አርኪዎሎጂ
የሰው ዘር መገኛነታችንን ዳግም ያረጋገጠው ግኝት
ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ
መሆኗን ያረጋገጡ የተለያዩ ግኝቶች በተለያዩ ጊዜያት ተገኝተዋል፡፡ የሉሲ(ድንቅነሽ) እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም.፣ አርዲ እ.ኤ.አ
2009 ዓ.ም. እንዲሁም ሆሞሳፒያን ኢዳልቱ እ.ኤ.አ 1997 ዓ.ም. ከተገኙት ግኝቶቹ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት
ፋና ወጊነታችንን የሚያጠናክሩ ግኝቶች እየተገኙ ቢሆንም የመጀመሪያውን የሆሞ የቅድመ ሰው ዘር እድሜ ይታመንበት ከነበረው አመለካከት
የቀየረና 2.8 ሚሊዩን ዓመት ያስቆጠረ ቅሪተ አካል ተገኝቷል፡፡ ይህ በአፋር ክልል በታችኛው አዋሽ ሸለቆ ሌዲ ገራሮ በሚባል የመካነ
መቃብር ስፍራ የተገኘው ቅሪተ አካል የሰው ዘር የታችኛው ከፊል የመንጋጋ ክፍል ሲሆን በስነ-ህይወት ምድብ ጂነስ ሆሞ (Genus Homo) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ይህ ቅሪተ አካል በዋናነት የተገኘው
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባልደረባ በሆነውና በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ በአሪዞና ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪውን
በማጥናት ላይ በሚገኘው ቻላቸው መስፍን አማካኝነት ነው፡፡ ሉሲ ከተገኘችበት 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተገኘው ቅሪተ አካል ከአውስትራሎፒቲከስ
ወደ ኦሞ ዝርያ የተደረገውን ሽግግር እንደሚጠቁም የካቲት 26/2007 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በተሰጠው
ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልፆል፡፡
በስፍራው የተገኙት የባህልና ቱሪዝም
ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር የቅሪተ አካሉ መገኘት የአገሪቱን ገፅታ በመገንባት ረገድ ሁነኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ አዲሱ
ግኝት ኢትዮጵያ በሰው ዘር ግኝት እያበረከተች ያለችው አስተዋፅኦ የኢትዮጵያን ገፅታ በእጅጉ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል፡፡
የጥናቱ መሪና ግኝቱን ይፋ ያደረገችው ዶክተር ኬሮድ እነዚህ ግኝቶች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚጠቁሙ ሲሆኑ ኢትዮጵያ
ከሌሎች አገራት ጋር በፍፁም የማይስተካከል 4.8 ሚሊዮን እድሜ ያስቆጠረ ቅሪተ አካል ያላት ፣ በቅሪተ አካል ብዛት እንዲሁም የኦሞ
ሳፒያን ሰው ዘር የተገኘባት ብቸኛ አገር ናት ብላለች፡፡
ተመራማሪዎቹ ግኝቱ በሉሲ (ድንቅነሽ)
እና በሆሞ ቀደምት ሰው ዝርያዎች መካከል የነበረውን የዝግመተ ለውጥ ጥናት ክፍተት የሚያጠብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በርካታ ግኝቶች በአገራችን
ቢገኙም ምርምር የሚካሄደው በውጪ ሃገራት የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዚህ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ
የቀደመውን አሰራር የቀየረና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ በዚህ ዘርፍ ምርምር ከሚካሄድባቸው ትልልቅ የሳይንስ ላብራቶሪዎች ተርታ የሚመደበው
ስመ ጥር ተመራማሪዎች ተመራምረው ዉጤት የሚያስመዘግቡበት የምርምር ማዕከል መገንባት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ የሰራ ሲሆን ቅሪቱም ሙሉ
በሙሉ ጥናት የተደረገበትና ለውጤት የበቃው በአገራችን በሚገኘው የምርምር ክፍል እንደሆነ የገለፁት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና
ዳይሬክተር አቶ ዩናስ ደስታ አክለውም ከዚህ ጋር ተያይዞ በዋናነት ሊነሳ የሚገባው ነገር ሁልግዜ በውጪ ሀገር ሰዎች ነው ጥናቱን
የምንሰራው? የኛ ሰዎች ተምረው ይህንን ስራ ለምን መስራት አይችሉም? የሚለው ነገር ሲሆን በዘርፉ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ችግሮችና
ፈተናዎች አልፈው ብቅ ያሉ ሁለት ሶስት ተመራማሪዎች ነው ያሉት እነሱን የሚተኩ ያስፈልጉናል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍና ኢትዮጵያውያንን
የምርምሩ አካል ሆኖ ለማስቀጠልና በእውቀቱ ላይ ለማሳተፍ እንዲያስችል በዚህ ዓመት 32 የሚሆኑ የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ሰራተኞችን
የማስተርስና የፒኤችዲ ፕሮግራሞች እንዲከታተሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡ ጥናትና ምርምሩ ይቀጥላል ብዙ ግኝቶችም ይኖራሉ፡፡ እነሱን
እንደገና አስፍቶ ለመጠቀም ሰው ላይ የግድ መፍጠን ይኖርብናል ስለዚህ እነሱ የተማሩት ትምህርት ቤት እነሱ በተማሩት የትምህርት
ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡ በትምህርት ላይ ያሉት አጠናቀው ሲመጡ የምርምሩ መሪዎች ኢትዮጵያውያን
ይሆናሉ ማለት ነው ብለዋል፡፡
እየተሰራ ያለው ስራ ኢትዮጵያ በዘርፉ
በራሷ ተወላጆች የምትመራመርበት ይበልጥ ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዝበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አዲሱ ግኝትም በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክና
ስፍራ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ባመዛኙ መልስ የሰጠ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሰው ዘር ግኝት ያላትን ቀዳሚ ቦታ በድጋሚ ያረጋገጠ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment