶ)፣ ሀሮ ሉኩ፣ ሀሮ ድንጉሬ፣ ሀሮ ኡመሮ፣ መስጊድ ዙቅጡም፣ መስጊድ ባላ፣ ገሙ ባላ እና ሌሎችም 13 መስጊዶች አሉ፡፡ በጥቅሉ ስፍራው እጅግ አስደናቂ ሲሆን ተፈጥሮአዊ መስህብ ከሚባሉት ደግሞ ጎዳ አይናገኝ፣ ዶዶላ፣ ጎዳ አዮመኮ ይጠቀሳሉ፡፡

የመካነ ህይወት ተክለ ሃይማኖት ገዳም
የመካነ ህይወት ተክለ ሃይማኖት ገዳም በባሌ ደቡብ ምስራቅ ከጎባ ከተማ በ2.5 .ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በ447.5 .ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ገዳሙ የተመሰረተው ታህሳስ 30 ቀን 1979 .ም. በወቅቱ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት አቡነ ሰላማ ተባርኮ ተገደመ፡፡ ለገዳሙ መመስረት ዋናው ምክንያት የጠበል መገኘት ነው፡፡ የገዳሙ መልክአ ምድራዊ ገፅታው ተራራማ፣ ሸለቆአማ፣ በጣም በሚያምር ደን የተሸፈነ፣ ምንጭ ያለውና ለጎብኝዎች እጅግ ማራኪ በሆነ ቦታ ነው፤ በውስጡ የፅድ፣ የወይራ እና የባህር ዛፍ ዝርያዎች ሲገኙ ደኑን ተከትሎ የተለያዩ አእዋፍ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ጦጣና ጅብ ይገኙበታል፡፡ የገዳሙ የቱሪስት መዳረሻ ሲሆን በየእለቱ ምዕመናንና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ይስተናገዳሉ፣ በአብዛኛው ለጠበል የሚመጣ ሰው የሚበዛ ሲሆን ከ15-30 ቀናት ይቆያሉ፤ ጠበልተኞቹ በሚቆዩባቸው ግዜያት አትክልት በመንከባከብ፣ በችግኝ መትከል፣ በግንባታ ስራ እንደአቅማቸውና እንደየችሎታቸው ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡
በገዳሙ ግቢ ውስጥ የባሞ እና የግንፍሌ ወንዞች መገናኘት ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ ባሞ ወንዝ በገዳሙ በምዕራብ በኩል ገብቶ በምስራቅ ሲወርድ ግንፍሌ ደግሞ በገዳሙ በስተደቡብ ገብቶ በምስራቅ ይወርዳል፡፡ ሁለቱ ወንዞች ሲገናኙ የሚፈጥሩት ፏፏቴ ልዩ ዜማን ይፈጥራል፡፡
በገዳሙ የተለያዩ ሰው ሰራሽ መስህቦችም ይገኛሉ፡፡ 1979 በኋላ ከ7 ዋሻዎች በላይ ተሰርተዋል፡፡ እያንዳንዱን ዋሻ ቆፍሮ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ለመጠቀም ከ14 ዓመታት በላይ ፈጅቷል፡፡ አንዳንዶቹ ዋሻዎች በቤተክርስቲያን ዓይነት የተሰሩ ሲሆን ለመኖሪያነት ያገለግላሉ፡፡ የተወሰኑት ዋሻዎች ቁፋሮ ተጀምሮ መነኮሳቱ ወደ ተለያየ አካባቢዎች በመሄዳቸው ሳይጠናቀቁ የተቀመጡ አሉ፤ አባ ገ/መድህን ተክለሀይማኖት የተባሉ አባት የሰሩት ዋሻ ለቤተክርስቲያንነት አገልግሏል፡፡
በገዳሙ በፈዋሽነታቸው የሚታወቁ 19 ጠበሎች ሲኖሩ 9 ቱቦ ያላቸውና አስሩ ቱቦ የሌላቸው ናቸው፡፡ በገዳሙ ውስጥ የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት፣ ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ የብራና መፅሀፍት ይገኛሉ፡፡ ውዳሴ ማርያም፣ መልከ ማርያም፣ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የግእዝ ቋንቋ፣ ሰዓታት፣ ንባብ፣ ድጓ፣ ዝማሬ፣ መእዋሲት፣ ምዕራፍ በገዳሙ ውስጥ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡
የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለቱሪዝም ዘርፍ ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች
የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዲፓርትመንት ከተቋቋመ ከ2003 .ም. ጀምሮ ሶስት ዓላማዎችን አንግቦ የተነሳ ሲሆን ይኸውም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ናቸው፡፡ ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በምርምር ከፓርኩ፣ ድሬህ ሼህ ሁሴን አካባቢ ካሉ ሰዎች እንዲሁም ከሶፍ ኡመር እና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትም በሶፍ ኡመርና በድሬህ ሼህ ሁሴን ላሉ ማህበረሰቦች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እና በማማከር አገልግሎት ላይ ተሳትፏል፡፡ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማካሄድና ወደ ፕሮጀክት በመቀየር የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት በእቅድ ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢውን የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግም እየሰራ ይገኛል፤ ይኸውም ከአዲስ አበባ-ባሌ፣ ከባሌ-ሀረር ድረስ ለማስተሳሰርና በዚህም ከአዲስ አበባ ባሌ ሲመጣ ድሬህ ሼህ ሁሴንና ሶፍ ኡመርን ጎብኝቶ ወደ መዳ ወላቡ አልፎ ያቤሎ ድረስ በደቡብ (አርባ ምንጭ)ን ለማገናኘት ታስቧል፡፡
የዞኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች
የባሌ ዞን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ዞን ነው፡፡ ሰፊ መሬት፣ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞች፣ እና ሶስት ዓይነት የአየር ፀባይ ያለው ዞን ሲሆን እያንዳንዱን ወረዳ ከወረዳ የሚያገናኝ መንገድ መኖሩ በግብርናውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የተመቸ አካባቢ ነው፡፡ ይኸውም ከፍተኛ የስንዴ ምርት ያለበት አካባቢ በመሆኑ የፓስታና መኮሮኒ፣ የዱቄት ፋብሪካ ቢከፈት አዋጪ መስክ ነው፡፡ ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላ የአየር ፀባይ መኖሩ ዞኑ ምን ግዜም አረንጓዴ እሸት የማይጠፋበት፤ አንዱጋ ሲታጨድ አንዱጋ እሸት፤ ሌላውጋ ደግሞ ለዘር የሚዘጋጁበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ በእንስሳት እርባታ 9 የአርብቶ አደር ወረዳዎች ሲኖሩ በቂ የሆነ መኖ ያለበት አካባቢ ስለሆነ ተመራጭ ዞን ነው፡፡ ባሌ ለግብርና ኢንዱስትሪ እጅግ ተመራጩ ስፍራ ነው፡፡
በቱሪዝም ዘርፍም በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ያሉበት አካባቢ በመሆኑና ከአዲስ አበባ እስከ ዞኑ የአስፓልት መንገድ መኖር፣ ለቱሪስቶች ምቹ አካባቢ በመሆኑ እንግዶችን ለማስተናገድ በቂ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለ መኖራቸው በሮቤና በጎባ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሎጆችን ለመገንቢያ የሚሆኑ ቦታዎች የተዘጋጁ በመሆኑ ኢንቨስተሮች ወደ ዞኑ በመሄድ ኢንቨስት በማድረግ ራሳቸውንም ሆነ ሀገሪቱን መጥቀም ይችላሉ፡፡ ባሌ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያለሙትን ለማሳካት ወደ ስኬት መጓዝ ነው፡፡





                                 















No comments:

Post a Comment