Monday, May 27, 2013


ኮንሶ…….

የኮንሶ ህዝብ ገናና ነው፡፡ ስራ ስሙን ከፍ አድርጎት ከጥንት እስከ ዛሬ ብዙ ይወራለታል፡፡ የወረዳ ስያሜ በብሔረሰቡ መጠሪያ ስም ኮንሶ ይባላል፡፡ በደቡብ ክልል ሲገኝ በባህል ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መዳረሻ እየሆነ በመጣው የደቡብ ኦሞ በራፍ የሚገኝ አካባቢ ነው፡፡
ኮንሶ- ካራት
 
አዲሲቷ ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ሥር ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች አንዱ የሆነው ኮንሶ ወረዳ  ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ከሀዋሳ ደግሞ በ365 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በደቡባዊ ምስራቅ ቀጠና ይገኛል፡፡ ለደቡብ ኦሞ ጅንካ ከተማና  ለያቤሎ ሞያሌ መስመር ቀጠና መሆኑ የንግድ ማእከል እንዲሆንም አድርጎታል፡፡

41 የገጠር ቀበሌያትና ሁለት ከተማ አስተዳድሮችን አካቶ የተዋቀረው የኮንሶ ወረዳ ከ236 ሺ በላይ ህዝብ ይኖርበታል፡፡ የኩሽ ቤተሰብ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ኮንሶዎች በሚኖሩበት ምድር ከ500 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸው የብዙ ተመራማሪዎችን ትኩረት ለዓመታት ስበው የኖሩ ቅርሶች ለትውልድ መተው የቻሉ ህዝቦች ናቸው፡፡

ኮንሶ ከባህር ጠለል በላይ ከ500-2010 ሜትር ከፍታ ባለው ስፍራ ሲገኝ በሰሜን ከደራሼ፣ ከቡርጂ አማሮ፣ በስተምዕራብ ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ በደቡብ ደግሞ የኦሮምያ ክልል ያዋስኑታል፡፡ ኮንሶዎች በእጅጉ የታወቀ ለበርካታ ዓመታት የሥነ-ሰውና ሥነ-ምድር ተመራማሪዎችን ትኩረት ስቦ የኖረ መልከአ-ምድር ባለቤት ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጉባኤ ሰኔ 20ቀን 2003 ዓ.ም በፓሪስ ባካሄደው 35ኛው ጉባኤ ኮንሶ በይፋ የአለም ህዝብ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን ያወጀው፤

ምድርን መጠበቅ የሚችሉት የኮንሶ ገበሬዎች በብዛት ማሽላና በቆሎ ያበቅላሉ፣ ቡና ጥጥና አተር በብዛት ሲያመርቱ ሙዝ ጫትና ፓፓዬም በአንዳንድ የኮንሶ አካባቢዎች ይበቅላሉ፡፡ ኮንሶ የተለያዩ የአርኪዎሎጂ ግኝቶችና ቅርተ-አካሎች የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡ በሆሞ ኢረክትስና አውስትሮሊፒቲከስ የሰው ዘር ዝርያዎች የተሞላ ምድር እንደሆነ አጥኚዎች መስክረውለታል፡፡

70 በመቶው የኮንሶ ምድር ቆላማ ነው ቀሪው 30 በመቶው ደግሞ ወይና ደጋማ የአየር ንብረት ሲኖረው አማካኝ አመታዊ የዝናብ መጠኑ ከ601-1200 ሚሊ ነው፡፡ ኮንሶ አሁን የብዙዎችን ትኩረት የሳበ የጎብኚ መዳረሻ የተመራማሪዎች የምርምር ቀጠና የኢትዮጵያውያን የታታሪነት ተምሳሌት መሆኑን አስመስክሯል፡፡

የኮንሶዎች አፈርን የመጠበቅ ጥበብ ከተአምርነት አልፎ የዓለምን ትኩረት የሳበ አንድ የጥቁር ህዝቦች የኩራት መስህብ ለመሆን ችሏል፡፡ አፍሪካውያን ለግብርና ጥበብ ቀዳሚዎቹ ናቸው የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ የሚያጸናው ይህ ኮንሶዎች ከአፈር ጋር ተያይዞ ያላቸው እውቀት ነው፡፡ የእርከን ጥበብ እንዲህ ሳይዘምን፣ የአፈርና ውሃ ተመራማሪዎች ስለ አፈር እና ውሃ ያላቸው እውቀት ሳይልቅ፣ ኮንሶ የዚህ ጥበብ ሰርቶ ማሳያ ማእከል ነበር፡፡

የኮንሶ እርከን ስራ አፈሩን ከመጠረግ ይከላከላል፡፡ ውሃ ያከማቻል፤ የተረፈውን ውሃ ደግሞ ያስወግዳል፡፡ እርከኑ አፈር በመሸከም ለእርሻ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ተራራዎቹ ለኮንሶ እርከን ዋና ገፅታዎች ሲሆኑ በደረቅ ድንጋይ የተሰሩ አላቸው፡፡ የእርከኑ ግንብ እርሻው በደራሽ ውሃ እንዳይጎዳ ይጠብቀዋል፡፡ በአጠቃላይ እርከን የኮንሶዎች የሥራ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሳቢ እና ታይቶ የማይጠገብ አንድ ድንቅ ምትሀት ሆኗል፡፡

ኮንሶዎች የሚታወቁበት ሌላው ተግባር ባህላዊ ደኖች ጥብቅ አድርጎ የማልማታቸው ሚስጥር ነው፡፡ በኮንሶ ጥብቅ ደኖች አሉ፤ የተቀደሱ ደኖች ናቸው፡፡ በጥቅሉ ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህላዊ እሴትን ተችረዋል፤ ይኸ እሴት የላቀ እውቀት ሆኖ ከዓለም ሃብትነት መዝገብ የሰፈረላቸው የኢትዮጵያን ገናናነት ማሳያ ህዝቦች ናቸው፡፡ ይኸ ገናናነት ምናልባትም የሰው ልጅ ለኑሮው መሰረት ከሆነው የግብርና ስራ ጋር በእጅጉ የተቋራኘ ነው፡፡

በኮንሶ ሰሜን በመካከለኛና በምስራቅ በድንጋይ የተገነባው ከተማ ለሁሉም ነገር ስትራቴጂያዊ በሆነ አመቺ ስፍራ ላይ የተገነባ ነው፡፡ ፓሌታ ይባላል፡፡ የግንብ ግድግዳ ከተማ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚሰሩት ከተሞች እስከ ስድስት ዙር በተከበቡ የደረቅ ካብ መከላከያ ግንቦች የታጠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ በእንጨትና በደረቅ ካብ ግድግዳ በተሰራ የግንብ ከተማ ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ እስከ 400 ስኩየር ሜትር ቦታ በመያዝ የሸፈራሁ ተክልና ቡናን በማብቀል እንዲሁም ከብቶችን በማርባት ይኖራል፡፡ የኮንሶዎች ቤት በእንጨትና በጭቃ ይሰራል፡፡ ቤታቸው መኝታ ቤት፣ ዕቃ ቤት፣ ማዕድ ቤትና የከብት ቤትን ያካትታል፡፡

ቤታቸው ሲነሳ መገለጫቸው የሆነው ሞራ የኮንሶዎች አንድ ጥበብ ነው፡፡ ሞራ ኮንሶ ሰብሰብ ባለ ሁኔታ ባህላዊ ከተሞችን በመሰረተባቸው ሁሉ አለ፡፡ በዚህም ሞራ የሚባሉ የመሰብሰቢያ አደባባዮች ይገኛሉ፡፡ ሞራዎች ለኮንሶ በርካታ ጠቀሜታን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሞራ ዳውራ ወይም የክብር ሞራ የሚባለው መንደሩ ሲመሰረት አብሮ የተመሰረተ ትልቅ አክብሮት የሚቸረው የጀብድ ስራዎችን የሰሩ የጀግኖች ወይም የጀብድ መዘከሪያ ትክል ድንጋዮች ሁሉ ሊገኙበት ይችላሉ፡፡ በሞራ ዳውራ ታላላቅ የዓመት በዓል ሥነ-ሥርዓቶች እንዲሁም የስልጣን ሽግግር ሥነ-ሥርዓት ይከበርበታል፡፡ ሞራ ዳውራ ለአንድ አምባ መንደር አንድ ነው፡፡ ሌላው ሞራ ኻኻ ነው የመሃላ ሞራ ይባላል፡፡ ይህ ሞራ አልፎ አልፎ ሞራዱካታ ይሰኛል፡፡ ስፍራው አብዛኛውን ጊዜ ጠፍጠፍ ያለ ድንጊያ ይገኝበታል፡፡ ይኽም ለአንድ አምባ መንደር አንድ ብቻ ነው፡፡

ሶስተኛው የመዝናኛ ሞራ ነው፡፡ እነዚህ በአንድ ሰፈር ውስጥ በቁጥር በርካታ ናቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ይካሄድባቸዋል፡፡ በእነዚህ ሞራዎች ከህፃናት እስከ አረጋውያን የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችን ይጫወቱባቸዋል፡፡ ሞራ ለኮንሶ ህዝብ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ምሽት ላይ የኮንሶ ወጣቶችና ጎልማሳዎች ያድሩበታል፡፡ ባህላዊ የዳኝነትና የእርቅ ሥርዓት የሚከናወነው በሞራ ነው፡፡ ህዝባዊ ስብሰባ፣ ውሳኔዎችን፣ አዳዲስ አዋጆች ይተላለፍበታል፡፡ የተለያየ እድሜ ያላቸው ሰዎች ይዝናኑበታል፡፡ ሞራ መማማሪያ ስፍራ፣ ትውልድ እውቀትን የሚለዋወጥበት ተቋም፣ የስልጣን ርክክብ ማከናወኛ፣ የትውልድ መቁጠሪያ እንጨቶች/ አላሂያ መቆሚያና አኩሬ የትውልድ ወይንም የጀግኖች ጀብድ መዘከሪያ ትክል ድንጋዮች የሚቆሙበት ስፍራም ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ከክህደት ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የማህላ ሥነ-ሥርዓቶች፣ ከማህበረሰቡ ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈፀሙ የውግዘት ማከናወኛዎችም ጭምር ናቸው፡፡

በኮንሶዎች ባህል ለጎሳ መሪዎች ወይም በህይወት ዘመናቸው ጀብዱ ለሰሩ ግለሰቦች መታሰቢያነት በመቃብራቸው ላይ የሚቆሙትና የተለያዩ መልእክቶችን እንዲያስተላልፍ ተደርገው የሚዘጋጁት ከእንጨት ተጠርበው የሚዘጋጁ ሀውልቶች ዋካ ይባላሉ፡፡ በሌላ በኩል ኮንሶዎች በአካባቢው ከዝናብ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የውሃ እጥረት እና የሚያስከስትለውን ችግር ለመቅረፍ በባህላዊ የኮንሶ ተመራማሪዎች የተሰሩ ባህላዊ የውሃ ኩሬዎች ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ የውሃ ማከማቻዎች 10 ዓመትና ከዚያ በላይ ውሃን ይዘው ማቆየት የሚችሉ ናቸው፡፡

ኮንሶ ሲባል ታታሪው ህዝብ ብቻ ዓይደለም ምድሩም ነው፤ ኾንሲታ ይሉታል ኮንሶዎች፡፡ የኮንሶ ወረዳ መዲና በቃ ውሌ በ1974 ዓ.ም ነበር የተቆረቆረችው፤ በቃ ውሌ ዛሬ ካራት የሚለውን ስያሜ ይዛለች፡፡ ከትናንትናዋ በቃ ውሌ የሚለያት የስሟ ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ በቃ ውሌ ትናንትና የነበረች ትንሽ መንደር ነበረች፡፡ ካራት ግን ኢንቨስተመንት ያደመቃት የጎብኚ መዳረሻ እና የንግድ ማዕከል በመሆን በየቀኑ በእድገት ላይ የምትገኝ የኮንሶዎች መዲና ናት፡፡

የካራት ከተማ ስትቆረቆር መነሻ የነበረው ስፍራ የዛሬው አሮጌ ከተማ ተብሎ የሚጠራው ዶካቱ አካባቢ ነበር፡፡ ይህ ስፍራ በከተማው ምስራቃዊ ክፍል ከፍ ብሎ ዛሬም ለምልክት የቀሩ አሮጌ ቤቶች ይገኙበታል፡፡ በቃ ውሌ በ1949 ዓ.ም ነበር፡፡ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ ህጋዊ እውቅና አግኝታ የከተማነት እድገትን የጀመረችው፡፡ የዛሬዋ ካራት 544 ሄክታር የቆዳ ስፋት ሲኖራት 5787 የሚደርስ ህዝብ ይኖርባታል፡፡ ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት በጅማሬ ማስተር ፕላን ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ አራት በር ያላት ካራት በዋናነት በአርባ ምንጭ በኩል ከአዲስ አበባና ሀዋሳ የሚያመጣው ሲሆን ሁለተኛው ወደ ጂንካ በኩል ደቡብ ኦሞ የሚወስደው ነው፡፡ ይኽ ከየአቅያጫው ወደ ካራት የሚገባው መንገድ ካራት የንግድ ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ዛሬ በካራት አደባባይ የኮንሶ ባህላዊ መልከአ ምድር የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን የሚያውጀው አደባባይ ቆሞባታል፡፡ ይህንን በዓለም ቅርስ መዝገብ ያስመዘገበችበትን ዓመታዊ በዓል ለማክበር ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡  

No comments:

Post a Comment